ህወሓት ብልጽግናን ለመቀላቀል እየተደራደረ መሆኑ ተሰማ
ህወሓት ከአራት ዓመት በፊት “ሕገወጥ ነው” ያለውን ገዥውን ፓርቲ ብልጽግና ለመቀላቀል ተከታታይ ድርድሮች እያደረገ መሆኑ ተሰምቷል።
ከኹለት ዓመት ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት የተፈረሙት ህወሓት እና ገዥው ፓርቲ ብልጽግና ውህደት ለመፍጠር ድርድር እያደጉ መሆኑን ዋዜማ ራዲዮ ዘግባለች።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ በሊቀመንበርነት የሚመሩትን ብልጽግናን በመቀላቀል ህወሓት ለመቀላቀል ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጡን ዘገባው አመለክቷል፡፡
ከብልጽግና በፊት የነበረው ኢሕአዴግ እኩል የሥራ አስፈፃሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ ውክልና ያላቸው አራት ንዑስ ፓርቲዎች ጥምረት ሲሆን፣ ብልጽግና ግን አንድ ወጥ ፓርቲ ነው። የብልጽግና የፓርቲ ውክልና በህዝብ ብዛት የሚወሰን እንጂ እንደ ኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች እኩል ውክልና አይኖራቸውም።
አሁን እየተደረገ ባለው ድርድር ህወሓት እና የብልጽግና ፓርቲ ሕገ-ደንብ ተሻሽሎ በፓርቲ ውስጥ አባል ድርጅቶች እኩል የማዕከላዊ ኮሚቴና የሥራ አስፈፃሚ ውክልና እንዲኖራቸው ይፈልጋል ተብሏል። ብልጽግና ግን ህወሓት የተናጠል ህልውናውን አክስሞ ብልፅግናን እንዲቀላቀልና ውክልናውም በትግራይ ህዝብ ቁጥር ልክ የሚወሰን መሆኑን ይገልጻል።
የህወሓት ሊቀ መንበር ደብረፅዮን ገብረሚካዔል በአዲስ አበባ ተገኝተው ይህን ድርድር የጀመሩት ሲሆን፤ ከሁለት ሳምንት በኋላ የብልጽግና ምክትል ሊቀመንበር አደም ፋራህ ወደ መቀሌ ተጉዘው በጉዳዩ ላይ በስፋት መነጋገራቸው ተገልጿል።
በህወሓት በኩል ብልጽግናን መቀላቀል “ስህተት ነው፣ አስፈላጊም አይደለም” ብለው የሚያምኑ አመራሮች መኖራቸው ተመላክቷል፡፡ አበንጻሩ “ውህደቱ ለትግራይ ችግሮች መፍትሄ ለማምጣት ጠቀሜታ አለው፣ በተለይም የትግራይን ጸጥታና ደህንነት ለመስጠበቅ ከብልጽግና ጋር አብሮ መቆም አስፈላጊ ነው” ብለው የሚያምኑ መኖራቸውንም ዘገባው አመላክቷል።
ምንጭ፦ ዋዜማ ራዲዮ