የሚቃጠል ቤት

ከ 8 ሰአት በፊት

በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ አጎና በተባለ ‘የቀበሌ ከተማ’ ባለፈው ሰኞ ሚያዚያ 7/2016 ዓ.ም. በፋኖ እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል የተካሄደ ግጭትን ተከትሎ ነዋሪዎች መገደላቸውን እና በርካታ ቤቶች መቃጠላቸውን የተጎጂ ቤተሰቦች እና የዐይን እማኞች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ጋይንት፣ ሞጃ፣ እስቴ እና ስማዳ ለተባሉ የደቡብ ጎንደር ወረዳዎች ማዕከል ናት በተባለችው አጎና የፋኖ ታጣቂዎች እና የመንግሥት ኃይሎች “በአጋጣሚ መንገድ ላይ ተገናኝተው” የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸውን ተከትሎ ጥቃቱ መፈጸሙን አራት ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ከእስቴ ወረዳ የመጡ ናቸው የተባሉ የፋኖ ታጣቂዎች እና ወደ ጋይንት ወረዳ በመጓዝ ላይ ነበሩ የተባሉ የመንግሥት ኃይሎች መጋጨታቸውን ተከትሎ በንጹሃን ሰዎች እና በቤቶች ላይ ጥቃቱ መፈጸሙን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ሰኞ ሚያዚያ 7/2016 ዓ.ም. ጠዋት 3 ሰዓት አካባቢ ግድያው እንደተፈጸመ የተናገሩ አንድ የአካባቢው ነዋሪ፤ “በተኩስ ልውውጡ የመንግሥት ኃይሎች ጉዳት ስለደረሰባቸው ጥቃቱን እንደፈጸሙ” ተናግረዋል።

አንድ የአጎና ነዋሪ “በአጋጣሚ የመኪና መንገድ ላይ እና መንደር ላይ ያገኟቸውን ንጹሃን አንድ ሴት እና አራት ወንዶችን ነው የመቷቸው” ሲሉ ስለ ጥቃቱ ተናግረዋል።

“ከረምቡላ ቤት፣ ፑል ቤት ያሉትን እየከፈቱ እዚያ የሚጫወቱትን ነው ጨፍጭፈዋቸው የሄዱት” ያሉ ሌላ ነዋሪ ድግሞ፤ ይህ ሲሆን “የፋኖ ኃይሎች በቦታው አልነበሩም” ብለዋል።

በጥቃቱ የ22 ዓመት ወንድማቸው እንደተገደለባቸው ለቢቢሲ የተናገሩ አንድ የሃይማኖት አባት፤ ታናሽ ወንድማቸው ተደብቆ ከነበረበት ፑል ቤት ከሦስት ጓደኞቹ ጋር መገደሉን ተናግረዋል።

ወንድማቸው ከመሞቱ በፊት “ነፍሱ” ላይ ደርሼ ነበር ያሉት ይኚህ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ ነዋሪ፤ ጤና ጣቢያ ማድረስ ባለመቻላቸው ወደ ቤታቸው ወስደው የህክምና እርዳታ ቢደረግለትም ሕይወቱ እንዳለፈ ተናግረዋል።

“ከፋኖ ጋር ግንኙነት የለውም። ዐይን ዐይኑን የማየው ወንድሜን ነው ቁርጥ አድርገው የጣሉት። . . . ተማሪ ነበር። አሁን ትምህርት ስለሌለ እርሻ እያረሰ ነበር የሚኖረው፤ ገበሬ ነው” ሲሉ ስለ ወንድማቸው ተናግረዋል።

ሟቾቹ አራት ወንዶች እና አንድ ውሃ ስትቀዳ ነበር የተባለች ህጻን እንደሆኑም የሃይማኖት አባት የሆኑት ነዋሪ ተናግረዋል።

የሁሉም ሟቾች ቀብር በማግሥቱ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ 6 ሰዓት ላይ ‘አጎና ማሪያም’ ቤተ-ክርስቲያን እንደተፈጸመ የሃይማኖት አባቱ ተናግረዋል።

የሰላማዊ ሠዎቹን ግድያ የመከላከያ ሠራዊት አባላት እንደፈጸሙት የተናገሩት ነዋሪዎች፤ ጥቃት ፈጻሚዎችን በደንብ ልብሳቸው እና በሚያሽከረክሯቸው መኪኖች መለየት እንደቻሉ ገልጸዋል።

ለግድያው ምክንያት ፋኖን ትደግፋላችሁ የሚል እንደሆነ የተናገሩ አንድ ነዋሪ፤ “እናንተ ባትኖሩ ፋኖ አይኖርም ነበር” በሚል ጥቃቱ እንደተፈጸመ ተናግረዋል።

የመንግሥት ኃይሎች ከተማዋን ጥለው ወጥተው [ከጋይንት መስመር] ሲመለሱ ከሰዓት በኋላ ሰንዝረውታል በተባለ ጥቃት 18 ቤቶችን መቃጠላቸውንም ነዋሪዎቹ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቢቢሲ በአካባቢው የተቃጠሉ ናቸው የተባሉ ቤቶችን የሚያሳይ ቪዲዮ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያገኘ ቢሆንም፣ ስለትክክለኛነታቸው ግን ማረጋገጥ አልቻለም።

በነዋሪዎች ላይ ስለተፈጸመው ግድያ እና በቤቶች ላይ ስለደረሰው ቃጠሎ ቢቢሲ ከደቡብ ጎንደር ዞን አስተዳደር እና ከአካባቢው ኮማንድ ፖስት ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

የሚቃጠል ቤት

15 መኖሪያ ቤቶች እና ሁለት ጎጆ ቤቶች መቃጠላቸውን የተናገሩ ቤታቸው የተቃጠለባቸው አንድ ነዋሪ፣ ሙሉ ለሙሉ ከወደሙ ሦስት ቤቶች ውስጥ አንደኛው የእሳቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ነዋሪው ቤታቸው 30 ሺህ የጥሬ ገንዘብ እና ለንግድ የተቀመጠ 90 ሺህ ብር የተገዛ እህል፣ እንዲሁም ለቀለብ የተዘጋጁ ምግቦች እና ሙሉ ንብረታቸው እንደተቃጠለባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“በየተራ” ዘመድ ቤት ተጠልለው እንደሚገኙ የተናገሩት የጥቃቱ ሰለባው፤ ራሳቸውን ለማጥፋት አስበው እንደነበር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የንግድ እና የመኖሪያ (ለሁለት የተከፈለ) ቤታቸው የተቃጠለባቸው ሌላ ነዋሪ ቤታቸውን ከሠሩት ገና አንድ ዓመት መሆኑን ገልጸዋል።

የአካባቢው ነዋሪው ጭስ አይቶ ቤቶችን ለማጥፋት ወደ አካባቢው ሲመለስ ተኩስ እንደተከፈተበትም ተናግረዋል።

ግለሰቧ ቤታቸው እየተቃጠለ መሆኑን በሽሽት ላይ እያሉ ተደውሎ እንደተነገራቸው ገልጸው፤ ለማጥፋት ያደረጉት ሙኩራ መከላከያ ናቸው ያሏቸው የመንግሥት ኃይሎች በከፈቱት ተኩስ እንዳልተሳካ እና ቤታቸው ከነ ሙሉ ንብረቱ እንደተቃጠለባው ገልጸዋል።

የአካባቢው ማኅበረሰብ ድጋፍ እያደረገላቸው እንደሆነ የተናገሩት ነዋሪዋ፤ ቤቶቹ ‘በጋዝ እና ላይተር’ እንደተቃጠሉ ተናግረዋል።

በቤት ቃጠሎው ወቅት የአካባቢው ነዋሪዎች ግድያው በመፈጸሙ “ነፍሱን ለማዳን” ከከተማው በመውጣቱ ምክንያት በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት አለመድረሱን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

“ዘወትር ሲመላለሱ እናያቸዋለን። በመኪና ነው የሚመጡትም። ያው ማዳበሪያም ይዘው ይወርዳሉ፤ ሬሽንም ለመውሰድ ይወጣሉ” በማለት ግድያውን እና የቤት ቃጠሎውን የፈጸሙት የመንግሥት ኃይሎች ናቸው በማለት አንድ ነዋሪ ከሰዋል።

በስጋት የተሸበበው የአካባቢው ነዋሪ ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ጥቃት በመድረሱ አካባቢውን ለቆ በተለይም ወደ ገጠር “እየተሰደደ” መሆኑን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

እርሳቸው “ደካማ አባት” ስላላቸው ለቀው መውጣት እንዳልቻሉ የተናገሩ አንድ ሌላ ነዋሪ፤ “ከከተማዋ አብዛኛው ሕዝብ ለቋል። እቃ፣ እህል እየተጫነ ነው። ከተማዋ ትለበለባለች [ትቃጠላለች] ተብሎ ማለት ነው” ሲሉ ስለ ስጋቱን ተናግረዋል።

“ቤቱ ብቻ ነው ቆሞ ያለው። ሰውና ንብረቱ ሸሽቷል” ሲሉ ሌላ ነዋሪ ሕዝቡ በስጋት ምክንያት ከተማዋን ለቆ እየወጣ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

“ነገ መጡ ዛሬ መጡ እየተባለ [ነው]” ያሉ አንድ ነዋሪ ተመሳሳይ ጥቃት ይፈጸማል በሚል አካባቢው ላይ አሁንም ስጋት አለ ብለዋል።

“አጎና ዋስትና የላትም። ከሌላው ቀበሌ፤ ከሌላው ወረዳ የተለየ [ነው]። ሕዝቡ ንጹህ አርሶ አደር ነው፤ አርሶ አደር ተገድሎ ምንድን ነው የሚገኘው? አርሶ አደር ከሌለ እኮ የማንኛው ሠው ሕይወት አስቸጋሪ ነው። አርሶ አደር ይገደል ተብሎ የተወሰነው ውሳኔ ነው አልገባኝ ያለው። ለማን እንደምንነግርም ግራ ገብቶናል” ያሉ ነዋሪ በአካባቢው ስጋት ስለመንገሱ ተናግረዋል።

የፌደራል መንግሥት ኢመደበኛ ያላቸውን ታጣቂዎች ትጥቅ ለማስፈታት መወሰኑን ተከትሎ በአመራ ክልል የተከሰተው አለመረጋጋት በተለያዩ የክልሉ ክፍሎች ውስጥ ከተስፋፋ አንድ ዓመት ሊሞላው ተቃርቧል።

በክልሉ የተሰማራው የመከላከያ ሠራዊት ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር በሚያካሂደው ግጭት የበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን በተለያዩ ጊዜያት የወጡ ሪፖርቶች ያመለክታሉ።