

April 24, 2024
ከዚህ በፊት ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ ተደርጎ የነበረው የጥሬ ቡና ወጪ ንግድ የገበያ ሁኔታ ሳይስተካከል ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት መደረጉ፣ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ከገበያ ሊያስወጣ እንደሚችል ሥጋት እንዳለ ተነገረ፡፡
በወጪና በገቢ ንግድ፣ እንዲሁም በጅምላና በችርቻሮ ንግድ የውጭ ባለሀብቶች እንዲገቡ ሲደረግ የገበያ ውድድርን ከመፍጠር አኳያ መልካም ጎን ቢኖረውም፣ መመርያው ገደቦችን ባለማስቀመጡ የአገር ውስጥ ቡና ላኪዎችን ከገበያ ሊያስወጣ እንደሚችል የቡና ላኪዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛት ወርቁ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ቡናን ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ሲከስሩ እሴት ጨምሮ ለገበያ ከማቅረብ ይልቅ ወደ አገር ውስጥ በሚያስገቧቸው ምርቶች ማካካስ የተለመደ መሆኑን የገለጹት አቶ ግዛት፣ ይህ የገበያ ሁኔታ ሳይሻሻል ለውጭ ባለሀብቶች ፈቃድ መሰጠቱ የተፈለገውን ያህል ውጤት ላያመጣ እንደሚችል ሥጋታቸውን አስረድተዋል፡፡
ገበያውን ሙሉ በሙሉ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ከማድረግ ይልቅ ከአገሬው ውስጥ ባለሀብቶች ጋር በጋራ የሚሠሩበት ሁኔታ በመመርያው ቢካተት የተሻለ ይሆን እንደነበር ገልጸው፣ አሁንም የሚመለከታቸው አካላት ከአገር ወስጥ ነጋዴዎች ጋር ውይይት ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ይህ ማለት ግን በውሳኔው አስፈላጊነት ላይ ጥያቄ ማንሳት አለመሆኑን፣ አገሪቱ ወደ ካፒታሊዝም እንድትገባ ከተፈለገ እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎች አስፈላጊ መሆናቸውንና ገደብ ማበጀት ይገባል ብለዋል፡፡
በጥሬ ቡና ወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ከውጭ ባለሀብቶች ጋር ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ከማስቻል አኳያ ምን ዓይነት ተግባራት ሊከናወኑ እንደታሰቡ፣ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ለቡናና ሻይ ባለሥልጣን የተደረገውን ተደጋጋሚ ሙከራ የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች ማብራሪያ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን በመግለጻቸው አልተሳካም፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ መመርያውን አስመልክቶ ባለፈው ሳምንት የኢንቨስትመንት ኮሚሽንና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ መመርያው ሲዘጋጅ ጥናቶች መደረጋቸውንና አራቱ ዘርፎች ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ብቻ ተከልለው መቆየታቸው የተፈለገውን ያህል ጥቅም እየሰጠ ባለመሆኑ፣ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በሚፈለገው መጠንና ጥራት እሴት የሚጨምሩ የአምራች ኢንቨስትመንት የተሸጋገሩበት ሁኔታ በጣም ውስን በመሆኑ ነው መባሉ አይዘነጋም፡፡
በተጨማሪም ከለላ በተሰጣቸው ዘርፎች ሰፊ የአገልግሎት ተደራሽነትና የጥራት ችግሮች በማጋጠማቸው፣ እንዲሁም ለሕገወጥ ድርጊት በሰፊው መጋለጣቸው አሳሳቢ በመሆኑ፣ የአገርንና የሕዝብን ጥቅም ከማረጋገጥ አንፃር የንግድ ኢንቨስትመንት መስኮች ለውጭ ባለሀብቶች መከፈት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ ተገልጾ ነበር፡፡