![ቲሙር ኢቫኖቭ [ግራ] ቭላድሚር ፑቲን [መሐል] እና መከላከያ ሚኒስትሩ ሰርጌይ ሾይጉ [ቀኝ]](https://i0.wp.com/ichef.bbci.co.uk/ace/ws/640/cpsprodpb/85ec/live/10487a70-01f7-11ef-8369-47dc4454b972.jpg?w=800&ssl=1)
ከ 4 ሰአት በፊት
የሩሲያ ምክትል መከላከያ ሚኒስትር ጉቦ ተቀብለዋል በሚል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የሀገሪቱ መርማሪ ቡድን አስታወቀ።
መርማሪው ኮሚቴ ማክሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ ቲሙር ኢቫኖቭ በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ ተከፍቶባቸዋል።
በአውሮፓውያኑ 2016 የመከላከያ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የተሾሙት የ47 ዓመቱ ኢቫኖቭ የሩሲያ ወታደራዊ መሠረተ-ልማት በማበልፀግ ይታወቃሉ።
አክቲቪስቶች በሩሲያ ሙስና ተንሰራፍቷል ሲሉ ትችት ማቅረብ ከጀመሩ ሰነባብተዋል።
በሟቹ ተቃዋሚ አሌክሴይ ናቫልኒ የተቋቋመው የፀረ-ሙስና ፋውንዴሽን በ2022 ምክትል ሚኒስትሩ በተለይ በሩሲያ ቁጥጥር ሥር ባሉ የዩክሬን አካባቢዎች “በሙስና ወንጀል እየተሳተፉ ነው” ሲል ወቀሳ አቅርቦባቸው ነበር።
ተቋሙ እንደሚለው በሩሲያ የአየር ድብደባ በወደመችው በዩክሬኗ የወደብ ከተማ ማሪዮፖል ሲካሄድ ከነበረው ግንባታ በጣም ብዙ ገንዘብ አግኝተዋል ሲል ይወቅሳቸዋል።
- አቶ ጌታቸው ረዳ ከብልፅግና ጋር ስለመዋሃድ፣ ስለሰሞኑ ግጭት እና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ስላላቸው ግንኙነት ምን አሉ?ከ 5 ሰአት በፊት
- ዩኬ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ የምትልክበት ሕግ ምንድን ነው? ተፈጻሚነቱስ በማን ላይ ነው?ከ 5 ሰአት በፊት
- በሁለት ሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ በደረሰ የጀልባ አደጋ 16 ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ሞቱ23 ሚያዚያ 2024
መርማሪው ኮሚቴ ያወጣው መግለጫ ኢቫኖቭ ለቀረበባቸው ክስ የሰጡት ምላሽ ያለ እንደሆነ የሚገልጠው ነገር የለም።
ኢቫኖቭ በቁጥጥር ሥር የዋሉበት የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንድ ተጠርጣሪ የወሰደው ጉቦ ከአንድ ሚሊዮን ሩብልስ [10 ሺህ ዶላር ገደማ] በላይ ሲሆን ነው በቁጥጥር ሥር የሚውለው ይላል።
ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ ግለሰቦች ጠብሰቅ ያለ ገንዘብ እና እስከ 15 ዓመት የሚደርስ ቅጣት ሊተላለፍባቸው ይችላል።
ኢቫኖቭ ከዚህ ቀደም የሞስኮው ክልል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ። የአሁኑ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሾይጉ ለተወሰነ ጊዜ የሞስኮው አስተዳዳሪ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን የኢቫኖቭ የቅርብ ወዳጅ ናቸው ይባልላቸዋል።
የሩሲያ ከፍተኛ ባለሥልጣን በሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር ዋለ የሚለው ዜና እምብዛም የተለመደ አይደለም። አብዛኛዎቹ ባለሥልጣናት ወንበራቸውን ተጠቅመው ግላዊ ጥቅም አጋብሰዋል ተብለው ይወቀሳሉ።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ድሚትሪ ፔስኮቭ፤ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ሚኒስትሩ በቁጥጥር ሥር ስለመዋላቸው ቀደም ብሎ ተነግሯቸዋል ሲሉ ለሪፖርተሮች ተናግረዋል።
ኢቫኖቭ በአሜሪካ እና ዩኬ የጉዞ ማዕቀብ፤ ከአውሮፓ ሕብረት ደግሞ ንብረታቸው እንዳይንቀሳቀስ እግድ ከተጣለባቸው የሩሲያ ባለሥልጣናት መካከል ናቸው።
የአውሮፓው ሕብረት ግለሰቡ “በሩሲያ ወታደራዊ አስተዳደር እርከን 10ኛው ግለሰብ ናቸው” ይላል።