ስደተኞች በጀልባ ወደዩኬ ይገባሉ
የምስሉ መግለጫ,ስደተኞች በጀልባ ወደዩኬ ይገባሉ

ከ 7 ሰአት በፊት

በዩናይትድ ኪንግደም ፓርላማ ላለፉት ወራት እጅግ ሲያወዛግብ የነበረው ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ ዕቅድ ህግ ሆኖ ሊወጣ ነው።

የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሽ ሱናክ የነደፉት ይህ ዕቅድ የተወሰኑ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ከዩናይትድ ኪንግድም ወደ ሩዋንዳ የሚያሸጋግር ነው።

ስደተኞቹ የጥገኝነት ጥያቄያቸው እስከሚጠናቀቅ በሩዋንዳ ይቆያሉ።

ታዲያ የዚህ ዕቅድ ተቃዋሚዎች ሲያቀረቡት የነበረው ዋነኛ መከራከሪያ ሩዋንዳ ለስደተኞች ደህንነት እና ጥበቃ የተመቸች አይደለችም የሚል ነው።

ይህ ዕቅድ በከፍተኛ ተቃውሞ ቢታጀብም ትላንት ዕኩለ ሌሊት ከመሆኖ አስቀድሞ የምክር ቤቱ አባላት ህግ ሆኖ እንዲወጣ ይሁንታቸውን ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሽ ሱናክ ስደተኞችን የያዙ አውሮፕላኖች ከ10 እስከ 12 ሳምንታት ባለው ጊዜ መብረር እንደሚጀምሩ ገልጸዋል

ሆኖም ፍርድ ቤቶች በሚሰጡት ትእዛዝ ወይም ዕቅዱን ለስደተኞች አስተማማኝ ለማድረግ በሚከናወኑ ስራዎች ምክንያት በረራዎች ከዚህም ጊዜ በላይ ሊዘገዩ ይችላሉ።

የዩኬ ሀገር ውስጥ ጉዳይ መስሪያ ቤት ኃላፊ ጄምስ ክሌቨርሊይ ይህ መጽደቁ ስደተኞች ወደ ዩኬ ባህር አቋርጠው እንዳይገቡ ወሳኝ እርምጃ ነው ብለዋል።

ሆኖም ትይዩ የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር የሆኑት ዩቬት ከፐር ውሳኔውን ክፉኛ ተቃውመውታል።

ይህ ዕቅድ ወደ ጠረጴዛ ከመጣ ከአንድ ዓመት በላይ አስቆጥሯል። ይሁን እንጂ የዩኬ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዕቅዱ ከህግ አግባብ ውጪ ነው ሲል ውድቅ አድርጎት ነበር።

ትላንት ሰኞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሱናክ በረራዎች ተዘጋጅተው እንደነበር ገልጸዋል። በነዚህ በረራዎች ከ500 በላይ ሰራተኞች ስደተኞችን እስከሩዋንዳ ለመሸኘት ዝግጅት ሲያደርጉ እንደነበር ተነስተዋል።

አሁን ህግ ሀኖ ከወጣ በኋላ በወር ውስጥ በርካታ በረራዎች ወደ ሩዋንዳ እንደሚደረጉ ገልጸዋል። “ምክንያቱም ጀልባዎችን ለማስቀረት ስልታዊው መንገድ ይህ ነው” ብለዋል።

በዚህ ዕቅድ ላይ በምክር ቤቱ የነበረው ውይይት ሰዓታትን የወሰደ ነበር። ከዚያም አልፎ የምክር ቤት አባላቱ ዕቅዱ አስት ጊዜ ቀርቦላቸዋል።

ይህ ክርክር እየተካሄደ ቆይቶ እኩለ ለሊት ሲቃረብ አባላቱ ከስምምነት ደርሰዋል።

ይህንን ዕቅድ ለማጽደቅ በርካታ ውጣ ውረዶች ወስጥ ያለፉት ሱናክ ምክር ቤት ከዚህ ውሳኔ ላይ መድረሱ እንደ ትልቅ ፖለቲካዊ ድል ተቆጥሮላቸዋል።

በአሁኑ ወቅት በዩኬ ጠቅላላ ምርጫ እየደረሰ በመሆኑ ይህ የሱናክ ዕቅድ የት ድረስ እንደሚሄድ ግን አልተረጋገጠም።