

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብዩ ተድላ
ዜና ‹‹ራሱን መመገብ ያልቻለ ሕዝብና አገር የሌሎች ተላላኪ ይሆናል›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል…
ቀን: April 21, 2024
- በጀኔቫ በተካሄደ የዕርዳታ ማሰባሰቢያ መድረክ 21 አገሮች ለኢትዮጵያ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል
‹‹ራሱን መመገብ ያልቻለ ሕዝብና አገር፣ የሌሎች ተላላኪ እንጂ፣ የውጭ ግንኙነት ቀርፆ ሊንቀሳቀሰ የሚችልበት ዕድል ጠባብ ነው፤›› ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ተናገሩ፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ነብዩ ተድላ ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ፣ ባለፉት ስድስት ዓመታት በምግብ ራስን በመቻልና በምግብ ሉዓላዊነት በተለይ ከበጋ የስንዴ ምርት አኳያ እጅግ ውጤታማና ዓለም የመሰከረለት ሥራ ለማከናወን ተችሏል ብለዋል፡፡
ይህ አፈጻጸም በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የውጭ ጉዳይ ነፀብራቅ መሆኑን ጠቅሰው፣ አገር ውስጥ ላለው ነባራዊ ሁኔታና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በምግብ ራስን ለመቻል እየተደረገ ለሚገኘው ጥረት ተምሳሌት ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት (FAO) ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ትልቅ የተባለውን አግሪ ኮላ ሜዳሊያ መሸለሙ፣ የዚህ ተግባር ዋና ማረጋገጫ ተደርጎ ይወስዳል ብለዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከኢትዮጵያ ሕዝብ ቢያንስ 21 ሚሊዮን ዜጎች በጦርነት፣ በጎርፍ፣ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በተከሰተ ድርቅና መሰል ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ክስተቶች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልገው ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
የተመድን መረጃ በመጥቀስ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ከእንግሊዝና ከኢትዮጵያ መንግሥታት ጋር በመሆን የዕርዳታ ማሳሰቢያ መድረክ መዘጋጀቱ፣ የምግብ ሉዓላዊነት ከሚለው ጉዳይ ጋር አይጋጭም ወይ በማለት ሪፖርተር ለአቶ ነብዩ ጥያቄ ቢያቀርብላቸውም፣ ‹‹ሁኔታው የሚጋጭ አይደለም›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በስዊዘርላንድ ጀኔቫ ከተማ የተዘጋጀው የዕርዳታ ማሰባሰቢያ መድረክ እ.ኤ.አ. በ2024 ለኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት 3.2 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ፍላጎት ውስጥ አንድ ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት የታሰበ ቢሆንም፣ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ከገቡ 21 አገሮች 630 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱ ይታወሳል፡፡
አቶ ነብዩ ኢትዮጵያ እንደ ታዳጊ አገር የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ አኳያ የጀመረቻቸው ሥራዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ ነገር ግን እነዚህ ሥራዎች ፍፁም ናቸው ማለት እንደማይቻልና ዳር ደርሰው እስኪሟሉ ድረስ የልማት አጋሮች ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በቅርቡ የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) ረዳት ኃላፊ በኢትዮጵያ ጉብኝት ሲያደርጉ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ አንድ የድርጅቱ የሥራ ኃላፊ፣ ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ራሷን መቻል ሳይሆን እጥረት እንዳለበት ጠቁመው የአስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን ተናግረው ነበር፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብዩ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ያነሱት ሌላ ነጥብ ኢትዮጵያ የቀጣናው የስበት ማዕከል መሆኗን ነው፡፡ ባለፉት ስድስት ዓመታት በኢትዮጵያና ኤርትራ ከተደረገው የሰላም ስምምነት ባሻገር በደቡብ ሱዳን፣ በሶማሊያ፣ በአጠቃላይ በአፍሪካ ቀንድ የሰላም አየር እንዲነፍስ አድርጋለች ብለዋል፡፡