ከሁለት ዓመት በፊት ገደማ ወደ ሩዋንዳ ስደተኞችን ይዞ ሊጓዝ የነበረው አውሮፕላን
የምስሉ መግለጫ,ከሁለት ዓመት በፊት ገደማ ወደ ሩዋንዳ ስደተኞችን ይዞ ሊጓዝ የነበረው አውሮፕላን ላይ የሕጋዊነት ጥያቄ ተነስቶበት ጉዞው ተሰርዞ ነበር

ከ 5 ሰአት በፊት

ለበርካታ ወራት ብዙ ሲያወዛግብ የቆየው ወደ ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) በሕገወጥ መንገድ የገቡ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ የሚያስችለውን ሕግ የአገሪቱ ፓርላማ ጸድቆ ሕግ ሆኗል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ሕጉ ተግባራዊ ሆኖ ሐምሌ 2016 ዓ.ም. ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ መላክ እንደሚጀር አስታውቀዋል።

ይህ ሕግ ኢንግሊሽ ቻናል ተብሎ በሚጠራው የውሃ አካል በኩል በጀልባ በሕገ-ወጥ መንገድ ዩኬ የደረሱ ስደተኞችን በአስገዳጅ ሁኔታ ወደ ሩዋንዳ የሚልክ ነው።

ስደተኞቹ በዩኬ የሚያቀርቡት የጥገኝነት ጥያቄ የሚታየው ሩዋንዳ ተወስደው ሲሆን፣ የጥገኝነት ጥያቄያቸው አዎንታዊ መልስ የሚያገኝ ከሆነ ስደተኞቹ በቋሚነት ወደ ዩኬ እንዲመለሱ ይደረጋል።

የጥገኝነት ጥያቄያቸው ውድቅ ከሆነ ደግሞ ስደተኞቹ ሌላ ምክንያት በማቅረብ በሩዋንዳ አልያም በሌላ ሦስተኛ አገር የጥገኝነት ጥያቄ ማቅረብ ይችላሉ።

የዩናይትድ ኪንግደም ባለሥልጣናት በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ አገር የሚገቡትን ስደተኞች ወደ ሩዋንዳ መላካቸው በፈረንሳይ በኩል በጀልባ ወደ ግዛታቸው የሚደረግ ጉዞን በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል ይላሉ።

ዩኬ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን አማካይነት ይህን ሕግ በተደጋጋሚ ለማስጸደቅ እና ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ስደተኞችን ያሳፈረ አውሮፕላን ሰኔ 2014 ዓ.ም. ወደ ሩዋንዳ በረራ ለማድረግ እየተዘጋጀ ሳለ ሕጋዊ ጉዳዮች ተነስተውበት ጉዞው ሳይደረግ ቀርቷል።

የዩኬ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከአምስት ወራት በፊት ይህ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ የመላኩ ዕቅድ ሕጋዊ መሠረት የሌለው እና ትክክለኛ ስጋት ያላቸውን ሰዎች ወደ ሩዋንዳ መላካቸው፣ ወደ ትውልድ አገራቸው ተገደው እንዲመለሱ እና አደጋ ላይ እንዲወድቁ ሊያደርግ ይችላል ብሎ ነበር።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆኑ ቡድኖችም የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ አነስተኛ ወደ ሆነባት ሩዋንዳ ስደተኞችን መላክን አጥብቀው እንደሚቃወሙት በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል።

የዩኬ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ መላኩ ሕጋዊ መሠረት የለውም ሲል፣ በሰጠው ውሳኔ ላይ የሩዋንዳ መንግሥትን በመቃወማቸው የተገደሉ ሰዎች መኖራቸውን ከግምት ማስገባቱን ጠቅሷል።

ይህን ተከትሎ የዩኬ መንግሥት ከሩዋንዳ ጋር የስደተኞችን ደኅንነት ለማስጠበቅ ተጨማሪ ስምምነት ደርሶ፣ ሩዋንዳ ለስደተኞች ደኅንነቷ የተጠበቀ ነው ሲል ደምድሟል።

ከሩዋንዳ ውጪ ወደ ሌላ አገር የማሻገር ዕቅድ አለ?

እንደ ‘ዘ ታይምስ’ ጋዜጣ ከሆነ ዩናይትድ ኪንግደም ከሩዋንዳ ጋር የደረሰችውን ስምምነት ዓይነት ከቦትስዋና፣ ከአይቮሪ ኮስት፣ ከኮስታሪካ እና አርሜኒያ ጋር ልትፈጽም ትችላለች።

‘ዘ ታይመስ’ ሾልከው የወጡ ሠነዶችን ተመልክቶ ባጠናቀረው ዘገባ ዩኬ ስደተኞችን ለማስተላለፍ ከአራቱ አገራት ጋር እያደረገች ያለችው ንግግር ወደፊት መራመድ አልቻለም ይላል።

ይልቁንም የመካከለኛዋ አሜሪካ አገር ኮስታሪካ ስደተኞችን ከዩኬ የመቀበልን ሐሳብ ሙሉ በሙሉ ትታዋለች።

የኮስታሪካ ፕሬዝዳንት ሮደሪጎ ሻቬስ “ኮስታሪካ የውጭ አገር ስደተኞችን እንደማትቀበል ለዩናይትድ ኪንግደም አሳውቀናል” ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

የዩኬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስደተኞችን ለማስተላለፍ እያጤናቸው ካሉ አገራት መካከል ፓራጓይ፣ ፔሩ፣ ብራዚል እና ኤኳዶር ይገኙበታል ተብሏል።

ሩዋንዳ ስደተኞችን ከዩኬ ለመቀበል የተስማማቸው ቢያንስ 370 ሚሊዮን ፓዎንድ በክፍያ መልክ ስለምትቀበል ነው።

ቀደም ሲል የወጡ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት ሩዋንዳ አንድ ስደተኛን በአምስት ዓመታት ውል ተቀብላ ለማቆየት እስከ 150ሺህ ፓዎንድ ይከፈላታል።

እአአ 2022 ጋና ከዩኬ ስደተኞችን ለመቀበል ዕቅድ አላት የሚል ሪፖርት ውጥቶ ነበር። ይሁን እንጂ ይህን ሪፖርት የጋና መንግሥት ከዩኬ ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ ጨርሶ አልተነጋገርኩም በሚል ውድቅ አድርጎታል።

ከጋና በተጨማሪ ኬፕ ቬርድ፣ ሴኔጋል፣ ታንዛኒያ እና ሲዬራሊዮን ስደተኞችን እንዲቀበሉ በዩኬ “የተጠባባቂ ዝርዝር” ውስጥ ያሉ አገራት ናቸው ተብሎም ነበር።

ዘ ማይግሬሽን ፖሊሲ ኢንስቲትዩት የተባለው ተቋም የአውሮፓ ኅብረት የቀድሞ ሶቪዬት ኅብረት ሞልዶቫ እና ጆርጂያ ስደተኞችን ሊቀበሉ የሚችሉ አገራት ናቸው ብሎ ለይቷል ይላል።

protesters

መሰል ሕግ ከዚህ ቀደም ተግባራዊ ሆኖ ያውቃል?

በእአአ 2013 እና 2018 እስራኤል ወደ 4 ሺህ የሚጠጉ ኤርትራውያን እና ሱዳናውያን ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ልካ ነበር።

እስራኤል ስደተኞቹን ወደ ሩዋንዳ “ያዘዋወርኩት በራሳቸው ፍቃድ ነው” ብትልም ለቢቢሲ ቃላቸውን የሰጡ ስደተኞች ግን “ወደ ሩዋንዳ ከመምጣት ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበረንም” ብለዋል።

ከእስራኤል ወደ ሩዋንዳ የተዘዋወረው ኤርትራዊው ባሃቤሎም መንገሻ ከእስራኤል ባለሥልጣናት ሦስት አማራጮች ቀርበውለት እንደነበረ ይናገራል።

ወደ ኤርትራ መመለስ፣ እስራኤል ውስጥ ወዳለ የስደተኞች ማቆያ ጣቢያ (እስር ቤት) ገብቶ መኖር አልያም 3 ሺህ 500 ዶላር ተከፍሎት ወደ ሩዋንዳ መሄድ።

በዚህ ጉዳይ በዩኬ እና በእስራኤል መካከል ያለው ልዩነት ዩኬ ከሩዋንዳ ጋር ስታደርገው የነበረው ድርድር ለሕዝብ ይፋ ሲደረግ የቆየ ነው።

በአንጻሩ እስራኤል ከሩዋንዳ ጋር ምንም ዓይነት ስምምነት ሳይኖራት ነበር ስደተኞቹን በምሥጢር ወደ ምሥራቅ አፍሪካዋ አገር ያዘዋወረችው።