
ከ 3 ሰአት በፊት
አሜሪካ ለአንድ የእስራኤል የጦር ክፍል የምትሰጠውን እርዳታ ለማቋረጥ ማቀዷን ከተዘገበ በኋላ በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ የሚጣለውን ማንኛውንም ማዕቀብ እንደማይቀበሉ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ገለጹ።
“በሙሉ አቅሜ እታገላለሁ” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
አክሲዮስ የዜና ጣቢያ እንደዘገበው ከሆነ የእስራኤሉ የኔትዛህ ይሁዳ ሻለቃ በዌስት ባንክ በሚፈጽመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምክንያት ዩናይትድ ስቴትስ ማዕቀብ ልትጥልበት አቅዳለች።
በዌስት ባንክ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ክስ ለቀረበበት የእስራኤል መከላከያ ኃይል ክፍሎች የሚሰጠውን ወታደራዊ እርዳታ ሊቋረጥ እንደሚችል ዘገባዎች መውጣታቸውን ተከሎ ስለጉዳዩ የተጠየቁት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን “ውሳኔ ወስኛለሁ፤ በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ ጠብቁ” ብለዋል
ዋነኛ የእስራኤል አጋር የሆነችው ዋሽንግተን ከዚህ በፊት ለእስራኤል ጦር ክፍል የሚሰጥ እርዳታን አቋርጣ አታውቅም።
የእስራኤል ጦር በበኩሉ ኔትዛህ ይሁዳ በዓለም አቀፍ ህግ መሠረት እየተንቀሳቀሰ ነው ብሏል።
“በሻለቃው ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ስለሚገልጹ ዘገባዎች ቢወጡም ጦሩ ስለጉዳዩ አያውቅም። ጦሩ ማንኛውንም ያልተለመደ ክስተት በሕጉ መሠረት መመርመሩን ይቀጥላል” ማለቱን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የእስራኤል የመከላከያ ሚንስትር ዮአቭ ጋላንት በበኩላቸው ዩናይትድ ስቴትስ በኔትዛህ ይሁዳ ላይ ማዕቀብ የመጣል ፍላጎቷን እንድታቆም ጠይቀው ዓለም የሁለቱን አገራት ግንኙነት ከምንጊዜውም በላይ በቅርበት እየተከታተለ ነው ብለዋል።
ጋላንት ባወጡት መግለጫ “አንድን ክፍል ለመተቸት የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ በጦሩ ተግባር ላይ ትልቅ ጥላ ይጥላል። ይህ ለአጋር እና ወዳጅ አገራት ትክክለኛው መንገድ አይደለም” ብለዋል።
- የኢትዮጵያውያን ስደተኞች መዳረሻ የሆነችው ደቡብ አፍሪካ ያቀደችው የኢሚግሬሽን ማሻሻያ ምን ይዟል?ከ 5 ሰአት በፊት
- ፎረስት የተፎካካሪ ቡድን ደጋፊ የሆኑት የቫር ዳኛ ሦስት ፍጹም ቅጣት ምቶች ከለከሉኝ አለከ 4 ሰአት በፊት
- ዛሬ በመላው ዓለም የሚከበረው የምድር ቀን ምንድን ነው? ምንስ ዓላማ አለው?ከ 5 ሰአት በፊት
አክሲዮስ ቅዳሜ ዕለት ጉዳዩን የሚያውቁ ሦስት የአሜሪካ ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ብሊንከን በቀናት ውስጥ በኔትዛህ ይሁዳ ላይ ስለሚጣሉ እርምጃዎች ያሳውቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።
እርምጃው የሚወሰደው በዌስት ባንክ ውስጥ ተፈጽሟል በተባለው የመብት ጥሰት ነው። ፍልስጤማዊ አሜሪካዊው የ80 ዓመቱ ኦማር አሳድ በዌስት ባንክ በተደረገ ፍተሻ በእስራኤላውያን ወታደሮች ከታሰረ በኋላ የሞተበትን አንድ ክስተት ይጨምራልም ተብሏል።
በወቅቱ በጉዳዩ ላይ “የተሟላ የወንጀል ምርመራ እና ሙሉ ተጠያቂነት” እንዲኖር አሜሪካ ጠይቃ ነበር።
የእስራኤል ጦር በአሳድ ሞት መጸጸቱን ገልጾ በዚህ ምክንያትም የኔታህ ይሁዳ አዛዥ “ማስጠንቀቂያ” እንደሚደርሰው አስታውቆ ነበር።
ሁለት ወታደሮች ደግሞ በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ላይ ለሁለት ዓመታት እንዳያገለግሉ እንደሚታገዱ ገልጾ በህግ ግን አይጠየቁም ሲል አክሏል። የአሳድ ሕይወት ያለፈው ቀደም ሲል በነበረባቸው የጤና እክል ምክንያት ነው ብሏል።
መቀመጫቸውን በአሜሪካ ያደረጉት የአሳድ ቤተሰቦች ጉዳዩን በዚሁ ለመዝጋት መወሰኑን ተቃውመዋል።
ሁሉም ጥሰቶች ተፈጽመዋል የተባሉት ሐማስ መስከረም 26 በእስራኤል ላይ ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት ነው።
አሜሪካ ከባድ የሰብአዊ መብት ረገጣ ለተሳተፉ የሌላ አገር የጦር ክፍሎች የገንዘብ ወይም የስልጠና ድጋፍ እንዳይደረግ የሚከለክል ሕግ አላት።
እአአ 1999 የተመሰረተው ኔትዛህ ይሁዳ በአክራሪ ኦርቶዶክሳዊ አይሁዶች የሚያገለግሉበት ልዩ የወንዶች ብቻ ወታደራዊ ክፍል ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በእስራኤላዊው የቀኝ ክንፍ አክቲቪስት ቤን ዛዮን ጎፕስታይን ላይ ማዕቀብ ጥሏል። ድርጅቱ ሌሃቫ “በዌስት ባንክ ተጽዕኖ በሚያሳድር ሁከት ውስጥ ተሰማርቷል” ተብሏል።