ዜና
ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የበጀት እጥረትና የሠራተኞች ፍልሰት ፈተና ሆነውበታል

ናርዶስ ዮሴፍ

ቀን: April 24, 2024

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ሪፖርት 722 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ቢያሳይም፣ የበጀት እጥረት የታቀዱ ግዥዎችን ለመፈጸም አዳጋች እንዳደረገበትና የሠራተኞች ፍልሰት ተግዳሮቶች እንደገጠሙት ታወቀ። 

ባለሥልጣኑ ለሠራተኞቹ አቅርቦ ውይይት የተደረገበት ሪፖርት፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለማሰባሰብ ከታቀደው 300 ሚሊዮን ብር ገቢ አንፃር ከእጥፍ በላይ አፈጻጸም ማስመዝገቡን ያስረዳል። 

ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልን ለአየር መንገዶች ለሚሰጠው በረራዎችን የመምራት (Air Navigation) አገልግሎቱ የሚሰበስበው የታሪፍ መጠን ላይ ከሚያዚያ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ማሻሻያ በማድረጉ፣ በታሪኩ ከፍተኛ የተባለውን ገቢ መጠን ማስመዝገብ መቻሉ ተገልጿል፡፡

በረራዎችን የመምራት አገልግሎት ታሪፍ የኢትዮጵያ አየር ክልልን አቋርጦ ለማለፍም ሆነ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ አርፎ ለመነሳት አየር መንገዶች የሚፈጽሙት ክፍያ ነው። 

የታሪፍ ክፍያው ከውጭ አገር የበረራ አገልግሎት አቅራቢ ድርጅቶች ባለፈ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ ሌሎችም አገር በቀል የአቪዬሽን ተቋማትን ያካትታል። 

ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ኃላፊ ‹‹እስከ 2015 ዓ.ም. ድረስ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ የነበረ የታሪፍ ተመን ነው ሲሠራበት የቆየው፤›› ብለዋል። 

‹‹ትልልቅ ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች መጥተው የሚጠየቁትን ታሪፍ ከአብራሪው ኪስ መውጣት የሚችል መጠን ያህል ከፍለው ነበር የሚሄዱት፣ ታሪፉ በጣም ትንሽ ነበር፤›› ሲሉም የቆየውን አሠራር አስረድተዋል። 

አሁን የተደረገው ማሻሻያ መጠነኛ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነፃፀር አሁንም በጣም አነስተኛ ነው ብለው፣ ‹‹ይህ ደግሞ በአንዴ ከፍ በማድረግ ማስደንገጥ አይገባም በሚል የተደረገ ነው፤›› ብለዋል። 

ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በ2016 ዓ.ም. በጀት ዓመት መጨረሻ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማስገኘት ማቀዱ ታውቋል። 

ይሁንና የመረጃ ልውውጥ ሥርዓቱን የተቀላጠፈ ለማድረግ ወደ የሚያስችል አሠራር ለማሳደግ በተያዘው ዕቅድ ዝርዝር መሟላት ያለባቸው የቴክኒክ መሥፈርቶች (specifications) ቢያዘጋጅም፣ የበጀት እጥረት በመኖሩ በሚቀጥለው በጀት ዓመት ለመግዛት ዕቅዱ መሸጋገሩን ሪፖርቱ ያስረዳል። 

በሌላ በኩል ከፍተኛ የሆነ የሠራተኛ ፍልሰት መኖር፣ ከደመወዝና ከጥቅማ ጥቅም ጋር በተያያዘ የሠራተኞች እርካታ ማነስ፣ እንዲሁም አዳዲስ ባለሙያዎችን ወደ ተቋሙ መሳብ አለመቻል በበጀት ዓመቱ ካጋጠሙ ችግሮች ዋነኞቹ ተብለው በሪፖርቱ ተዳሰዋል።

የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ከሚጠይቀው ኦፕሬሽንና የአስተዳደር ነፃነት አኳያ የባለሥልጣኑ አደረጃጀትና አሠራር የተጣጣመ አለመሆን፣ ሕጋዊ ቁመናና የፋይናንስና አስተዳደር ነፃነት አለመኖር፣ በውጭ አገሮች ለሚከናወኑ የቁጥጥር ተግባራት የጉዞ ፈቃድ አለማግኘት፣ እንዲሁም ባለሥልጣኑ በቂ ተሽከሪካሪዎች ስለሌሉትና ያሉትም ያረጁ መሆናቸው በዝርዝር ከተጠቀሱት ተግዳሮቶች ተጠቃሽ ናቸው።

በሪፖርቱ መሠረት ባለሥልጣኑ አጋጠሙኝ ያላቸውን ችግሮች ለመፍታት አደረግኩት ባላቸው እንቅስቃሴዎች ተጨባጭ ዕርምጃዎች መውሰድ የቻለው የተሽከርካሪ ችግርን ለመቅረፍ፣ በብልሽት  ምክንያት ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት መስጠት የማይችሉትን እንደ አስፈላጊነቱ  በመጠገን አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረጉን የተመለከተው ነው፡፡

የባለሥልጣኑ ሕጋዊ ቁመና፣ ጥናትና የጥቅማ ጥቅም መመርያ ተዘጋጅቶ ለትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ቀርቦ ውሳኔ እየተጠበቀ መሆኑን የሚገልጸው ሪፖርቱ፣ የሚጠበቀው ምላሽ እስኪገኝ ድረስ የሰው ኃይል እጥረቱን ለመቅረፍ አዲስ በፀደቀው መዋቅር መሠረት የሠራተኞች ምደባ የተከናወነ መሆኑን፣ በተወሰኑ የሥራ መደቦች ላይ ሠራተኞች በቋሚነትና በጊዜያዊነት እንዲቀጠሩ መደረጉ ተመላክቷል፡፡