
22 ሚያዚያ 2024, 15:12 EAT
የጀርመን ባለሥልጣናት ሦስት ለቻይና ሲስልሉ ነበር ብለው የጠረጠሯቸውን ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን ይፋ አደረጉ።
ዋነኛው ተጠርጣሪ ቶማስ አር ለቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የደኅንነት መሥሪያ ቤት በመሰለል ተከሷል።
የጀርመን ዐቃቤ ሕግ እንደሚለው ግለሰቡ ከጀመርን የጥናት እና ምርምር ድርጅቶች ጋር የሚሠራ ኩባንያ አለው።
ተጠርጣሪዎቹ በጣም አስፈላጊ የሚባሉ ምሥጢራዊ መረጃዎችን ሰብሰበዋል፤ በተለይ ደግሞ ለጦር መርከቦች የሚሆን ሞተር ዲዛይን አሳልፈው ለቻይና ሰጥተዋል ተብለው ተከሰዋል።
የጀርመን ዐቃቤ ሕግ፤ ቶማስ አር የተባለው ግሰለብ “ለወታደራዊ ግልጋሎት የሚውሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን” ይዞ ተገኝቷል ሲሉ ይወቅሰዋል።
ተጠርጣሪው ኩባንያውን ተጠቅሞ ሄርዊግ ኤፍ እና ኢና ኤፍ ከተባሉ ከሁለት ግብረ-አብሮቹ ጋር ሳይንስ እና ምርምር ላይ የሚሠሩ ሰዎችን ቀርቧል ተብሏል።
- ዩክሬን እና ሩሲያ ሱዳን ውስጥ በእጅ አዙር ጦርነት እያካሄዱ ነው?22 ሚያዚያ 2024
- ከሦስት ቀናት በፊት በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የተነሳው እሳት እስካሁን አልጠፋም22 ሚያዚያ 2024
- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን ታዳጊዎችን ጨምሮ አራት ሰዎች በታጣቂዎች ተገደሉ22 ሚያዚያ 2024
ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር በዋሉበት ወቅት በአጃቸው ካስገቧቸው ፕሮጀክቶች በተጨማሪ ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን ወስደው ለቻይና ባሕር ኃይል ለመስጠት መኩራ ላይ እንደነበሩ ዐቃቤ ሕግ ይናገራል።
ግለሰቦቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት በምዕራብ ጀርመን ግዛቶች ወስጥ መሆኑ ተዘግቧል።
ሦስቱ ተጠርጣሪዎች በአውሮፓ ኅብረት ጥቅም ላይ እንዳይውል የተከለከውን የጨረር ቴክኖሎጂን ወደ ቻይና በማጓጓዝም ተከሰዋል።
የአውሮፓ ኅብረት ሕግ ለወታደራዊ እና ሌሎች ሰላማዊ ግልጋሎቶች ጥቅም ላይ የሚውሉ አንዳንድ ቁሳቁሶችን ወደ ውጭ አገራት መላክ ይከለክላል።
የጀርመን የአገር ውስጥ ሚኒስትር ናንሲ ፊዘር የተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር መዋል “ለደኅንነት ዘርፉ” ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።
“በተለይ ለወታደራዊ አገልግሎት የሚውሉ የጀርመን ቴክኖሎጂዎች እጅግ በጣም ጥብቅ መረጃዎች ናቸው” ይላሉ ሚኒስትሯ።
ከአንድ ሳምንት በፊት የጀርመን መራሄ-መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ወደ ቤጂንግ ለኦፊሴላዊ ጉብኝት አቅንተው ነበር። መሪው ቻይና ለሩሲያ የምታደርገውን ድጋፍ የተመለከተ ንግግር በቤይጂንግ አሰምተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በጀመርኗ ባቫሪያ ግዛት ለዩክሬን ድጋፍ የሚውሉ የወታደራዊ ቁሳቁሶችን ጉዞ ሊያደናቅፉ ነበር የተባሉ ሁለት ተጠርጣሪዎች ከቀናት በፊት በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወሳል።
ሁለቱ ግለሰቦች የጀርመን እና ሩሲያ ጥምር ዜግነት ያላቸው ናቸው የተባለ ሲሆን፣ ለሩሲያ በመሰለል ተጠርጥረው ነው በቁጥጥር ሥር የዋሉት።