ጀልባ

ከ 36 ደቂቃዎች በፊት

በሁለት ሳምንት ልዩነት ውስጥ ዳግም ቀይ ባሕር ላይ ባጋጠመ የጀልባ መስመጥ አደጋ የ16 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሕይወት ማለፉ ተገለጸ።

ሰኞ ሚያዝያ 14/2016 ዓ.ም. 77 ኢትዮጵያውያንን ይዛ ከየመን ወደ ጂቡቲ ስትጓዝ የነበረች ጀልባ ሰምጣ ሴቶች እና ሕጻናትን ጨምሮ 16 ሰዎች መሞታቸውን በጂቡቲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና የመንግሥታቱ ድርጅት አስታውቀዋል።

ከሁለት ሳምንት በፊት ሚያዚያ 1/2016 ዓ.ም. መነሻቸውን ጂቡቲ አድርገው ወደ የመን ሲጓዙ የነበሩ ስደተኞች ጀልባቸው በጂቡቲ ባሕር ዳርቻ ላይ ተገልብጣ ቢያንስ 38 ኢትዮጵያውያን መሞታቸው ይታወሳል።

ሰኞ ዕለት ባገጠመው አደጋ ሕይወታቸው ማለፉ ከተረጋገጡት 16 ሰዎች በተጨማሪ 28 ሰዎች እስከሁን የደረሱበት አልታወቀም። በዚህም የሟቾች ቁጥር ከፍ ሊል እንደሚችል ስጋት አለ።

የተባበሩት መንግሥታት የፍልሰተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ከአደጋው 33 ሰዎች በሕይወት መትረፋቸውን ገልጾ፣ የጠፉትን ለማግኘት በሚደረገው ጥረት ለአካባቢው ባለሥልጣናት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከየመን ወደ ጂቡቲ ስትጓዝ የነበረችው ጀልባ ላይ አደጋው ያጋጠመው ጎዶሪያ በሚባል ቦታ መሆኑን ገልጾ፣ የአደጋው ምንስኤ ምን እንደሆነ አልጠቀሰም።

በየዓመቱ ከ200 ሺህ የሚበልጡ ስደተኞች ከጅቡቲ ተነስተው ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገራት ለመድረስ በየብስ እና በባሕር አደገኛ ጉዞ ያደረጋሉ።

ባለፉት አምስት ዓመታት በጀልባ መስመጥ አደጋ ብቻ ከ200 በላይ ኢትዮጵያውያን ሕይወት ማለፉን አሃዞች ያሳያሉ።

ምንም እንኳ ስደተኞች በዚህ የጉዞ አቅጣጫ አደገኛ ሁኔታ እየገጠማቸው ቢሆንም፣ የስደተኞች ቁጥር አሁንም እየጨመረ ነው።

ከሁለት ሳምንት በፊት 38 ስደተኞች ሕይወታቸውን ያጡበትን አደጋ ተከትሎ በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ “በጅቡቲ በኩል ወደ የመን የሚደረግ ሕገ ወጥ ጉዞ ከሞት ውጪ ሌላ ትርፍ የለውም” ብሎ ነበር።

አክሎም ኢትዮጵያውያን በደላሎች “በመታለል ውድ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው በዚህ አደገኛ የጉዞ መስመር” ከመንቀሳቀስ እንዲቆጠቡ አሳስቧል።

ኤምባሲው የፍትህ አካላት ከገጠራማ የአገሪቱ አካባቢዎች ዜጎቻችን በመመልመል ለስደት በሚዳርጓቸው ግለሰቦች ላይ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪውን አስተላልፏል።