አማሮ ዞን

22 ሚያዚያ 2024, 13:46 EAT

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን፤ “ከምዕራብ ጉጂ ዞን መጥተዋል” የተባሉ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ሦስት ታዳጊ ልጆችን ጨምሮ አራት ሰዎች መገደላቸውን ጥቃቱ የተፈጸመበት ቆቦ ቀበሌ ሊቀመንበር እና ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

የኮሬ ዞን አስተዳደር ባወጣው መግለጫ “ለንጹሐን አርሶ አደሮች” ሞት ምክንያት ለሆነው ጥቃት “በምዕራብ ጉጂ ዞን ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ እና ፀረ-ሰላም” ሲል የጠራቸውን አካላት ተጠያቂ አድርጓል።

ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መመሥረት አስቀድሞ “አማሮ ልዩ ወረዳ” በሚል ሲጠራ በነበረው የአሁኑ ኮሬ ዞን፣ ጎርካ ወረዳ፣ ቆቦ ቀበሌ አራት ሰዎች የተገደሉበት ጥቃት የተፈጸመው፤ ትናንት እሁድ ሚያዝያ 13/2016 ዓ.ም. መሆኑን የቆቦ ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ መንግሥቱ መኩሪያ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከቀኑ አምስት ሰዓት ገደማ ጥቃት የተፈጸመባቸው ነዋሪዎች ከ100 በላይ ከብቶችን ለግጦሽ ለማሰማራት እየተጓዙ እንደነበር የቀበሌው አስተዳዳሪ እና ሁለት ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ጥቃት ከደረሰባቸው ነዋሪዎች መካከል አንድ የ14 ዓመት ታዳጊ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ አጋፋሪ መንገሻ የተባሉት የቀበሌው ነዋሪ፤ ሁለቱ ደግሞ እድሜያቸው ከ17 እስከ 19 ባለው ውስጥ እንደሚገመትም ገልፀዋል። ምስጋናው ታምራት የተባሉ ሌላ የቀበሌው ነዋሪ ከተገደሉት ሰዎች ውስጥ ታዳጊዎች እንደሚገኙበት ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

አቶ አጋፋሪ፤ “እነሱ [ታጣቂዎቹ] ቀደም ብለው ማታ ላይ ገብተው ቦታ ይዘው ነበር። ሰባት ክላሽ የታጠቁ [ሰዎች] ናቸው የመጡት። ሟቾቹ ከብት ሊያግዱ ይዘው እየሄዱ እያለ፤ ከብት የሚታገድበት ቆላ የሚባል ቦታ [ሲደርሱ] እዚያ ጋር ነው ተኩስ የጀመሩት” ሲሉ ጥቃቱ የተፈጸመበትን ሁኔታ ገልጸዋል።

ታጣቂዎቹ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ አራቱ ታዳጊዎች እያገዱ የነበሯቸውን ከብቶች ለመውሰድ ቢሞክሩም ተኩሱን ሰምተው በመጡ የአካባቢው ነዋሪዎች እንዲመለስ መደረጉን ነዋሪዎቹ አስረድተዋል።

የትናንቱን ጥቃት የፈጸሙት ዞኑን ከሚያዋስነው የኦሮሚያ ክልሉ ምዕራብ ጉጂ ዞን የመጡ ታጣቂዎች እንደሆኑ የቀበሌው ሊቀመንበር አቶ መንግሥቱ እና ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

የኮሬ ዞን አስተዳደር በተመሳሳይ ትናንት ምሽት ባወጣው የሐዘን መግለጫ፤ “በምዕራብ ጉጂ ዞን ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛው እና ፀረ-ሰላም ኃይሎች” አርሶ አደሮች ላይ ግድያ መፈጸማቸውን አስታውቋል።

የኮሬ ሕዝብ በሚያዝያ ወር ብቻ “ብዙ ሞቶችን” ማስተናገዱን የጠቀሰው መግለጫው፤ “በምዕራብ ጉጂ ዞን በገላና እና በሱሮ ባርጉዳ ወረዳዎች፤ ኮሬ ዞን አዋሳኝ ቀበሌያት ውስጥ ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ፅንፈኛው እና ፀረ-ሰላም ኃይል መኖሩ በቀጠናው ለሚከሰት ሞት እና ንብረት ዝርፊያ ምክንያት ሆኖ እየተጠቀሰ ይገኛል” ብሏል።

በእስካሁኑ ጥቃቶች ዞኑ ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉ በመግለጫው ላይ አልጠቀሰም። ቢቢሲ ያነገጋራቸው ነዋሪዎች ከመጋቢት ወር ጀምሮ ቢያንስ አራት ጊዜ በተፈጸሙ ጥቃቶች ነዋሪዎች መገደላቸውን ገልጸዋል።

የኮሬ ዞን አስተዳደር፤ ታጣቂዎች መጥተዋል ከተባለበት ምዕራብ ጉጂ ዞን እንዲሁም “ከሌሎች ፌዴራል እና ክልል መንግሥታት እና ከፀጥታ መዋቅሮች” ጋር በመነጋጋር፤ “ጽንፈኛውን እና ሀሳቡን በመጋራት ነፍስ የሚያጠፉ፣ ንብረት የሚዘርፉ አጥፊዎች ተለይተው በሕግ የሚጠየቁበት” ሥራ እንደሚያከናውንም ገልጿል።

የኮሬ እና የአጎራባቹ የምዕራብ ጉጂ ዞን አካባቢዎች ከ2009 እስከ 2015 ዓ.ም. ተደጋጋሚ ግጭቶችን ሲያስተናግዱ ቆይተዋል። ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር የአገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት እርቅ ተፈጽሞ ነበር። ከዚሁ እርቅ በኋላ የሚታዩ ግጭቶች መርገባቸውን የቀበሌዋ ነዋሪዎች ገልጸዋል።