April 21, 2024

ርዕሰ አንቀጽ

የኪነ ጥበቡ ዘርፍ በተለይም ፊልምና ሙዚቃ በውስብስብ ችግሮች ውስጥ እያለፈ ይገኛል፡፡ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ሲስተም በአግባቡ አልተበጁለትም፡፡ ስለሆነም ይህ ችግር ከመሠረቱ እየተፈታና እየተቀረፈ ካልሄደ ከዓመት ዓመት በተመሳሳይ መንገድ ከመጓዝ የዘለለ ለውጥ አይኖርም፡፡

ትኩረቱን በኢትዮጵያ ሙዚቃና ፊልም ላይ ያደረገ የጥበባት ኢንዱስትሪ ጉባዔ ‹‹ሰላም ኢትዮጵያ›› በተባለ ድርጅት አስተባባሪነት በሚያዝያ መባቻ ተካሂዷል፡፡

ስልታዊ መፍትሔን የሚሻው የኪነ ጥበቡ ዘርፍ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

የሰላም ኢትዮጵያ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ተሾመ ወንድሙ እንደተናገሩት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የባህልና የኪነ ጥበብ ዘርፍ እያደገ መጥቷል፡፡ ዘርፉን ለማሳደግና የሚገባው ከፍታ ላይ ለማስቀመጥ ከባለሙያዎች፣ ከመንግሥትና ከባለድርሻ አካላት ጋር መድረክ ፈጥሮ መወያየትና ለችግሮቹም መፍትሔ ማበጀት ይገባል፡፡

በቅጅ መብቶች፣ በፖሊሲና ስትራቴጂ ጉዳዮች መድረክ በመፍጠር ባሉ ችግሮችና ምቹ ሁኔታዎች ዙሪያ ውይይት በማካሄድ ዘርፉን ውጤታማ ማድረግ ይቻላል፡፡

በሥራ አስኪያጁ አገላለጽ፣ የባህልና የኪነ ጥበብ ዘርፉ በተፈለገው ልክ እንዲያድግ በትምህርት መደገፍ ይኖርበታል፡፡ ለሙዚቃ ዘርፉ ማደግ አስተዋጽኦ ያላቸውን እንደ ፕሮዲውሰር፣ ሳውንድ ኢንጂነር፣ ስቱዲዮ ቴክኒሺያንና የመሳሰሉ ትምህርቶች ሥርዓተ ትምህርት ተቀርፆላቸው በትምህርት ተቋማት መሰጠት ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ ዙሪያ አጽንኦት ሰጥቶት  ሊሠራበት ይገባል፡፡

የኪነ ጥበቡ ዘርፍ እንዲያድግ ማኅበረሰቡ ለባለሙያው ክብር ሊሰጥ  ይገባል ያሉት አቶ ተሾመ፣ ኅብረተሰቡ ለሁነቶችና ለዲጂታል ስትሪሚንግ ቻናሎች ክፍያ መፈጸም እንደሚኖርበት ይህንን ለማስፈጸም ደግሞ ሕግ መውጣት ይኖርበታል ብለዋል፡፡

ሙዚቃና ፊልምን በተመለከተ የገበያ ጥናት በመሠራት ላይ መሆኑንና በቅርብ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የተናገሩት አቶ ተሾመ፣ ጥናቱ ከዳሰሳቸው ጉዳዮች አንዱ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ባህል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በጥናቱም መሠረት 84 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ማዳመጥ የሚፈልገው አገርኛ ሙዚቃ ነው፡፡ እንደ ጃዝ፣ ሂፕ ሆፕ፣ አርኤንድቢ፣ ሬጌና የመሳሰሉት ሙዚቃዎች ግን ለሕዝቡ ያለውዴታ እየቀረቡለት የሚገኙ ናቸው ብለዋል፡፡  

ድምፃዊ ሔኖክ መሐሪ በበኩሉ፣ እንደ አገር በሙዚቃው ዘርፍ በርካታ ችግሮች ያሉ ቢሆንም ከችግሮቹ በላይ መፍትሔ ላይ አተኩሮ መሥራት እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡  

ማኅበራቸው በአሁኑ ወቅት ሮያሊቲን በተመለከተ አመርቂ የሚባሉ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ መሆኑን፣ እየተሠራ ያለው ሥራ ሲጠናቀቅም የሙዚቃ ኢንዱስትሪው ላይ ጉልህ ለውጥ የሚያመጣና የድምፃውያኑንም የኢኮኖሚ ችግር በአንድ ደረጃ ያቃልላል ተብሎ ይጠበቃል ብሏል፡፡

በኪነ ጥበብ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች ላይ የሚደርሱ የመብት ጥሰቶች በተለይም የኢኮኖሚ መብት የተነፈጋቸውና መከፈል የሚገባቸውን ያህል ክፍያ ያልተፈጸመላቸው በርካታ ናቸው ያለው ድምፃዊው፣ ለ40 ዓመታት ያህል ከሥራቸው ማግኘት የሚገባቸውን ገቢ ሳያገኙ የቆዩ ገጣሚያንና የዜማ ደራሲያን ጥቂት እንደማይባሉ አውስቷል፡፡

እንደ ድምፃዊ ሔኖክ፣ አንድ ሙዚቀኛ ‹‹ሲታመም እንርዳው፣ ገንዘብ የለውም›› የሚባለው ሀብቱ በሰው እጅ ላይ በመኖሩና እርሱ ኪስ ውስጥ ሊገባ ባለመቻሉ ነው፡፡ ሀብቱን የኢትዮጵያ ሕዝብ እየተገለገለበትና እየተጠቀመበት ሙዚቀኛው ግን ከሀብቱ ፍሬ ተቋዳሽ አልሆነም፡፡

በውጭ አገሮች በተለይ በሠለጠነው ዓለም አንድ ሙዚቃ በተለያዩ ስትሪሚንጎች በተደመጠ ቁጥር ለድምፃዊው የሚከፈል ክፍያ አለ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ይህ ልምድ ባለመኖሩና የሮያሊቲ መብት ባለመጠበቁ አርቲስቶች በሥራቸው ተጠቃሚ ሳይሆኑ ለዓመታት ቆይተዋል፡፡  

ድምፃዊ ሔኖክ እንደሚናገረው፣ ከሮያሊቲ ባሻገር አንድ ሙዚቃ ቤት በ1970 ዓ.ም. ያሳተመውን አልበም ሳያሳድስ በየዓመቱ፣ በየአሥር ዓመቱና ባሻው ሰዓት እያባዛ ይሸጣል፡፡ ይህ ትልቅ ወንጀል ነው፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በሙዚቃ ውስጥ ያሉ እኚህና እነኚህን መሰል ችግሮች ደረጃ በደረጃ በመቅረፍ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት እየተሠራ ይገኛል፡፡

የአክሽን ሚዲያ ባለቤትና የፊልም ባለሙያ የሆነው ሔኖክ መብራቱ እንደሚገልጸው፣ ‹‹ሰላም ኢትዮጵያ›› እንዳዘጋጀው ዓይነት ያሉ መድረኮች ለፊልሙና ለሙዚቃው ዕድገት ከፍ ያለ አበርክቶ ይኖራቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከሌሎች የኪነ ጥበብ ዘርፎች በተለየ የፊልሙ ዘርፍ ፖሊሲ ተቀርፆለት ይገኛል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2017 ፖሊሲው የተዘጋጀ ቢሆንም በዘርፉ ግን የሚታይና የተፈለገውን ያህል ለውጥ ሊመጣ አልቻለም፡፡

ፖሊሲውን መሬት ለማውረድና ተግባራዊ እንዲሆን ለማስቻል ስልታዊ (ስትራቴጂክ) ሰነድና ተቋማዊ ማዕቀፍ ከዩኔስኮ ጋር በመሆን ተሠርቷል፡፡ ሆኖም ግን ወደ ተግባር ሳይተረጎም መደርደሪያ ላይ ተቀምጦ ቀርቷል፡፡ በመሆኑም እንዲህ ዓይነት መድረኮች በመንግሥትም ሆነ በባለድርሻ አካላት የተዘነጉትን ጉዳዮች ወደፊት እንዲመጡ፣ እንዲታወሱና እንዲተገበሩ በማድረግ በኩል የራሳቸው የሆነ አዎንታዊ ጎን አላቸው፡፡  

እንደ ባለሙያው፣ ከሥዕልና ከሙዚቃ በላይ ፊልም የቡድን ሥራን የሚጠይቅ ነው፡፡ በመሆኑም በሙያው ውስጥ ያሉ አርቲስቶች እርስ በርስ በመደጋገፍና በመተባበር ዘርፉን ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሙያ ማኅበሩም፣ በፊልሙ ውስጥ የሚታዩ ችግሮችን በማስወገድና ሜዳውን በማመቻቸት በኩል አፅንኦት ሰጥቶ መሥራት ይገባዋል፡፡