

ቻምፒዮንስ አካዳሚ የኦቲዝም የግንዛቤ ማስጨበጫ ቀንን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል
ማኅበራዊ ኦቲዝም በደሃዎች ጓዳ
ቀን: April 21, 2024
ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ልጆችን እንደ ባህሪያቸው ተንከባክቦ ማሳደጉ እንኳን በድህነት ለሚኖሩ ወላጆች፣ ሀብታም የሚባሉትንም የሚፈትን ነው፡፡ በተለያየ ደረጃና ዓይነት የሚገለጸው ኦቲዝም ከተጓዳኝ የጤና እክል ጋር ሲመጣ ደግሞ ችግሩን ያጎላዋል፡፡ ኦቲዝምን ጨምሮ ከአዕምሮ ሕመም ጋር የተያያዙ ችግሮችና የአካል ጉዳት ያለባቸውን ልጆች የመንከባከብ ኃላፊነቱ የሚወድቅባት እናት ደግሞ ይበልጡኑ ትፈተናለች፡፡
በተለይ ችግሩ ያለባቸው ልጆች ሲወለዱ አባቶች ቤት ጥለው የሄዱባቸው እናቶች አሊያም ቤትም ሆነው እምብዛም ድጋፍ ለመስጠት የማይፈልጉ አባቶች መኖራቸው ጫናው በእናቶች ላይ እንዲበረታ አድርጓል፡፡
ትንሽ አቅም አግኝተው መዋያ ማዕከል መውሰድ የቻሉትም ቢሆኑ፣ ማዕከላት ዘላቂነት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ባለባቸው ክፍተት ምክንያት መፈተናቸው አልቀረም፡፡ አነስተኛ ገቢ ወይም ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ በሚገፉ ቤተሰቦች ውስጥ ኦቲዝም ያለበት ልጅ ሲጨመር ደግሞ ጫናውም የበዛ ነው፡፡
የኦቲዝም ወርን አስመልክቶ በተለያዩ ድርጅቶች በተዘጋጁ መድረኮች የተገኘው ሪፖርተር ጋዜጣም ይህንኑ ለመታዘብ ችሏል፡፡ በርካታ ኦቲዝም ያለባቸው ልጆቻቸውን የሚያሳድጉ እናቶች በድህነት የተፈተኑ፣ ልጆቻቸውን ለማኖር ላይ ታች የሚሉና የሚኳትኑ ናቸው፡፡
ወ/ሮ ሊጢፋ ጊዲ በኦቲዝም ጥላ ሥር የምትኖረው የስምንት ዓመቷ ተስሊም መሀዲ እናት ናቸው፡፡
ወ/ሮ ሊጢፋ እንደሚናገሩት፣ ልጃቸውን ከአራት ዓመቷ ጀምሮ በማዕከል ውስጥ የሞግዚት እየከፈሉ እንድትማር ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡
ልጃቸው ወደ ማዕከሉ ከመግባቷ በፊት ሽንቷን መቆጣጠር ስለማትችል ዳይፐር ትጠቀም ነበር፡፡ ምግቧን በራሷ እጆች መመገብ አትችልም፡፡ በማዕከሉ ባገኘችው ሥልጠና ግን አሁን ላይ ራሷን ችላ መፀዳጃ ቤት ትሄዳለች፣ ምግቧንም ያለሰው ዕርዳታ እየተመገበች ነው፡፡ በማዕከል ቆይታዋ ከባህሪ ለውጥ ጀምሮ ብዙ መሻሻሎችን አሳይታለች፡፡
ሆኖም ግን ማዕከሉ ሌሎች አገልግሎት የሚፈለጉ ሕፃናትን ለማስተናገድ በሚል ሕፃን ተስሊምን ወደ ቤታችሁ ይዛችሁ ሂዱ ወይም ሌላ ቦታ ፈልጉላት በማለቱ ወ/ሮ ለጢፋ ተጨንቀዋል፡፡
የተከራየሁት ቤት ውስጥ ልጄን ለማዋል እጅግ ከባድ ነው፡፡ ልጄ ከኦቲዝም በተጨማሪ ተደራራቢ የጤና ችግር ያለባት በመሆኑ፣ ሰዎች እንደ ተላላፊ በሽታ በመቁጠር ያገሏታል፡፡ ከእርሷ ጋር ሰባት ቤተሰብ ይዤ በስቃይና በፈተና ውስጥ እገኛለሁ ሲሉ ይናገራሉ፡፡
ወ/ሮ አዳነች ጌታቸው፣ አብርሃም ሰለሞን የተባለ ከኦቲዝም ጋር የሚኖር የአምስት ዓመት ልጅ አላቸው፡፡ በልጃቸው ምክንያት በርካታ እንቅልፍ አልባ ሌሊቶችንና ውጥረት የተሞላበት ሕይወት በማሳለፍ ላይ ናቸው፡፡
‹‹ልጅሽ እያለቀሰ እንቅልፍ ነሳን›› በሚል ምክንያት ቤት አከራዮቻቸው በ12ኛ ቀናቸው ከአራስ ቤት ቤት ፈልጊ በማለት እንዳባረሯቸው ይናገራሉ፡፡
እንጀራ በመጋገርና ልብስ በማጠብ የሚተዳደሩት ወ/ሮ አዳነች፣ ከኦቲዝም ጋር የሚኖር ልጃቸውን ተቀብሎ የሚደግፍና የሚያግዝ ተቋም በማጣታቸው ከትምህርት ገበታ ርቆ ይገኛል፡፡
የተሻለ ቤት ተከራይተው እንዳይኖሩ፣ በልጃቸው ምክንያት የሚያስጠጋቸው ባለመኖሩ የፈራረሰና የወደቀ ቤት ውስጥ ለመኖር መገደዳቸውን ይገልጻሉ፡፡
ወ/ሮ መዓዛ መንክር የአዕምሮ ሕክምና ባለሙያና አማካሪ ናቸው፡፡ የቻምፒዮንስ አካዳሚ ባለቤትና የኦቲዝምና የዕድገት እክል ላለባቸው ልጆች ይጠቅማል በሚሉት ‹‹ሁሉም በአንድ ተግባር ተኮር›› የሕክምና መጽሐፍ በማዘጋጀትም ይታወቃሉ፡፡
ወ/ሮ መዓዛ እንደሚናገሩት ኦትስቲክ፣ ኦቲዝም ልጆች ከሌሎች የሚለዩት በሚማሩበት መንገድ ነው፡፡ እንደማንኛውም ልጅ ይጫወታሉ፣ ይደሰታሉ፣ ውጤታማ መሆንም ይችላሉ፡፡
ተጨማሪ የጤና እክል ከሌላቸው በስተቀር ከሌሎች ልጆች የተለየ ምንም ዓይነት አካላዊ መገለጫ የላቸውም፡፡ እንደ ማንኛውም ልጅ የሚሮጡ፣ የሚስቁና የሚደሰቱ ናቸው፡፡
ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች ከተወለዱ እስከ ሦስት ዓመት ባለው ጊዜ በሚያሳዩት ባህሪና ማኅበራዊ ግንኙነት ላይ ተመሥርቶ በሚደረግ ምርመራ ኦቲዝም እንዳለባቸውና እንደሌለባቸው ለማወቅ ይቻላል፡፡
ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች በለጋ ዕድሜያቸው ተገቢውን ትምህርት፣ ሥልጠናና ክትትል ካገኙ ውጤታማ ከመሆን የሚያግዳቸው ነገር አይኖርም፡፡
እንደ ወ/ሮ መዓዛ፣ አብዛኞቹ ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች ተደራራቢ የጤና ችግር አለባቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል ትኩረት የማጣትና የመረጋጋት ችግር፣ የሚጥል ሕመም፣ የእንቅልፍ ችግርና ሌሎች የጤና እክሎች ሲኖሯቸው ችግሩን የበለጠ ሊያወሳስበውና በውጤታማነታቸው ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል፡፡
ኦቲዝም ብቻውን ከሆነና ሌላ የጤና ችግር አብሮት ከሌለ በትምህርትና በሥልጠና ልጆቹን በማገዝ ወደሚፈለገው ውጤት ማምጣት ይቻላል፡፡
ቻምፒዮንስ አካዳሚ የኦቲዝም ልጆችን ከመደበኛ ተማሪዎች ጋር አካቶ ማስተማር ከጀመረ አሥራ ስድስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በእነዚህም ዓመታት በርካታ ልጆችን በትምህርትና በሥልጠና በማገዝ ትርጉም ያለው ሕይወት እንዲኖሩ በማድረግ ረገድ የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
እንደ ወ/ሮ መዓዛ አካዳሚው ከሦስት እስከ ሰባት ዕድሜ ያላቸውን ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ልጆች በክፍያ ተቀብሎ ያስተምራል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ከ1500 እስከ 1800 የሚሆኑ ልጆች ይህንን ዕድል ለማግኘት ተመዝግበው በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡
በዓለም አቀፍና በአገር ደረጃ እየተከበረ የሚገኘውን የኦቲዝም ቀን ምክንያት በማድረግ ከወላጆች፣ ከተማሪዎችና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ሚያዝያ 5 ቀን 2016 ዓ.ም. ያከበሩ ሲሆን፣ ዕለቱን በማስመልከትም ከሦስት እስከ አምስት ዓመት ዕድሜ ክልል ለሚገኙ 25 ልጆች ለአንድ ሳምንት የሚቆይ ነፃ የምክርና የምርመራ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀቱን ወ/ሮ መዓዛ ተናግረዋል፡፡
የትኩረት ለሴቶችና ለሕፃናት ማኅበር መሥራችና ዳይሬክተር ሲስተር አሳየች ይርጋ በበኩላቸው፣ ማኅበሩ ከምሥረታው ጀምሮ ላለፉት አሥራ ሰባት ዓመታት በአዲስ አበባ፣ በደቡብና በኦሮሚያ ክልሎች ለችግር የተጋለጡ ሕፃናትን፣ በድህነት የሚኖሩ ሴቶችንና የተለያዩ ዕገዛና ትኩረት የሚሹ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ሲደግፍ ቆይቷል፡፡
ማኅበሩ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት፣ ሸገር ከተማ አስተዳደር ፉሪ ክፍለ ከተማ ወረዳ 15፣ አኩስታ የካቶሊክ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም አጠገብ፣ ልዩ ፍላጎት ላላቸው ሕፃናት ግራር/አኬዥያ ቪሌጅ መንደር ገንብቶ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡
እንደ ሲስተር አሳየች፣ በአሁኑ ወቅት በማዕከሉ አሥራ ስምንት ሕፃናት የመጠለያ፣ የትምህርት፣ የምግብና የሕክምና አገልግሎት በማግኘት ላይ ናቸው፡፡
ማኅበሩ ዓለም አቀፍ የኦቲዝም ቀንን ምክንያት፣ በማድረግ ሚያዝያ 6 ቀን 2016 ዓ.ም. የግንዛቤ ማስጨበጫና ማኅበሩ ለሚገነባው ጂ+9 ግራር/ኦኬዥያ ቪሌጅ ቁጥር ሁለት ሕንፃ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር አካሂዷል፡፡
ሲስተር አሳየች እንደሚናገሩት፣ ሊገነባ የታሰበው ሕንፃ ልዩ ፍላጎት ላላቸው ሕፃናት የጤና፣ የመመገቢያ፣ የመዋያ ማዕከላት እንዲሁም ትምህርት ቤት፣ ለእናቶች የሙያ ማሠልጠኛና የገቢ ምንጭ ሆነው ሊያገለግሉ የሚችሉ የንግድ ማዕከላትን የሚይዝ ይሆናል፡፡