
22 ሚያዚያ 2024, 13:34 EAT
መስከረም 2016 ዓ.ም. ላይ በማይገመት ቦታ፣ ጨርሶ ሊገመቱ በማይችሉ ሁለት መሪዎች መካከል ስብሰባ ተደረገ።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ ከሱዳኑ መሪ ጄኔራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን ጋር በአየርላንድ በሚገኝ አየር ማረፊያ መገናኘታቸው ብዙዎችን አስደንቆ ነበር።
ይህን የሁለቱን መሪዎች ውይይት በዩክሬን ጦር ውስጥ ያሉ የልዩ ኃይል አባላት እንዳመቻቹት ተገልጿል።
ዜሌንስኪ በኒው ዮርክ የመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተሳትፈው ወደ ዩክሬን እየተመለሱ ሳለ አውሮፕላናቸው በአየርላንድ ሻነን አየር ማረፊያ ነዳጅ ለመሙላት በቆመበት ወቅት ነበር ከሱዳኑ መሪ ጋር የተገናኙት።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ሁለቱ መሪዎች የተገናኙበት አጋጣሚ “ቀድሞ የታቀደ አልነበረም” ባለበት ወይይት፤ ዜሌንስኪ እና አል ብሩሃን “በሩሲያ የሚደገፉ ሕገ-ወጥ ቡድኖች የፈጠሩት ስጋት” ላይ ተነጋግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የሱዳን ጦር አዛዥ ጄኔራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሹ ኃይል መሪ ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሔምቲ) ጦር ተማዘው ሱዳን በእርስ በእርስ ጦርነት እየታመሰች ትገኛለች።
በሁለቱ የጦር መሪዎች መካከል የተፈጠረው የሥልጣን ሽሚያ በሺዎች የሚቆጠሩ የአገሪቱን ዜጎች ሕይወት ከመቅጠፉም በላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩትን አፈናቅሎ የሱዳንን መሠረተ ልማት አውድሟል።
ሁለቱን የጦር ጀነራሎች በተለያየ ጽንፍ የተሰለፉ መንግሥታት በድብቅ እንደሚደግፉ ሲገለጽ ቆይቷል።

በሩሲያ ወረራ የተፈጸመባት ዩክሬን ለአል-ቡሩሃን ጦር ድጋፍ የማድረጓ ዜና እየተሰማ ነው።
ዎል ስትሪት ጆርናል በቅርቡ ባወጣው ዘገባ ላይ ነሐሴ 2015 ዓ.ም. ካርቱም የሚገኘው የአል-ቡሩሃን ዋና መሥሪያ ቤት በዳጋሎ ጦር በተከበበ ወቅት ጄኔራሉን ያስመለጡት የዩክሬን ወታደሮች ናቸው ብሏል።
ዎል ስትሪት የዳጋሎ ጦር ካርቱም የሚገኘውን የአገሪቱን ጦር ዋና መሥሪያ ቤት ከመክበቡ ቀደም ብሎ አል-ቡሩሃን እና ዜሌንስኪ በስልክ ንግግር ካደረጉ በኋላ “ቲሙር” በሚል ስያሜው በሚታወቀው የደኅንነት መኮንን የተመሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዩክሬናውያን ወታደሮች ሱዳን መግባታቸውን ዘግቧል።
እንደ ዘገባው ከሆነ የዩክሬን ጦር አል-ቡሩሃንን ከከበባ ከማስወጣቱ በተጨማሪ ለአገሪቱ ጦር የቅኝት ሥራ የሚሠሩ ድሮኖችን (ሰው አልባ አውሮፕላኖችን) በማቅረብ እና በፍጥኖ ደራሹ ኃይል ላይ ድንተኛ የምሽት ጥቃት በመፈጸም የጦርነቱን አካሄድ መቀየር ችለዋል።
ዩክሬን በሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ስላላት ተሳትፎ ከቢቢሲ ለቀረበ ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ ሳትሰጥ ቀርታለች።
“የዩክሬንን ብሔራዊ ፍላጎት ማስጠበቅ አስፈላጊ ሆኖ በተገኘበት በየትኛውም የዓለም ክፍል ተቋሙ (የአገሪቱ የደኅንነት) አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳል” ሲል ከቢቢሲ ለቀረበ ጥያቄ ምላሽ ሰጥቷል።
- ሩሲያን አሸብሮ የነበረው የቫግነር ቡድን ማን ነው? መሪውስ?24 ነሐሴ 2023
- ረሃብ ባንዣበበባት ሱዳን ከጦርነቱ ከሚሸሹ ሰዎች የሚሰሙ የግድያ እና የመደፈር ታሪኮች21 ሚያዚያ 2024
- የተረሳው ግጭት እና ከአስከፊ የረሃብ ቀውስ አፋፍ ላይ የምትገኘው ሱዳን14 ሚያዚያ 2024
ሩሲያ እና ዩክሬን በሱዳን
ከሁለት ወራት በፊት ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የወጣ ተንቀሳቃሽ ምሥል የዩክሬን ወታደሮች ሱዳን ውስጥ እንዳሉ አሳይቶ ነበር።
በዚህ ቪዲዮ ላይ የዩክሬን ወታደሮች የሩሲያዊ ወታደር አስክሬንን የጫነ ብረት ለበስ ተሸከርካሪ ሲፈትሹ ያሳያል።
ይህ ተሸከርካሪ ከሩሲያዊው ወታደር አስክሬን በተጨማሪ የቫግነር ቅጥረኛ ቡድን ተዋጊዎችን ጭኖ ነበር።
በሌላ የዚህ ቪዲዮ ክፍል ላይ የዩክሬን ወታደሮች በተሽከርካሪው ላይ ያሉ ሩሲያውያን ተዋጊዎችን በጥያቄ ሲያፋጥጡ ይታያሉ።
“እዚህ ዓላማችሁ ምንድን ነው?” ሲል ዩክሬናዊው ወታደር ሲጠይቅ ይታያል።
ሩሲያዊው ደግሞ “የአገሪቱን መንግሥት መጣል” ሲል ይደመጣል።
ቢቢሲ የዚህን ቪዲዮ ትክክለኛነት ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ እንዲሁም ተንቀሳቃሽ ምስሉ የት እና መቼ እንደተቀረጸ ማወቅም አልተቻለም።

ይሁን እንጂ የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቫግነር በሱዳን መንቀሳቀስ ከጀመረ ሰነባብቷል። ይህ ቡድን በአገሪቱ ጦር እና በፍጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል ጦርነት ከመቀስቀሱ ቀደም ብሎ በሱዳን ነበር።
በወቅቱ የቫርግነር ወታደሮች የሱዳን ወታደሮችን በማሠልጠን እና መንግሥት ላይ የአደባባይ የተቃውሞ ሰልፎችን በአጭሩ እንዲጩ ሲያስተባብሩ ነበር።
ቫግነር ከሱዳን በተጨማሪ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ይንቀሳቀሳል። የመሪው የቭጌኒ ፕሪጎዢን ሞትን ተከትሎ በአፍሪካ የሚንቀሳቀሱ የቫግነር አባላት በሩሲያ ልዩ አገልግሎት ስር መተዳደር ጀምረዋል።
በሱዳን የሚገኙ የዩክሬን ወታደሮች ዋነኛ ዓላማ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን እየረዱ ያሉ የቫግነር ኃይሎችን ዒላማ ማድረግ ሊሆን እንደሚችል የቢቢሲ ሞኒተሪንግ ተንታኝ ቤቨርሊ ኦቺዬንግ ትገልጻለች።
“እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ዩክሬናውያኑ የአገሪቱ መንግሥት ከፈጥኖ ደራሹ ጋር ለገባው ጦርነት ድጋፍ ከማድረግ ይልቅ ትኩረት እያደረጉ ያሉት በሱዳን ባሉ ሩሲያውያን ላይ ነው” በማለት ኦቺዬንግ ትናገራለች።
የቫግነር ቡድን የዩክሬንን ጨምሮ በተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይከሳሳል።
ይህ ቡድን ከአፍሪካ በተጨማሪ ከሩሲያ ጎን ተሰልፎ ዩክሬንን ሲወጋም ቆይቷል።
የዩክሬን ወታደሮች በሱዳን የተገኙበት ሌላኛው ምክንያት የቅጥረኛ ቡድኑ የገንዘብ ምንጭን ለማድረቅ ሊሆን እንደሚችል መቀመጫውን ለንደን ያደረገው ሪማርክስ ኦን ፖለቲካል ቫዮለንስ የተባለው ተቋም ባልደረባ የሆኑት ሙራድ ባታለ ሺሻኒ ናቸው።
“ሔሜቲ (የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ) በአፍሪካ ትልቁ የሩሲያው ቫግነር ቡድን አጋር ናቸው። የቫግነር ዋነኛ የገቢ ምንጭ የሆነውን የሱዳንን ወርቅ የሚቆጣጠረው ሔሜቲ ነው” ይላሉ።
እአአ 2022 ላይ ሲኤንኤን ባወጣው ዘገባ ሩሲያ በሱዳን በወርቅ ሽያጭ እና በወርቅ ማውጣት ተሳትፋ እንደምትገኝ እና በወርቅ የተሞሉ 16 አውሮፕላኖች ከሱዳን ወደ ሶሪያ መላኳን ዘግቦ ነበር።
በሱዳን ያሉ የዩክሬን ወታደሮች በአገሪቱ ያለውን የሩሲያ የወርቅ ንግድ ዒላማ የማድረግ ዕቅድ መኖሩን የዩክሬን የደኅንነት ተቋም ለዎልስትሪት ጆርናል ተናግረዋል።
“የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው”
አንዳንድ ተንታኞች በሱዳን ያለውን ሁኔታ ‘የእጅ አዙር ጦርነት’ ጥሩ ምሳሌ ነው ይላሉ። ዩክሬን እና ሩሲያ በሦስተኛ አገር ያላቸውን ፍላጎት ለማሳካት በሁለት ጽንፍ ሆነው እየተዋጉ ያሉ ሁለት ቡድኖችን እየደገፉ ይገኛሉ።
“ሔምቲ በዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ እና በሩሲያ ይደጋፋል። አል-ቡርሃን ደግሞ በሳዑዲ አረቢያ ገንዘብ እና በዩክሬን ድጋፍ የሔምቲን የጦር እንቅስቃሴ እያስቆመ ይገኛል” በማለት የሚነገሩት ደግሞ የጄምሰንታውን ፋውንዴሽን የቀድሞ ኃላፊ ግሊን ሃዋርድ ናቸው።
እኒህ ተንታኝ የዜሌንስኪ እና የአል-ቡረሃን ግንኙነት የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው በሚል መርኅ ላይ የተመሠረተ ነው ይላሉ።
“ይህ ዩክሬን በየትኛውም የዓለም ክፍል፣ በየትኛውም ሰዓት ፑቲንን ልትገዳደር እንደምትችል ለዓለም አቀፍ ማኅብረሰቡ የምታሳይበት ዕድል ይሆንላታል።”
ይሁን እንጂ በሩሲያ ጦርነት ጭንቅ ውስጥ የምትገኘው ዩክሬን የአፍሪካዊቷን አገር የጦር ጄኔራል ልትረዳ የምትችለው አነስተኛ ቁጥር ባላቸው የልዩ ኃይል አባላት ብቻ ነው።
በተቃራኒው ሩሲያ በሱዳን የቆየ መሠረት ጥላለች።
ቫግነር ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በሻለቃ በተደራጀ ቡድን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።