የሞጆ ደረቅ ወደብ

ዜና የሞጆ ደረቅ ወደብ ጥበቃ ሠራተኞች የጦር መሣሪያዎቻቸው ተወስደውባቸው በዱላ እየጠበቁ ነው ተባለ

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: April 21, 2024

የአገሪቱን 90 በመቶ ደረቅ ጭነት የሚያስተናግደው የሞጆ ደረቅ ወደብ የጥበቃ ሠራተኞች፣ በእጃቸው የነበሩ የጦር መሣሪያዎች በመወሰዳቸው በዱላ ጥበቃ እያደረጉ መሆናቸው ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. የ2014/15 ባህር ትራንስፖርትና የየብስ ወደቦች አገልግሎት የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ ውይይት ሲያደርግ ነው፡፡

በደረቅ ወደቡ ለሚሠሩ ጥበቃዎች የጦር መሣሪያዎችና ጥይቶች፣ የመገናኛ ሬዲዮዎች፣ የሰውና የተሽከርካሪ መፈተሻ መሣሪያዎችና የመሳሰሉት እንዲሟሉ አለመደረጉ ጥያቄ ቀርቧል፡፡

ደረጃቸውን የጠበቁ የጥበቃ ማማዎች፣ የግቢ ዙሪያ አጥርና የቅኝት ካሜራዎች በሁሉም የሥጋት ቦታዎች አለመኖራቸውን፣ ካሜራዎች ከመሬት ከፍ ብለው በመስቀላቸው መሬት ላይ ያለውን እንቅስቃሴ በአግባቡ መቅረፅ አለመቻላቸውን፣ የካሜራዎች ቀረፃ መቋረጥ፣ የተቀረፁ ቪዲዮዎች በሥርዓት አለመቀመጥና ሲፈለጉ አውጥቶ መጠቀም አለመቻል የሚሉና የወደቡ በርካታ ችግሮች ተጠቅሰዋል፡፡

የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ምሕረተአብ ተክሉ፣ የጦር መሣሪያዎች አቅርቦት ችግር ሊፈታ አለመቻሉንና በተለይ በአገሪቱ ካለው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ጋር ተያይዞ በየደረጃው ላሉ አካላት ጥያቄ ቢቀርብም መልስ አልተገኘም ብለዋል፡፡ አሳማኝ ምክንያት ቀርቦ ግዥ እስኪፈቀድ ድረስ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የጥበቃ ሠራተኞች የተቋሙን መሣሪያዎች ይጠቀሙ የነበረ ቢሆንም፣ መንግሥት ለምዝገባ ብሎ በመወሰዱና ባለመመለሳቸው በዱላ ብቻ ጥብቃ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

ጉዳይ ከድርጅቱ አቅምና ቁጥጥር በላይ በመሆኑ ጥያቄው ለሚመለከታቸው አካላት ቢቀርብም መልስ ማግኘት እንዳልተቻለ አስረድተዋል፡፡

የሞጆ ደረቅ ወደብ ከመደበኛ የጦር መሣሪያ በተጨማሪ በድሮን መጠበቅ የሚገባው ነው ያሉት አቶ ምሕረተአብ፣ ካሉት የጥበቃ ሠራተኞች በተጨማሪ በአካባቢው የፌዴራል ፖሊስ በመኖሩ ለወደቡ ደኅንነት ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል፡፡

የወደቡን ደኅንነት ለመጠበቅ ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎ ሲሲቲቪ ካሜራ ቢገጠምም፣ አልፎ አልፎ የኤሌክትሪክ ኃይልና ኢንተርኔት በማይኖርበት ጊዜ የአገልግሎት ክፍተት እንደሚፈጠር ገልጸዋል፡፡ አቶ ምሕረተአብ የአንድ ቀን ወይም የግማሽ ሰዓት የኃይል መጥፋት ወይም የኢንተርኔት መቆራረጥ ሲያጋጥም የጥበቃ ሠራተኞችን በማደራጀት የወደቡ ደኅንነት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ቋሚ ኮሚቴው በኦዲት ሪፖርቱ ላይ ባቀረበው ጥያቄ ተቋሙ በመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ከውጭ አገሮች በጂቡቲ ወደብ ወደ አገር ውስጥ የሚያስገባቸውንና የሚያጓጉዛቸው ዕቃዎች፣ የትራንዚት ሒደታቸውን ጠብቀው ወደ መዳረሻ ቦታቸው እንደማይሄዱ ገልጿል፡፡

በአገልግሎት አሰጣጥ ስህተት ምክንያት ዕቃዎች ጂቡቲ ወደብ ከደረሱ በኋላ ዱከም መራገፍ ሲገባቸው ሞጆ፣ ጂቡቲ መራገፍ ሲገባቸው ሞጆ፣ አዲስ አበባ ኤርፖርት ጉምሩክ ቅርንጫፍ መረገፍ ሲገባቸው ቃሊቲ የተራገፍና መሰል ችግሮች መኖራቸውን ቋሚ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡

በሌላ በኩል ከጂቡቲ ወደብ ወደ አገር ውስጥ ደረቅ ወደቦች በኮንቴይነር ዕቃዎችን ለማጓጓዝ ውል የገቡ የትራንስፖርት ማኅበራት፣ በሕገወጥ ንግድና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ መሳተፋቸው በኦዲት መረጋገጡ ተገልጿል፡፡

ለአብነት አንድ የደረቅ ጭነት ማመላለሻ ባለንብረቶች ማኅበር ከሞጆ ደረቅ ወደ ወደ ጂቡቲ ለማጓጓዝ ኮንቴይነሩን ጭኖ የወጣ ቢሆንም፣ ተሽከርካሪው ኮንትሮባንድ ልባሽ ጨርቆችን በኮንቴይነር ጭኖ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዝ አማራ ክልል ውስጥ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተገልጿል፡፡

በተመሳሳይ ከሞጆ ደረቅ ወደብ ወደ ጂቡቲ ለመመለስ የተረከበውን ኮንቴይነር ባዶውን ጭኖ መመለስ ሲገባው፣ የኮንትሮባድ ዕቃ ጭኖ አዲስ አበባ መመለሱን በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

የተቋሙ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሲራጅ አብድላኒ በሰጡት ምላሽ፣ ተቋማቸው በየዓመቱ ቢያንስ እስከ 200 ሺሕ ኮንቴይነሮች እንደሚያጓጉዝና በዚህ መሀል ክፍተቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ለሚፈጠሩ ክፍተቶች ደንበኞች ይቅርታ ተጠይቀው አስፈላጊው ማካካሻ በማድረግ፣ በተቻለ መጠን የመዳረሻ ስህተት እንደገና እንዳይፈጠር ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረጋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በኢትዮ ጂቡቲ ኮሪደር ከ3,000 በላይ ተሽከርካሪዎች እንደሚጓጓዙ የገለጹት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ አልፎ አልፎ ከድርጅቱ ጋር ውል ያሰሩ ትራንስፖርተሮች በሕገወጥ ድርጊት እንደሚሳተፉና በእነዚህ አካላት ላይ ዕርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል፡፡