የዕድርና የዕድር ምክር ቤቶች የምዝገባና ዕድሳት አሰጣጥ መመርያ ዙሪያ ውይይት ተሳታፊዎች

ማኅበራዊ ዕድሮችን የማዘመን ጅማሮ

አበበ ፍቅር

ቀን: April 21, 2024

የአንድ አካባቢ ሰዎች ዘርና ሃይማኖትን ሳይለዩ በመሰባሰብ የራሳቸውን መተዳደሪያ ደንብ አውጥተው በሐዘንና በደስታ በመገናኘት የሞተን የሚቀብሩበት የደከመን የሚረዱበት ነው፡፡

ዘመናትን ተሻግሮ ለዛሬ ትውልድ የበቃ ትልቅ አገራዊ ተቋም ነው። ተቋሙ በሐዘንና በደስታ ጊዜ ብቻ ሳይሆን፣ የበደለን ቀጥቶ ተበዳይን ክሶ የተጣላን  ያስታርቃል፡፡

ዕድሮችን የማዘመን ጅማሮ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ብዙ ሰዎች ወደ ዕድር የሚገቡት፣ መዋጮ የሚያወጡት፣ ለሕግና ለደንቡ ተገዥ የሚሆኑት በዋናነት እራሳቸው ወይም ከቤተሰብ አባላቸው አንዱ በሚሞት ወቅት ለሚደረገው የቀብር ክንውን ሲሉ ነው።

ዕድር የገባ ሰው ሐዘን ቤቱ ሲገባ ሲሞት የሥጋ ዘመድ በቅርብ ኖረ አልኖረ ብሎ አይጨነቅም፡፡ ማን ያቃብረኛል ብሎ አያስብም፡፡ ከዕድር አባላት ውስጥ ሞት ቤቱ የገባ ወይም በሞት የቀደመ ሰው ከሞተበት ደቂቃ ጀምሮ ግብዓተ መሬት ተፈጽሞ  ለቀብር ከሩቅ የመጡ ዘመድ ወዳጆች እስኪሸኙ ሦስተኛው ቀን (ሰልስት) ድረስ  የሚከናወኑ ሥርዓቶች የሚከወኑት በዕድር አባላት አስተባባሪነት ነው። ዕድር ለብዙዎች ሐዘን ቀዳሚ ደራሽም ነው፡፡

በገጠር አካባቢ ‹‹ዕድር ለምኔ›› ብሎ ራሱን ያገለለ ሰው፣ አይደለም የሰው ሞት የከብት ሞትም ሲያጋጥመው ችግሩ የከፋ ይሆንበታል።

በመሆኑም የአካባቢው ሰዎች ዕድር ያልገባ ካለ እንዲገባ መወትወታቸው የተለመደ ነው፡፡ ከተሜዎችም ጠንከር ያለ መተዳደሪያ ደንብ አውጥተው ዕድርን ይጠቀሙበታል።

በተለይ ለመቃብር ቦታ መሬትን ቆርሶ መስጠት አካልን ቆርሶ እንደመስጠት በሚቆጠርባት አዲስ አበባ፣ ዕድር ያልገባ ሰው የዘላለም ማረፊያውን ለማግኘት አዳጋች ይሆንበታል።

በመዲናዋ ከሰባት ሺሕ በላይ ዕድሮች ይገኛሉ ተብሎ ይታመናል። እነዚህ ዕድሮች የሞተን ከመቅበር ባሻገር በአካባቢ ልማት ላይ ትልቅ ተሳትፎ አላቸው። ተሳትፏቸውን ይበልጥ ለማጎልበት በየወቅቱ የተለያዩ አሠራሮች እየተዘረጉ፣ የራሳቸው መተዳደሪያና መመርያዎችን በማውጣት እየተሻሻሉ ቢመጡም፣ አሁንም መዘመን የሚኖርባቸው አሠራሮች እንዳሉ ይታመናል።

ሆኖም ከማኅበራዊ እንቅስቃሴ ባሻገር ራሳቸውን በኢኮኖሚ አጎልብተው ትልልቅ ፕሮጀክቶችን እስከማቋቋም የሚያስችል ዘመናዊ አሠራር በመዘርጋት የሚንቀሳቀሱ ዕድሮችም ከመንግሥት በኩል አስቻይ አሠራር አልተዘረጋላቸውም፡፡

በስማቸው ያለን ሀብት መሸጥና መለወጥ አይችሉም የሚሉና ሌሎች በሕግ ያልተደገፉ አሳሪ መመርያዎች ለሥራቸው እንቅፋት ሆነው እንደቆዩባቸው የዕድር ምክር ቤት አባላት ይናገራሉ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በዕድሮች ዙሪያ የሚታዩ የአሠራር ክፍተቶችን ይቀርፋል የተባለና በዘልማድ የነበሩ አሠራሮችን ሕጋዊ ማዕቀፍ እንዲኖራቸው የሚያስችል የዕድሮችና ዕድር ምክር ቤቶች የምዝገባና ዕድሳት አሰጣጥ መመርያ ቁጥር 151/2016 በፍትሕ ሚኒስቴር አፀድቆ ወደ ሥራ ገብቷል።

በወጣው መመሪያ ላይ ውይይት ያደረጉ የእድር ምክር ቤቶች ተወካዮች፣ መመሪያው በተለይ የአፈፃፀም ችግር ካልገጠመውና ጣልቃገብነት ከሌለበት የተሻለ እንቅስቀሴ ለማድረግ በር የከፈተ እንደሆነ ተናግረዋል።

ተጠሪነቱን የተረከበው የከተማዋ ሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በበኩሉ፣ የወጡ መመርያዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ፣ ዕድሮች ተመዝግበው ዕውቅና እንዲኖራቸውና በኢኮኖሚ አቅማቸው ይጎለብቱ ዘንድ ለመደገፍ ካልሆነ፣ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ ይገልጻል።

ቢሮው በዕድሮች ላይ ዝርዝር ተግባርና ኃላፊነቶች እንዳሉት በመመርያው በስፋት የተዘረዘረ ሲሆን፣ በአንቀጽ 18 ንዑስ አንቀጽ 3 ላይ ‹‹የዕድሮችን መረጃዎች ይሰበስባል፣ ያደራጃል፣ ይተነትናል እንደ አስፈሊጊነቱ ለሚመለከታቸው አካላት ያሠራጫል›› በሚለው ሥር “ያደራጃል” የሚለው ሐሳብ ጣልቃ ገብነት እንዳያስከትል የዕድር ምክር ቤት ሀላፊዎች ስጋታቸውን ተናግረዋል።

ቢሮው በበኩሉ፣ በትግበራ ወቅት እነዚህና መሰል ለአሠራር አመች ያልሆኑ ችግሮች ቢፈጠሩ ቅሬታ በማቅረብ መስተካከል እንደሚችሉ አሳውቋል።

በመመርያው መሠረት፣ ዕድሮች ወይም በየደረጃው የሚገኙ የዕድር ምክር ቤቶች ለዓላማቸው ማስፈጸሚያ ሊውሉ በሚችሉ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ ሊሠማሩ ይችላሉ፡፡

በገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ የሚሠማራ ዕድር የተለየ ሒሳብ መዛግብት መያዝ የሚኖርበት ሲሆን፣ በአገሪቱ ሕግ መሠረት መሟላት የሚገባውን መሥፈርትና ሌሎች ግዴታዎች አሟልቶ መገኘት ይኖርበታል፡፡

የተመዘገበ የዕድር ወይም የዕድር ምክር ቤት መብቶች፣ ውል የመዋዋል፣ የንብረት ባለቤት መሆን፣ በራስ ስም የመክሰስና የመከሰስና ለሌሎች ሕጋዊ ሰውነት ላላቸው አካላት የተሰጡ መብቶች ይኖሩታል።

የአገሪቱን የንግድ ሕጎችና አዋጆች እንዲሁም የከተማው አስተዳደር አሠራሮችን በማክበርና ተገቢውን መሥፈርት አሟልተው ሲገኙ፣ የገቢ አቅማቸውን ለማሳደግና ማኅበራዊ ችግሮቻቸውን ለመፍታት ሁለገብ የአገልግሎት የኅብረት ሥራ ማኅበር ማቋቋም ይችላሉ፡፡

ዕድሮች ከተመሠረቱ ጀምሮ ሲጠቀሙበት የነበረውን ይዞታ እንደማንኛውም አካል ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ተገቢውን መሥፈርት አሟልተው ከተገኙ የይዞታ ባለመብት የመሆንና በሕገ ደንቡ መሠረት በልማት ሥራዎችና በማኅበራዊ ጉዳይ የመሳተፍ መብቶች ይኖራቸዋል፡፡