እኤአ በ2010 እየተገነባ የነበረ መንገድ

24 ሚያዚያ 2024, 15:58 EAT

ተሻሽሏል 24 ሚያዚያ 2024, 15:59 EAT

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር “በፀጥታ ችግር” ምክንያት በተቋረጡ እና በቆሙ የመንገዶች ፕሮጀክቶች ላይ 34.95 ቢሊዮን ብር ካሳ በተቋራጮች መጠየቁን አስታወቀ።

አስተዳደሩ እስከ 2016 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ድረስ “በፀጥታ ችግር” ምክንያት “ሙሉ በሙሉ የኮንትራት ውላቸው የተቋረጠ” 31 የመንገድ ፕሮጀክቶች መኖራቸውንም ይፋ አድርጓል።

አስተዳደሩ ይህን ይፋ ያደረገው ዛሬ ረቡዕ ሚያዝያ 16/2016 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተካሄደው የአገሪቱ የመንግሥት መሠረተ ልማት ሂደት ውይይት ላይ ነው።

በውይይቱ ላይ የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒን ጨምሮ እና የፓርላማው አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ተገኝተዋል።

ከዛሬው ውይይት ቀደም ብሎ “ወቅታዊ የመንገድ ዘርፍ ተግዳሮቶች እና የመፍትሔ ሐሳቦች” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተልኮላቸዋል።

በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የተዘጋጀው እና ቢቢሲ የተመለከተው ይህ ሰነድ አሁናዊ የመንገድ ዘርፍ ተግዳሮቶች፣ እና የመፍትሄ ሃሳቦች ቀርበውበታል።

በሰነዱ አሁናዊ የመንገድ ዘርፍ ተግዳሮቶች ተብለው የተጠቀሱ ጉዳዮች የፀጥታ ችግር፣ የክፍያ መዘግየት፣ የወሰን ማስከበር ችግር፣ የግብዓቶች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መናር እና የአቅርቦት ችግር እንዲሁም የሥራ ተቋራጮች አቅም ውስንነት ናቸው።

በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት የፕሮጀክቶች መቆም እና መቋረጥ እንዲሁም፤ “የፀጥታን ችግር በመፍራት የፕሮጀክቶች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መናር” ማጋጠሙ በሰነዱ ላይ ሰፍሯል።

እስከ 2016 ግማሽ ዓመት በፀጥታ ችግር ምክንያት 31 የመንገድ ፕሮጀክቶች የኮንትራት ውላቸው “ሙሉ በሙሉ” መቋረጡን አስተዳደሩ አስታውቋል።

ከእነዚህ የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል 19ኙ የሚገኙት የፋኖ ታጣቂዎች እና የፌደራል መንግሥቱ ግጭት ውስጥ በገቡበት የአማራ ክልል ነው።

ለሁለት ዓመታት ያህል ጦርነት በተካሄደበት የትግራይ ክልል ደግሞ 11 የመንገድ ፕሮጀክቶች ውላቸው ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል። ቀሪው አንድ የመንገድ ፕሮጀክት ደግሞ የሚገኘው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ነው።

51 የመንገድ ፕሮጀክቶች ደግሞ በተመሳሳይ በፀጥታ ችግር ምክንያት በጊዜያዊነት መቆማቸው በሰነዱ ላይ ተመላክቷል። ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል ግማሽ ያህሉ በአማራ ክልል ተጀምረው የነበሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች ናቸው።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በሚንቀሳቀስበት የኦሮሚያ ክልል ደግሞ 19 የመንገድ ፕሮጀክቶች በጊዜያዊነት ቁመዋል።

ሰባት ፕሮጀክቶች ደግሞ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግንባታቸው እየተከናወነ አይደለም።

የፀጥታ ችግሮች የመንገድ ፕሮጀክቶች ከማቆም በተጨማሪ በተቋራጮች በኩል ቅሬታ መፍጠራቸውን አስተዳደሩ ጠቁሟል።

የሥራ ተቋራጮች ለወደሙባቸው እና ለጠፉባቸው የግንባታ መሳርያዎች፣ ፕሮጀክቶች ላይ ያሰማሯቸው መሳርያዎች እና ሠራተኞቻቸው ያለ ሥራ በመቆማቸው ላወጡት ወጪ እና ሠራተኞችቻውን እና መሳሪያዎቻቸውን ለማጓጓዝ ላወጡት ወጪ ካሳ መጠየቃቸውን የተቋሙ ሰነድ ያሳያል።

ከዚህ በተጨማሪ የቆሙ ፕሮጀክቶችን ለማስጀመር የዋጋ ማሻሻያ ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑም ተመላክቷል።

መንገድ ግንባታ ላይ የተሰማሩ ሰዎች

በፀጥታ ችግር በተቋረጡ እና በቆሙ ፕሮጀክቶች ላይ የአገር ውስጥ፣ የውጭ አገር የሥራ ተቋራጮች በድምሩ 34.95 ቢሊዮን ብር ካሳ ጠይቀዋል።

ከዚህ ውስጥ 87 በመቶ ወይም 30.5 ቢሊዮን ብር ካሳ የጠየቁት የአገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮች ናቸው።

ቀሪው 13 በመቶ ወይም 4.41 ቢሊዮን ብር ካሳ ደግሞ የተጠየቀው በውጭ አገር የሥራ ተቋራጮች ነው። የሥራ ተቋራጮቹ ካሳውን የጠየቁት ለወደመ እና ለጠፋ ንብረት መሆኑን የተቋሙ ሰነድ ላይ ሰፍሯል።

በተቋራጮቹ የተጠየቀው ካሳ ለመንገድ ፕሮጀክቹ ግንባታ ከሚያስፈልገው ገንዘብ 42 በመቶ ያህል ነው። የመንገድ ፕሮጀክቶቹን ለመገንባት በተገባው ውል መሠረት ወጪው 83.47 ቢሊዮን ብር ነው።

ለከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ተጠሪ የሆነው ይህ ተቋም ለፓርላማው በላከው ሰነድ ላይ ከካሳ ጋር በተያያዘ በተቋራጮች ለሚነሱ ጥያቄዎች ሊወሰዱ ይገባቸዋል ያላቸውን ምክረ ሃሳቦችም አቅርቧል።

የካሳ ጥያቄዎቹን በአገሪቱ ባለው የሕግ ማዕቀፍ ብቻ መልስ መስጠት፤ “በኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጫና” እንደሚፈጥር አስተዳደሩ ገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪም ሂደቱ “አገር በቀል የሥራ ተቋራጮችን የሚያከስም” እና የውጭ አገር ሥራ ተቋራጮች “ቀጣይ የልማት ተሳትፎ ላይ የሚኖራቸውን ፍላጎት በእጅጉ የሚጎዳ” መሆኑን አስገንዝቧል።

ስለሆነም ከካሳ ጋር በተያያዘ በተቋራጮች የሚነሱ ጥያቄዎችን “አስተዳደራዊ በሆነ መልኩ መፍትሔ መስጠት ተገቢ ነው” ብሏል።

ሌላኛው “አሁናዊ የመንገድ ዘርፉ ተግዳሮት” ተብሎ የተጠቀሰው ጉዳይ የክፍያ መዘግየት ነው።

ባለፉት አምስት የግንባታ ግብዓቶች ዋጋ መናር ጋር ተያይዞ ለፕሮጀክቶች ግንባታ የሚመደበው በጀት ጉድለት እንደሚያሳይ አስተዳደሩ በሰነዱ ላይ ጠቅሷል።

ባለፉት ዓመት ዓመታት ለፕሮጀክቶች መመደብ ከነበረበት 370.6 ቢሊዮን ብር ውስጥ የተመደበው 254.9 ቢሊዮን ብር ነው።

በጥሬ ገንዘብ ዕጥረት እስከ ስምንት ወር ድረስ ከተፈቀደው በጀት አስተዳደሩ መጠቀም የቻለው ከግማሽ በታች መሆኑን ይፋ አድርጓል። በዚሁ የጥሬ ገንዘብ ዕጥረት ምክንያት 32 ቢሊዮን ብር ያልተከፈለ ክፍያ መኖሩንም አስተዳደሩ አክሏል።

በውጭ ምንዛሬ ዕጥረት ምክንያት ደግሞ 248 ሚሊዮን ብር ክፍያ አለመፈጸሙን አስታውቋል። ይህ የውጭ ምንዛሬ ፍላጎት ወደ ብር ሲቀየር 14.3 ቢሊዮን ብር እንደሚሆን የገለጸው አስተዳደሩ፤ “በአጠቃላይ ወደ 46.2 ቢሊዮን ብር የሚገመት ያልተከፈሉ ክፍያዎች አሉ” ብሏል።

በክፍያዎች መዘግየት ምክንያት የፕሮጀክቶች አፈጻጸም መቀነስ፣ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን መጀመር አለመቻል እና የጨረታ ተሳታፊዎች ቁጥር መቀነስ መስተዋሉን አስተዳደሩ ገልጿል። በተቋሙ ሰነድ መሠረት የውል መቋረጥ እና የውል ጊዜ መራዘም ሌላው የክፍያ መዘግየት ያስከተለው ጉዳት ነው።

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የክፍያ መዘግየትን ለመፍታት ምክረ ሃሳቦችን አቅርቧል።

ከእነዚህ ምክረ ሃሳቦች መካከል፤ “የሥራ ተቋራጮች ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ጋር ያላቸውን ክፍያዎች አስይዘው ከባንክ የሚበደሩበትን አሠራር ማዘጋጀት” ቀዳሚው ነው።

የመንገድ ግንባታ

“ሥራ ተቋራጮች የነዳጅ አቅርቦት በብድር የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት” እና “በውጭ ምንዛሬ የሚከፈሉ ክፍያዎች ላይ ማሻሻያ ማድረግ” ከምክረ ሃሳቦቹ መካከል ናቸው።

የመንገድ ወሰን ማስከበርም ሌላኛው “አሁናዊ የመንገድ ዘርፍ ተግዳሮት” በሚል የቀረበ ጉዳይ ነው። የተጋነነ የንብረቶች ነጠላ ዋጋ፣ ንብረቶችን በወቅቱ አለማንሳት እና ሕገ ወጥነት ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ አጋጠሙ ተብለው በአስተዳደሩ ከተገለጹ “ተግዳሮቶች” መካከል ናቸው።

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ ያልተከፈለ 13.29 ቢሊዮን ብር የወሰን ማስከበሪያ ውዝፍ ክፍያ እንዳለበት በዚሁ ሰነድ ላይ አመላክቷል።

የፌደራል መንግስት ባለሥልጣናትን ሲያማርር የነበረው የካሳ ክፍያ በክልሎች እንዲከፈል የሚያደርግ አዋጅ ከአንድ ወር በፊት የሕዝብ ተወካዮች ምከር ቤት መቅረቡ ይታወሳል።

ከካሳ ክፍያ በመቀጠል “አሁናዊ የመንገድ ዘርፍ ተግዳሮት” በሚል የተጠቀሰው የግንባታ ግብዓቶች አቅርቦት ነው።

አስተዳደሩ “በአገሪቱ በተከሰተው የግንባታ ዕቃዎች የፍላጎትና የአቅርቦት ሚዛን አለመጣጣም ምክንያት ለፕሮጀክት ግንባታ የሚያስፈልግ የግንባታ ግብዓቶችን ማቅረብ አልተቻለም” ብሏል።

ይህ የግብዓት አቅርቦት ችግር የመንገድ ጥገና ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ተቋሙ ገልጿል።

ባለፉት አራት ወራት በአስፋልት እጥረት ምክንያት 663 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው መንገዶች በጠጠር መጠገናቸውን አስተዳደሩ አስታውቋል።

የመንገዶች በጠጠር መጠገን፤ “መንገዱ ጥራት የሌለውና ለረጅም ጊዜ አገልግሎት መስጠት የማይችል በመሆኑ በተደጋጋሚ ወጪ የሚያስወጣ” መሆኑን ገልጿል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት ለመንገድ ጥገና ያስፈልግ ከነበረው 41 ሺህ 384 ኪሎ ግራም አስፋልት ማቅረብ የተቻለው 3,464 ኪሎ ግራም ብቻ ነው።

በተጨማሪም መቅረብ ከነበረበት 800 ሺህ 453 ኩንታል ሲሚንቶ የቀረበው 68 ሺህ 576 ኩንታል ብቻ ነው።

እነዚህን የጥገና ግብዓቶች ማቅረብ ያልተቻለው “የተጠየቁትን ግብዓቶች ለማቅረብ ከሚያስፈለግው የውጭ ምንዛሬ አንጻር ባለባቸው የአቅም ውስንነት” እና “የአቅራቢዎች ውስንነት እና የማቅረብ ፍላጎት ማጣት” ምክንያት መሆኑ በሰነዱ ላይ አስፍሯል።