April 24, 2024 

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ የኾኑትን ቀሲስ በላይ መኮንንን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ 8 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መፍቀዱን የአገር ውስጥ የዜና ምንጮች ዘግበዋል።

የቀሲስ በላይ መኮንን እና ተጠርጣሪ ግብረ አበሮቻቸው ጠበቆች፣ ፖሊስ ዋስትና ለማስከልከል ያቀረባቸው ምክንያቶች አሳማኝ አይደሉም በማለት ተከራክረው እንደነበር ዘገባዎቹ አመልክተዋል።

ፖሊስ ካኹን ቀደም በተሰጠው የ7 ቀን የምርመራ ጊዜ፣ በወቅቱ የነበረ የካሜራ ቅጂ ከአፍሪካ ኅብረት መጠየቁን፣ ለወንጀል ተግባር የዋለ ተሽከርካሪ ማረጋገጫ ለማግኘት ለሚመለከተው አካል ጥያቄ ማቅረቡን፣ በተጠርጣሪው ኹለት መኖሪያ ቤቶች ላይ ብርበራ ማድረጉንና በብርበራ የተገኘ አንድ የጦር መሳሪያ ሕጋዊነቱን የማረጋገጥ ሥራ እየሰራ መኾኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል ተብሏል።

ቀሲስ በላይ ከሳምንት በፊት በቁጥጥር ስር የዋሉት፣ ከአፍሪካ ኅብረት የባንክ አካውንት በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር በሐሰተኛ ሰነዶች ለማውጣት ሞክረዋል ተብለው ተጠርጥረው እንደኾነ አይዘነጋም።