አትሌት ዘርፌ ወንድማገኝ
የምስሉ መግለጫ,አትሌት ዘርፌ ወንድማገኝ ሁለት የተከለከሉ መድኃኒቶች ወስዳለች ተብላ ነው የተከሰሰችው

22 ሚያዚያ 2024, 15:51 EAT

ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ዘርፌ ወንድማገኝ የተከለከሉ አበረታች መድኃኒቶችን ወስዳ በመገኘቷ ለአምስት ዓመታት ከአትሌቲክስ መታገዷ ተገለጠ።

የ21 ዓመቷ የመካከለኛ ርቀት አትሌት ለአምስት ዓመታት መታገዷን የገለጠው አትሌቲክስ ኢንቴግሪቲ ዩኒት የተባለው ተቋም ነው።

ተቋሙ በቀድሞው ትዊተር በአሁኑ ኤክስ ሰሌዳው ላይ በለጠፈው መግለጫ አትሌቷ ምርመራ ከተደረገላት በኋላ ቅጣት ማስተላለፉን አሳውቋል።

የዓለም አትሌቲክስ አካል የሆነው ይህ ተቋም ባወጣው መግለጫ፣ አትሌቷ ሁለት የተከለከሉ ንጥረ-ነገሮችን መውሰዷን አምናለች ብሏል።

ዘርፌ፤ ቴስቶስቴሮን የተባለውን እና ኢፒኦ የተሰኘውን አትሌቶች በደማቸው ውስጥ የበለጠ ኦክሲጅን እንዲኖር የሚያደርግ ንጥረ ነገር መውሰዷን አምናለች።

ዘርፌ በቶኪዮ ኦሊምፒክስ በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ስምንተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ ይታወሳል።

ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት 2023 በቡዳፔሽት በተደረገው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ደግሞ አራተኛ ወጥታለች።

አትሌቷ ሦስት ጊዜ ምርመራ የተደረገላት ሲሆን፣ ሁለቱ የተደረጉላት ሀንጋሪ ሳለች መሆኑን እና ያስመዘገበችው ውጤትም ከውድድሩ መሰረዙን አሶሺየትድ ፕሬስ (ኤፒ) የዜና ወኪል ዘግቧል።

የዜና ወኪሉ አክሎ እንደዘገባው አትሌቲክስ ኢንቴግሪቲ ዪኒቲ (ኤአይዩ) የተባለው ዓለም አቀፉ ተቋም ከዶክተር በደረሰው መረጃ መሠረት አትሌቷ ለአኒሚያ እና ለኩላሊት ቁስለት በሚል ኢፒኦ የተባለው ንጥረ ነገር ተሰጥቷታል።

ኤአይዩ ጨምሮ እንደገለጠው ይህን የሚያረጋግጥ የተፈረመበት ደብዳቤ ባለፈው ሳምንት ከአትሌቷ ደርሶታል።

ተቋሙ በድረ-ገፁ ባወጣው መግለጫ አትሌቷ ለሦስተኛ ጊዜ የተመረመረችው ኢትዮጵያ ውስጥ ለገጣፎ መሆኑን አሳውቋል።

የተቋሙ መግለጫ አክሎ እንዳመለከተው አትሌቷ የተከለከ አበረታች መድኃኒት ደሟ ውስጥ ተገኝቷል በሚል ተጠርጥራ የተከሰሰችው ባለፈው ኅዳር እንደሆነ ገልጧል።

ዋዳ የተሰኘው ዓለም አቀፉ የፀረ-አበረታች መድኃኒት ተቋም በ2023 ባወጣው ዝርዝር መሠረት አትሌቷ የወሰደችው ንጥረ-ነገር ሕግን የሚጥስ መሆኑ ተዘግቧል።

የኤአይዩ መግለጫ እንደሚያትተው አትሌቷ ውሳኔውን በመቃወም ይግባኝ የምትጠይቅ ከሆነ መብቷ ይከበርላታል።

በ2019 የዓለም ሻምፒዮና በ16 ዓመቷ ኢትዮጵያን ወክላ የተወዳደረችው ዘርፌ ወንድማገኝ በ3000 ሜትር መሰናክል ተስፋ ከተጣልባቸው አትሌቶች አንዷ ናት ይላል የዓለም አትሌቲክስ በ2021 ያወጣው ዘገባ።

ዘርፌ በአፍሪካ ሻምፒዮና እና በዓለም ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ላይ ተሳትፋ የብር ሜዳሊያዎች ማግኘት ችላለች።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ አስተዳዳሪ አካል አበረታች መድኃኒት የሚወስዱ አትሌቶች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እያደረገ ነው።