የአግሪቴክ ሲምፖዚየም የተገኙ ተወካዮች

ዜና የአውሮፓ ኅብረት ተግባራዊ ሊያደርግ ያቀደው ሕግ ለአርሶ አደሮችና ለላኪዎች ፈታኝ ይሆናል ተባለ

ሰላማዊት መንገሻ

ቀን: April 24, 2024

የአውሮፓ ኅብረት ቡናን ጨምሮ ወደ አባል አገሮቹ የሚላኩ ሰባት የምርት ዓይነቶች ከደን ጭፍጨፋና መመናመን ነፃ መሆናቸው ሳይረጋገጥ፣ ለግብይት እንዳይቀርቡ የሚከለክል ሕግ አውጥቶ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ ማቀዱ፣ ለገበሬዎችና  በወጪ ንግድ ለተሰማሩ ነጋዴዎች ፈተና እንደሚሆንባቸው ተገለጸ።

ኦርቢት ኢኖቬሽን ሀብ ከዓለም የንግድ ማዕከል (አይቲሲ) አጋር ከሆነው ኤንቲኤፍ ቪ ኢትዮጵያ ቴክ ፕሮጀክትና ከአሜሪካ ቴክኖሎጂ ኮሌጅ በጋራ በመሆን፣ ትናንት ማክሰኞ ሚያዝያ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. ባዘጋጁት የአግሪቴክ ሲምፖዚየም በነበረ የውይይት መድረክ፣ የአውሮፓ ኅብረት ባወጣው ሕግ ምክንያት በአርሶ አደሮችና በላኪዎች ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮች በስፋት ተነስተዋል።

የአውሮፓ ኅብረት ያወጣው ሕግ ሲፈጸም ችግሮች እንዳይፈጠሩ ከአሁኑ ሰፊ ሥራ እንደሚጠይቅ በውይይቱ የተገለጸ ሲሆን፣ ወደ አውሮፓ አገሮች የሚላኩ የግብርና ምርቶች  ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ጠቃሚ በመሆናቸው ተረባርቦ መሥራት እንደሚያስፈልግ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡

የአውሮፓ ኅብረት ያወጣውን ሕግ ለመተግበር እስከ ሁለት ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ በውይይቱ ወቅት ተጠቁሞ፣ አርሶ አደሮች በተገቢው መንገድ ሥልጠና እንዲያገኙ በማድረግ ከደን ጭፍጨፋና መመናመን ነፃ የሆነ የምርት አቅርቦት እንዲኖር መሥራት እንደሚገባ ተገልጿል።

ለረዥም ዓመታት በግብርና ሚኒስቴር የሠሩትና በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት አቶ ፍቅሬ ማርቆስ በመንግሥት በኩል በርካታ ሥራዎች በመሥራት፣ መሻሻል የሚገባቸውን ሕጎች በማሻሻልና የሚመለከታቸው ተቋማት በጋራ በመሆን ሕጉ ተግባራዊ በሚሆንበት ወቅት ለሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሔ ማበጀት ያስፈልጋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ 70 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ በገጠር እንደሚኖርና 85 በመቶ የሚሆነው የግብርና ምርት የሚገኘው  ከአነስተኛ አርሶ አደሮች በመሆኑ፣ ግብርናን በቴክኖሎጂ የተደገፈ በማድረግ የገበያ ተደራሽነት ማስፋት፣  ምርታማነትንና ገቢን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ በውይይቱ ወቅት ተገልጿል።

በአገሪቱ የተበታተነ አሠራር ያለውን የግብርና ዘርፍ በቴክኖሎጂ ማበልፀግ በአውሮፓ ኅብረት የሚተገበረውን ሕግ ጫና ለመቀነስ አንደኛው መፍትሔ መሆን እንደሚችል፣ የዓለም የንግድ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ሳሙኤል ፈቃደ ተናግረዋል።

ለገበሬዎች የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን አጠቃቀም ሥልጠናና ድጋፍ መስጠት፣ የኢኮሜርስ መድረኮችንና የገበያ መዳረሻዎችን በማስተዋወቅ ገበሬዎችን ከሸማቾችና ከንግድ ተቋማት ጋር በቀጥታ ማገናኘት በቴክኖሎጂው የተደገፈ የገበያ መረጃ ሥርዓትና የወቅቱን ዋጋ መረጃ ማግኘት እንዲችሉ ያደርጋል ብለዋል።