የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

24 ሚያዚያ 2024, 15:01 EAT

አሜሪካ ውስጥ በድንገት በደረሰ አደጋ ምክንያት ከመንገድ ወጥቶ በእሳት በተያያዘ መኪና ውስጥ የነበረ ግለሰብን ሕይወት ያተረፉ ሁለት ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና ሌሎችም አድናቆት እየተቸራቸው ነው።

መኪና ላይ በተገጠመ ካሜራ የተቀረጸው ቪዲዮ እንደሚያሳየው ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ እና ሌሎችም በመንገዱ ላይ ሲያልፉ የነበሩ ሰዎች በእሳት ከተያያዘው መኪና አንድን ግለሰብ ለመታደርግ ያደረጉትን አስደናቂ ጥረት አሳይቷል።

ይህን ቪዲዮ የቀረጸው እና አሸከርካሪውን ከመኪናው ለማውጣት ከፍተኛ ትግል ሲያደርግ የነበረው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ከድር ቶላ ግለሰቡ ከባድ አደጋ ውስጥ እንደነበር ገልጿል።

ከድር እንዳለው “ከሚነደው መኪና ውስጥ የነበረውን ሹፌር ልናወጣ ስንታገል ዐይን ዐይናችንን ይመለከት ነበር” ሲል ክስተቱን በተመለከተ የፌስቡክ ገጹ ላይ ጽፏል።

በሴንት ፖል ሚኒሶታ ባጋጠመው በዚህ ክስተት ከሚነድ መኪና ውስጥ በሰዎች ጥረት ሕይወቱ የተረፈው ግሰለብ ከባድ ጉዳት አልደረሰበትም ተብሏል።

ይህን ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ የተሳተፉበት የነፍስ አድን ጥረትን የሚያሳየው ቪዲዮ በተለያዩ የአሜሪካ እና ኣለም አቀፍ የቴሌቪዢን ጣቢያዎች በስፋት እየታየ ነው።