April 23, 2024 – Konjit Sitotaw 

አማጺው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ወረ ጃርሶ ወረዳ ከአማራ ክልል በተነሱ ተሽከርካሪዎች ላይ ባለፈው ሳምንት ዓርብ በርካታ ሰዎችን አፍኖ መውሰዱን ዋዜማ በስፍራው ካሉ ምንጮቿ ሰምታለች።

አማጺው ቡድን እገታውን የፈጸመው፣ በጎሃጽዮን እና ቱሉ ሚልኪ ከተሞች መሃል ባለች ቢቱ ወንዝ ተብላ በምትጠራ ሥፍራ እንደሆነ ምንጮች ተናግረዋል።

እገታው የተፈጸመው፣ መነሻውን ከምሥራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ ባደረገው በተልምዶ “ታታ” ተብሎ በሚጠራ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ እና በሦስት ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ሲጓዙ በነበሩ መንገደኞች ላይ እንደኾነ ምንጮች ጠቁመዋል።

ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ፣ ታፍነው የተወሰዱት ሰዎች በታጣቂ ቡድኑ ቁጥጥር ስር መኾናቸውንም ዋዜማ ባደረገችው ማጣራት መረዳት ችላለች።