ዜና ከራያ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ወገኖች ቁጥር ከ50 ሺሕ በላይ መድረሱ ተገለጸ

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

ቀን: April 24, 2024

በቅርቡ ግጭት ከነበረባቸው የራያ ዞን አካባቢዎች ማለትም ከአላማጣ ከተማ፣ ከራያ አላማጣ፣ ከዛታና ከኦፍላ ወረዳዎች የተፈናቀሉ ወገኖች ቁጥር ከ50 ሺሕ በላይ መድረሱ ታወቀ፡፡ ከአካባቢው አስተዳደር ኃላፊዎች መረጃ አግኝቻለሁ ያለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት፣ 42 ሺሕ ተፈናቃዮች በቆቦ ከተማ ሲጠለሉ 8,300 ያህሉ ደግሞ በዋግህምራ ዞን ሰቆጣ ከተማ እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡

ከተፈናቃይ ወገኖች አብዛኞቹ ሕፃናት፣ ሴቶች፣ አረጋውያንና ወጣቶች እንደሆኑ ያስታወቀው ተመድ የተጠለሉትም ኅብረተሰቡ ውስጥ እንደሆነ ገልጿል፡፡ የተቀሩት ግን ከቆቦ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ ጋራ ሌንጫ በሚባል የኢንዱስትሪ አካባቢ ያለ በቂ መጠለያ ለበልግ ዝናብ መጋለጣቸውን አስታውቋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ የተወሰኑትን ተፈናቃዮች ካሉበት አካባቢ በማንሳት ወደ መጠለያዎች ለማስገባት ሥራ መጀመሩን ከአጋር አካላት መረዳት መቻሉን፣ ጉዳዩን በተመለከተ የተሟላ መረጃ ይፋ የሚደረገው ሙሉ በሙሉ ስለሁኔታው ሲታወቅ መሆኑን ተመድ ገልጿል፡፡

የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች አካባቢውን ከተቆጣጠሩ ወዲህ ከሰኞ ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በአላማጣ፣ በቆቦና በወልዲያ መረጋጋት መፈጠሩንና ከቆቦ አላማጣ፣ እንዲሁም ከአላማጣ እስከ ማይጨው ያለው መንገድ ለትራንስፖርት ክፍት መደረጉ ተገልጿል፡፡

ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች ዝግ ሆነው የቆየው የባንኮች አገልግሎት ሥራ መጀመሩን፣ ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶችም ክፍት እየተደረጉ እንደነበር ማክሰኞ ዕለት ለመረዳት ተችሏል፡፡

ከወልዲያ ወደ ሰቆጣ የሚወስደው መንገድ ለዕርዳታ አቅርቦት አስተማማኝ አለመሆኑን ከረድዔት አጋሮች መረዳቱን ተመድ ጠቁሞ፣ በዚህም ምክንያት የረድዔት ድርጅቶች ሰቆጣ የሚገኙ ተፈናቃዮችን ሁኔታ ለማወቅ እንዳልቻሉ አስታውቋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ከተፈናቃዮች በተገኘ መረጃ ላይ በመመሥረት ከፌዴራል መንግሥትና ከአማራ ክልል ጋር በመሆን ዕርዳታ ማቅረብ መጀመሩን፣ የዕርዳታ አቅርቦቱ ግን እየጨመረ ካለው ፍላጎት ጋር የሚጣጣም እንዳልሆነ አክሏል፡፡

በቅርቡ በአካባቢው በተከሰተው ግጭት የሰዎች ሕይወት ከማለፉም በላይ፣ የአካባቢ መንግሥታዊ መዋቅሮች መፈራረሳቸውንና አመራሮችና ሠራተኞችም እንደ ነዋሪዎች መፈናቀላቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡