
22 ሚያዚያ 2024, 15:01 EAT
በአማራ ክልል፣ ሰሜን ጎንደር ዞን ውስጥ በሚገኘው የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከሦስት ቀናት በፊት [ሚያዚያ 10፣ 2016 ዓ.ም.] የተነሳው እሳት በቁጥጥር ሥር አለማዋሉን የክልሉ ባለሥልጣን ገለጹ።
የክልሉ የባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ የሆኑት አባይ መንግሥቴ ለቢቢሲ እንደተናገሩት እሳቱ ከተነሳበት ቀን ጀምሮ የአካባቢው ማኅበረሰብ እና አመራሮች ለማጥፋት ጥረት ቢያደርጉም እሳቱን መቆጣጠር አልተቻለም።
“የቦታው አቀማመጥ አስቸጋሪ በመሆኑ ጠፋ ሲባል እንደገና እየተነሳ በቁጥጥር ሥር ማዋል አልተቻለም” ብለዋል ኃላፊው።
ሆኖም እሳቱ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይስፋፋ የአሰሳ እና የጥበቃ ሥራ እየተሠራ ነው ያሉት ኃላፊው፣ እሳቱ ከቁጥጥር ውጪ አለመውጣቱን ተናግረዋል።
በፓርኩ የእሳት አደጋ ሲከሰት ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።
ከአምስት ዓመታት በፊት በፓርኩ ከፍተኛ እሳት ተነስቶ ከክልሉ እና ከፌደራል አቅም በላይ ሆኖ የእስራኤል እና የኬንያ እሳት ማጥፊያ ሄሊኮፕተርን ድጋፍ እስከ መጠየቅ ተደርሶ ነበር።
- እሳቱን ለማጥፋት ከኬኒያ መንግሥት ሄሊኮፕተር ተጠየቀ11 ሚያዚያ 2019
- በሰሜን ተራሮች ፓርክ በሄሊኮፕተር ውሃ እየተረጨ ነው15 ሚያዚያ 2019
- የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከቃጠሎው በኋላ18 ሚያዚያ 2019

በርካታ ብርቅዬ እንስሳት፣ አዕዋፋት እና እፅዋት በሚገኙበት ፓርኩ ውስጥ በተደጋጋሚ እሳት የሚነሳበት ትክክለኛ መንስኤ ምን እንደሆነ አልተደረሰበትም።
ነገር ግን በአካባቢው እንስሳቶቻቸውን ለግጦሽ የሚያሰማሩ ማኅበረሰቦች ፓርኩን በባለቤትነት እንዲጠብቁ ለማድረግ የሚሰራው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ የተዳከመ በመሆኑ፣ እንዲሁም በፓርኩ አካባቢ የነበሩ ማኅበረሰቦች ወደ ሌላ ቦታ እንዲሰፍሩ ከተደረገ በኋላ ቃል የተገባላቸው ማቋቋሚያ አለመፈፀሙ የፈጠረው ቁጣ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ኃላፊው ግምታቸውን ተናግረዋል።
እንደ አቶ አባይ ከሆነ ከፓርኩ አካባቢ ተነስተው አምባራስ የሚባል አካባቢ ላይ ሰፍረው የነበሩ ከ100 በላይ አባወራዎችን በኢኮኖሚ ለማቋቋም የሚውል ወደ 60 ሚሊየን ብር ለማሰባሰብ ከአራት ዓመታት በፊት ቃል ተገብቶ የነበረ ቢሆንም፣ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ይህን ገንዘብ መሰብሰብ ባለመቻሉ ተፈፃሚ ሳይሆን ቀርቷል።
“ይህ ባለመሆኑም በማኅበረሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ጥያቄ እና ቅሬታን ፈጥሯል። በተደጋጋሚ በፓርኩ የሚነሳውን እሳትም በዘላቂነት ለመቆጣጠር አንዱ እንቅፋት ሆኗል” ብለዋል።
ነዋሪዎች ኑሯቸውን ለመደጎም ወደ ፓርኩ በመግባት ከሰል በማክሰል እና ንብ በማነብ ሥራ የተሰማሩ ግለሰቦች የሚያያይዙት እሳት ለፓርኩ መቃጠል እንደ አንድ ምክንያትም ይጠቀሳል።
ከዚህም በተጨማሪ “የአካባቢውን ማኅበረሰብ እረፍት ለመንሳት የሚሠራ ሥራ ሊኖር ይችላል” ሲሉም ጠቁመዋል።
አሁን ላይ የተነሳውን እሳት መንስኤ ለማወቅ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑንም ኃላፊው ገልጸዋል።
በፓርኩ ከሦስት ቀናት በፊት የተነሳው እሳት ምን ያህል ቦታን እንዳወደመ እና ምን ያህል ጉዳት እንዳደረሰ እስካሁን አልታወቀም።
ነገር ግን እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ በአካባቢው በሚገኘው ጓሳ የተባለ ሳር እና ‘ውጭና’ የተባለ አገር በቀል እፅዋት ላይ መጠኑ ያልታወቀ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን፣ በዱር እንስሳት ላይ የደረሰ ጉዳት ግን የለም።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1978 በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት በተመዘገበው የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ዋልያን እና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ በርካታ ብርቅዬ እንስሳቶች ይገኛሉ።