የየክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ

ከ 2 ሰአት በፊት

የየክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ የአሜሪካ ተወካዮች ምክር ቤት ለአገራቸው ያጸደቀው የ61 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ ማዕቀፍ በሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት ሊታደግ ይችላል አሉ።

ፕሬዝዳንቱ ከወራት መዘግየት በኋላ የአሜሪካ ምክር ቤት አገራቸው የሩሲያን ወረራ ለመቋቋም የሚያስችላትን እርዳታ በማጸደቁ አመስግነዋል።

የአንድ አገር መጻኢ ዕድል በራሱ በፖለቲከኞች መወሰኑ የተለመደ ቢሆንም እንደ ዩክሬን ግን ቀጣዩ ዕጣ ፈንታ ከአገሪቱ 5 ሺህ ማይልስ ርቆ በሚገኝ የምክር ቤት ድምጽ መወሰኑ ብዙዎችን አስገርሟል።

ዩክሬን በአሜሪካ ምክር ቤት እርዳታው እስኪጸድቅ ድረስ ባሉት ስድስት ወራት ከፍተኛ ዋጋ ከፍላለች።

የአሜሪካ የእርዳታ ማዕቀፍ እስካሁን ይፋ ባይሆንም የአየር መቃወሚያ፣ ረዥም እና መካከለኛ ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤሎች እና ሌሎች ወታደራዊ ትጥቆች ለዩክሬን ሊቀርቡ እንደሚችሉ ተገምቷል።

ባለፉት ወራት ዩክሬን ባጋጠማት የጦር መሳሪያዎች እጥረት ምክንያት በመቶ ኪሎ ሜትሮች የሚቆጠር የግዛቷ አካል በሩሲያ ተይዘውባታል።

የአሜሪካ ወታደዊ ትጥቆች በዩክሬን እጅ ሲገቡ ኪዬቭ የሞስኮን የአየር የበላይነት እንድትቋቋም፣ የጦር ግንባሮችን እንድታጠናክር እንዲሁም የሩሲያን ግስግሴ እንድትገታ እንደሚያግዝ ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ ከደጋፊ አገራት የሚገኘው እያንዳንዱ ሳንቲም አገራቸው ልምታካሂደው የመከላከል ዘመቻ ወሳኝ ነው ሲሉም ተዳምጠዋል።

“እጅግ በጣም ያስፈልገናል። ሁሉም ነገር ያስፈልገናል። እያንዳንዷ ጥይት እያንዳንዷ ሳንቲም እያንዳንዷ መልካም አስተሳሰብ ታስፈልገናለች። ሁሉንም እንፈልገዋለን” ሲሉም አክለዋል።

ዜሌንስኪ ባለፈው ወር ዶኔትስክ ግዛት ባቀኑበት ወቅት ወታደሮች በቂ መሳሪያ እንደሌላቸው መስማታቸውን የተናገሩ ሲሆን፣ የአሁኑ የአሜሪካ ድጋፍ በሩሲያ ቁጥጥር ስር ለመግባት የተቀራቡ አካባቢዎችን ለማትረፍ ያግዛል ብለዋል።

እርዳታው ዩክሬን በፍጥነት ከሩሲያ እጅግ በርካታ ግዛቶቿን እንድትመልስ ባያስችላትም ወደፊት መልሳ ልትይዝበት የምትችለውን ዕድል እንደሚፈጥር ተነግሯል።

ዩክሬን ያለ አሜሪካ እርዳታ በጦርነቶች ልትሸነፍ እንደማትችል ከዋሽንግተን ጋር ከመግባባት ላይ ደርሰዋል።

ፕሬዝዳንቱ “በድጋፉ በጣም ደስተኛ ነኝ። ረዥም ጊዜ በመውሰዱ ቅር ተሰኝቻለሁ። ለማንኛውም ግን ከሚቀር ዘግይቶ መምጣቱ የተሻለ ነው” ብለዋል።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችው ወረራ ሁለት ዓመትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ ዩክሬን ወረራውን እንድትከላል ከምዕራባውያን በኩል በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ወታደራዊ ድጋፍ ሲደረግላት ቆይቷል።