
April 24, 2024
- ሃያ አንድ ቀናት የሚፈጀው ጉዞ 66 ቀናት እየወሰደ ነው ተብሏል
የምግብ ዘይትና የስንዴ ዱቄት በቫይታሚንና በሚኒራሎች ለማበልፀግ የተዘጋጀውን አስገዳጅ የኢትዮጵያ ደረጃ ለመተግበር፣ በቀይ ባህር መተላለፊያ የመርከቦች እንቅስቃሴ መስተጓጎል እንቅፋት መሆኑ ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት በስንዴ ዱቄትና በምግብ ዘይት ላይ ያወጣውን አስገዳጅ ደረጃ ለመተግበር እስከ የካቲት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ የዕፎይታ ጊዜ ቢሰጥም፣ የዕፎይታ ጊዜው በቂ ባለመሆኑ እንዲራዘም ተደርጓል፡፡
አስገዳጅ ደረጃውን ለመተግበር እንቅፋት የሆነው ዋና ምክንያትም፣ በመካከለኛው ምሥራቅ በቀይ ባህር በንግድ መርከቦች ላይ የሁቲ አማጽያን እያደረሱት ያለው ችግር ነው ተብሏል፡፡
በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ከምግብ ነክ አስመጪ ማኅበር የቀረበለትን ጥያቄ መሠረት አድርጎ የዕፎይታ ጊዜው መራዘሙ ተገልጿል፡፡
አስገዳጅ ደረጃውን በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ለመተግበር በመርከብ እንቅስቃሴዎች ላይ የተፈጠረው ችግር አስመጪዎች በሌላ አማራጭ እንዲጠቀሙ በማድረጉ፣ 21 ቀናት ይፈጅ የነበረው ጉዞ አሁን ላይ 66 ቀናት እየወሰደ በመሆኑ፣ በተሰጠው የጊዜ ገደብ አስመጪዎች ግዴታቸውን ሊወጡ እንዳላስቻላቸው ተገልጿል፡፡
በመሆኑም አስመጪዎች ምርቱ የታዘዘበትን ቀንና ሙሉ መረጃ ለምግብና መድኃኒት ባለሥልጣንና ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እያቀረቡ፣ ምርቱ ተጓጉዞ የሚገባበትን ቀን ከግምት በማስገባት እንዲስተናገዱ ይደረጋል ተብሏል፡፡
በዚሁ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ባለፈው ሳምንት ለሁሉም ቅርንጫፎቹ እንዳስታወቀው፣ ከባህር ትራንስፖርት ችግር ጋር በተያያዘ ብቻ የዘገዩ መሆናቸው ማረጋገጫ የሚቀርብባቸው የስንዴ ዱቄትና የዘይት ምርቶች እንዲገቡ ተፈቅዷል፡፡
ነገር ግን ከጎረቤት አገሮች ለተፈጸሙ ግዥዎች የባህር ትራንስፖርት ጉዞ ስለሌለ፣ በዚህ ሒደት የማይካተቱ እንደሆነ በጥብቅ አስጠንቅቋል፡፡