
22 ሚያዚያ 2024, 13:02 EAT
የእስራኤል ወታደራዊ ደኅንነት ኃላፊ ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. የፈጸመውን ጥቃት ቀድመው ባለማስቆማቸው ኃላፊነቱን ወስደው ከሥልጣናቸው ለቀቁ።
የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት የባለሥልጣኑን ተተኪ ከተመረጠ በኋላ ሜጀር ጄኔራል አሮን ሃሊቫ ጡረታ እንደሚወጡ አስታውቋል።
የወታደራዊ ደኅንነት ኃላፊው “የተሰጠንን አደራ በአግባቡ አልተወጣንም” ሲሉ በሥራ መልቀቂያ ደብዳቤያቸው አምነዋል።
ሜጀር ጄኔራል አሮን ሃሊቫ በእስራኤል ታሪክ እጅግ አስከፊ በተባለው የሐማስ ጥቃት ምክንያት ከሥልጣን የለቀቁ የመጀመሪያው ከፍተኛ ባለሥልጣን ናቸው።
- እስራኤል እና ኢራን ጦርነት ውስጥ ቢገቡ ምን ይከሰታል? በወታደራዊ አቅምስ ይመጣጠናሉ?20 ሚያዚያ 2024
- በእስራኤል ጥቃት በአንድ ላይ ስለተገደሉት የሐማስ መሪ ልጆች እና የልጅ ልጆች ምን እናውቃለን?14 ሚያዚያ 2024
- ጀርመን ለእስራኤል የጦር መሳሪያ በመሸጥ በጋዛ የዘር ማጥፋት ላይ ተባብራለች የሚል ክስ ቀረበባት9 ሚያዚያ 2024
በመቶዎች የሚቆጠሩ የሐማስ ታጣቂዎች የጋዛን ድንበር ጥሰው ወደ እስራኤል በመግባት እና በአቅራቢያው ባሉ ነዋሪዎች፣ የጦር ሰፈሮች እና የሙዚቃ ፌስቲቫል ታዳሚዎች ላይ ጥቃት ከመሰንዘራቸው በፊት የእስራኤል ወታደራዊ እና የስለላ ባለሥልጣናት በርካታ ማስጠንቀቂያዎችን አልሰሙም ወይም ችላ ብለዋል።
እንደ እስራኤል ከሆነ በጥቃቱ ወደ አንድ ሺህ 200 እስራኤላውያን እና የውጭ ዜጎች ሲገደሉ፣ 253 ደግሞ ታግተው ወደ ጋዛ ተወስደዋል።
እስራኤል ሐማስን ለማጥፋት እና ታጋቾቹን ለማስለቀቅ በማለም በጋዛ ላይ የከፈተችውን ጠንከር ያለ ጦርነት በማካሄድ ምላሽ ሰጥታለች።
በጋዛ ከ34 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን (አብዛኞቹ ህጻናት እና ሴቶች ናቸው) በግጭቱ መሞታቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቋል።
እስራኤል የሐማስን ጥቃት ተከትሎ በምድር እና በአየር ከባድ ወታደራዊ ዘመቻ በጋዛ ሰርጥ ላይ ማካሄድ ከጀመረች ከስድስት ወራት በላይ ተቆጥረዋል።
እስራኤል ለተፈጸመባት ጥቃት ሐማስን ከጋዛ ለማጥፋት እና በእገታ ስር ያሉ ዜጎቿን ማስለቀቅ ዋነኛ ዓላማ አድርጋ ነው ወታደራዊ ዘመቻ እያካሄደች ያለችው።