አደጋው የደረሰበት ስፍራ
የምስሉ መግለጫ,አደጋው የደረሰበት ስፍራ

24 ሚያዚያ 2024, 14:33 EAT

በአዲስ አበባ ከተማ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ልዩ ስሙ ጠሮ መስጂድ በተባለ አካባቢ ለቤት ግንባታ የተከመረ ድንጋይ እና አፈር ተንዶ የሰባት ሠዎች ሕይወት አለፈ።

ረቡዕ ሚያዝያ 16/2016 ዓ.ም. ከሌሊት 11 ሰዓት ላይ የአደጋ ጥሪው እንደደረሰው ለቢቢሲ የተናገረው የአዲስ አበባ እሳት እና ድንገተኛ አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን፤ ድንጋይ እና አፈሩ ተደርምሶ አደጋው ሦስት ክፍል ያለው ቤት ላይ መድረሱን አስታውቋል።

የተቋሙ የሕዝብ ግንኙነት ባለሞያ አቶ ንጋቱ ማሞ የኮሚሽኑ ባለሞያዎች ወደ ስፍራው “በፍጥነት” ቢደርሱም ሕይወት ለማዳን ያደረጉት ጥረት ግን አልተሳካም ብለዋል።

“እተገነባ ያለው ቤት አፋፍ ላይ ነው፤ ከፍ ያለ ቦታ ነው። የተደረመሰባቸው ቤቶች ደግሞ ከስር ነው ያሉት። ከላይ ነው ወደ ታች የተደረመሰባቸው” ሲሉ ስለ አደጋው አስረድተዋል።

“አፈሩ ከፍተኛ መጠን ያለው ስለሆነ ሰለባዎቹ አየር በማጣት ነው ሕይወታቸውን ያጡት” ሲሉ ስለ ተጎጂዎች አሟሟት ተናግረዋል።

የነፍስ አድን ሠራተኞች ድንጋይ እና አፈር የተደረመሰባቸውን ሰዎች ሕይወት ለማትረፍ ለሁለት ሰዓታት ያህል ፍለጋ አከናውነው የአራት ሴቶች እና የሦስት ወንዶችን አስከሬን ማግኘታቸውን ለቢቢሲ አሳውቀዋል።

ሟቾቹ የአራት ዓመት ህጻን፣ ሦስት የ11 እና የ12 ዓመት ታዳጊዎች እንዲሁም ከ25 እስከ 30 ዓመት ያሉ ሦስት ወጣቶች መሆናቸውን አቶ ንጋቱ ገልጸዋል።

በደረሰው አደጋ ሕይወታቸው ያለፈው ሰዎች የሁለት ቤተሰብ አባላት መሆናቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለቢቢሲ ተናግሯል።

አደጋውን ተከትሎ የአዲስ አበባ ፖሊስ በሟቾች አስከሬን ለምርመራ ወደ ሆስፒታል መላኩን ለቢቢሲ ተናገረ ሲሆን፤ አደጋው የደረሰበት ምክንያት ምን እንደሆነ ለማወቅም ፖሊስ ምርመራ እያደረገ ነው ብሏል።

የፖሊስ ኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ የምርመራ ሲጠናቀቅ ውጤቱ ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ ተናግረው፤ ከምርመራው ጋር በተያያዘ በፖሊስ የተያዙ ሠዎች ስለመኖራቸው ከመናገር ተቆጥበዋል።

ለነፍስ አድን ሥራው ቦታው ምቹ እንዳልነበር ገልጸው፤ በሰው ጉልበት ሕይወት ለማዳን ባለመቻሉ በግንባታ ማሽን ቁፋሮው እንደተደረገ ተናግረዋል።

በአደጋው “ቤቱ ሙሉ ለሙሉ” መውደሙን የተናገሩት ባለሞያው፤ ለዚህም ቤቶቹ “በጭቃ እና በቀላል ማገር” የተሠራ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

ድንጋዩ እና አፈሩ በምን ምክንያት ተናደ የሚለውን ለማወቅ ፖሊስ የሚገነባው ቤት ባለቤት በሆኑት ግለሰብ ላይ ምርመራ እያካሄደ መሆኑንም አቶ ንጋቱ አክለው ለቢቢሲ ተናግረዋል።