ሂው ኤድዋርድስ

ከ 6 ሰአት በፊት

ከአንድ ታዳጊ ወሲባዊ ይዘት ያለው ፎቶግራፍ እንዲላክለት ገንዘብ ከፍሏል በሚል መወዛገቢያ ሆኖ የነበረው ታዋቂው የቢቢሲ ጋዜጠኛ ሂው ኤድዋርድስ ከሥራ ለቀቀ።

ሂው ኤድዋርድስ “በህክምና ምክር” ምክንያት ከቢቢሲ እንደለቀቀ ተቋሙ አስታውቋል።

ጋዜጠኛው ማንነት እና ፆታ ከልተገለጸ ታዳጊ ወሲባዊ ይዘት ያላቸው ፎቶዎች እንዲላክለት ገንዘብ ከፍሏል የሚል ክስ ሐምሌ ወር ከቀረበበት በኋላ በሥራ ላይ አልነበረም።

ሂው ኤድዋርድስ ቢቢሲ ካሉት ስመ ጥር የቴሌቪዥን አቅራቢዎች መካከል አንዱ ሲሆን፣ የአገሪቱን ታላላቅ ብሔራዊ ዝግጅቶችንም ለመዘገብ ከሚመረጡት አንዱ ነው።

“ሂው ኤድዋርድስ ከሥራ ለቋል እንዲሁም ቢቢሲንም ተሰናብቷል” የሚል አጭር መግለጫ ሰኞ ዕለት ወጥቷል።

“ከ40 ዓመታት አገልግሎት በኋላ የህክምና ባለሙያዎች በሰጡት ምክር ላይ በመመሥረት ሥራውን ለመልቀቅ መወሰኑን ገልጿል” ይላል።

“ቢቢሲ መልቀቂያውን የተቀበለ ሲሆን፤ ከዚህ በላይ አስተያየት መስጠት ተገቢ እንዳልሆነ እናምናለን” ብሏል የቢቢሲ መግለጫ።

ወሲባዊ ይዘት ላላቸው ፎቶዎች መክፈሉ ይፋ መሆኑን ተከትሎ “በከባድ የአዕምሮ ጤና ጉዳዮች” ምክንያት ሆስፒታል መግባቱን ባለቤቱ ከተናገረች ከዘጠኝ ወራት በኋላ ነው ጋዜጠኛው ከሥራ መልቀቁ የተሰማው።

ፖሊስ በበኩሉ ወንጀል ስለመፈጸሙ ማስረጃ ባለማግኘቱ በ61 ዓመቱ ጋዜጠኛ ላይ ምንም ዓይነት እርምጃ እንደማይወስድ አስታውቋል።

የቢቢሲ የቴሌቪዥን መርሃ ግብር አቅራቢ ከአንድ ታዳጊ ወሲባዊ ይዘት ያለው ፎቶግራፍ ለማግኘት መክፈላቸውን በመጀመሪያ የዘገበው ዘ ሰን ጋዜጣ ነው።

ጋዜጣው የጋዜጠኛውን ማንነት ሳይጠቅስ ከአንድ ታዳጊ ከ17 ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ልቅ ወሲባዊ ይዘት ያላቸው ፎቶዎች እንዲላክለት በአስር ሺህ ፓውንዶች የሚቆጠር ገንዘብ መክፈሉን የጋዜጣው ሪፖርት ይጠቁማል።

ቢቢሲ የግል የመረጃ መብታቸው ጋር ይጣረሳል በሚል የአቅራቢውን ማንነት ከመግለጽ ተቆጥቦ ነበር።

ጋዜጣው ለዘገባው ምንጮች የሆኑት የታዳጊው/ታዳጊዋ እናት እና እንጀራ አባት ሲሆኑ፣ በኋላ ግን ታዳጊውን የወከሉ የሕግ ባለሙያ ዘገባውን “እርባና ቢስ” ሲሉ አጣጥለውት ነበር።

ጋዜጠኛው ላይ የቀረቡ ያልተገቡ ድርጊቶች ውንጀላን ተከትሎ ቢቢሲ የራሱን ውስጣዊ ምርመራ አካሂዷል።

ጋዜጠኛው ከሥራ መልቀቁን አስመልክቶ የታዳጊው እናት ዘ ሰን ጋር በነበራቸው ቆይታ ስጋት እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል።

“ጋዜጠኛው ከሥራ በመልቀቁ ስንጠብቀው የነበረውን መልስ ላናገኝ እንችላለን የሚል ስጋት አድሮብናል። በምርመራ ስህተት መፈጸሙ ቢረጋገጥም ምንም ዓይነት እርምጃ ላይወሰድበት ይችላል” ስትል ገልጻለች።

ለአራት አስርት ዓመታት በቢቢሲ ጋዜጠኝነት የሠራው ሂው ኤድዋርድስ በተቋሙ ውስጥ ከፍተኛ ደመወዝ ከሚከፈላቸውም አንዱ ነው።

በአውሮፓውያኑ 2022፣ 435 ሺህ ፓውንድ እንዲሁም በ2023፣ 439 ሺህ 999 እንደተከፈለው መረጃዎች ያሳያሉ። ጋዜጠኛው ከባለቤቱ እና ከአምስት ልጆቹ ጋር በለንደን ይኖራል።