

የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ገጽታ
ኪንና ባህል ድጋፍ የሚሻው ሃይማኖታዊና መንግሥታዊው የታሪክና የቅርስ መድበሉ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል
ቀን:
April 21, 2024
Share
በኢትዮጵያ እጅግ ልዩ ኪነ ሕንፃን የተላበሰው የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ነው። ይህ ከዘጠኝ አሠርታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው ካቴድራል በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ (1923-1967) አማካይነት የተገነባ መሆኑ ታሪኩ ይናገራል፡፡
ካቴድራሉ መታሰቢያነቱ በአምስቱ የፋሺስት ጣሊያን ወረራ ዓመታት ለተዋጉት አርበኞች ሆኖ፣ ድኅረ ጦርነት ቅዳሴ ቤቱ ከተባረከ በኋላ በባህር የተጣሉትን፣ በገደል የወደቁትንና በማይታወቅ ቦታ የረገፉትን አርበኞች ዐፅም ተሰብስቦ በክብር ያረፈበት ነው፡፡

የንጉሠ ነገሥት ቤተ ዘመድና ለቤተ ክርስቲያንና ለመንግሥት ታላላቅ ሰዎች የዕረፍት ሥፍራ ከመሆንም ባለፈ የፓትርያርኮችና የሊቃነ ጳጳሳት የሹመት በዓል የሚፈጸምበት ቦታ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡
ድኅረ ዘውዳዊ ሥርዓትም በመጡት መንግሥታት ከርዕሰ ብሔራን ጀምሮ ታላላቅ ሹማምንት መካነ መቃብር እየሆነም ነው፡፡
በዕድሜው ርዝማኔ ምክንያት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በካቴድራሉ ውስጣዊና ውጫዊ አካሉ ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ለችግር የሚያጋልጠው ሆኖ በመገኘቱ በአሁኑ ወቅት እየታደሰ ይገኛል፡፡
ዕድሳቱን ለማጠናቀቅም ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ካቴድራሉ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
የካቴድራሉ አስተዳዳሪ ሊቀ ሥልጣናት ቆሞስ አባ ሲራክ አድማሱ ከዕድሳት ኮሚቴ አባላት ጋር በመሆን ሚያዝያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ ዕድሳቱን በ172 ሚሊዮን ብር ከሚያድሰው ቫርኔሮ ከተባለ ድርጅት ጋር ውል ገብቶ እየተካሄደ መሆኑንና አጠቃላይ የሕንፃ ጥገና ሥራው 75 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል፡፡
ከ90 ዓመታት በላይ አገልግሎት የሰጠው ካቴድራሉ ልዩ የኪነ ሕንፃ ጥበብን የተሞላ ከቤተ ክርስቲያኗ ባለፈ የአገር ቅርስ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለኮንትራክተሩ ክፍያ የሚፈጸመው ከምዕመናን ከሚሰበሰብ ገንዘብ መሆኑን በመግለጽም በተለያዩ ምክንያቶች ለክፍያ የሚሆን በቂ ገንዘብ ማግኘት አዳጋች ስለሆነ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ድጋፉን እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የካቴድራሉ ዕድሳት ከሦስት ወራት በኋላ እንደሚጠናቀቅ የገለጹት ሊቀ ሥልጣናት አባ ሲራክ፣ እስካሁን ለዕድሳቱ የተሰበሰበው 90 ሚሊዮን ብር መሆኑን ቀሪው 85 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ እሑድ ሚያዝያ 13 ቀን በኢንተር ኮንቲነንታል ሆቴልና ሚያዝያ 19 ቀን የቀጥታ ሥርጭት ገንዘብ ማሰባሰብ መርሐ ግብር መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡
ካቴድራሉ ከምዕመናን ከሚያገኘው ውጪ የገቢ ምንጭ እንደሌለው፣ በዙሪያው የሚገኙት ሕንፃዎች ግን የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ እንጂ የካቴድራሉ ንብረት አለመሆናቸውን የገለጹት አስተዳዳሪው፣ በአገር ውስጥና በውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያንና በጎ ፈቃዱ ያላቸው ሌሎችም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በካቴድራሉ ከሚገኙት ታሪካዊ ቅርሶች መካከል ከ1927-1933 ዓ.ም. የጦር ሠራዊት ሰንደቅ ዓላማ፣ የክብር ዘበኛ ሰንደቅ ዓላማ፣ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የጦር ተማሪ ቤት ሰንደቅ ዓላማ፣ ከ1927 እስከ 1933 ዓ.ም. ድረስ በጦር ሜዳ የወደቁ ጀግኖች ሰንደቅ ዓላማ ከተሸለሙት ከታላቁ የሥላሴን ኒሻን ኮርዶን ጋር ይገኙበታል፡፡