ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ

ዜና ከተሰጣቸው ሥልጣንና ኃላፊነት ውጪ በሚንቀሳቀሱ የፀጥታ አካላት ላይ ዕርምጃ መውሰድ ተጀመረ

ፅዮን ታደሰ

ቀን: April 24, 2024

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ ቢሮ፣ ከተሰጣቸው ሥልጣንና ኃላፊነት ውጪ በሚንቀሳቀሱ በርካታ የፀጥታ አካላት ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ መውሰዱን ትናንት ሚያዝያ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ሲያቀርብ አስታወቀ፡፡

የከተማዋ አንዳንድ የፀጥታ አካላት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተገን በማድረግ ሕገወጥ እስራት ስለመፈጸማቸው ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ፣ በአዲስ አበባ ከተማ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ እንደማይደረግ ገልጸው፣ ‹‹ከተማው ውስጥ ጉዳዮች ሲኖሩ በማንኛውም ሰዓት ኦፕሬሽን የመሥራት ሥልጣንና ኃላፊነት ስላለብን፣ የትኛውንም ኃይል መነሻ ያደረጉ ኦፕሬሽኖች ይከናወናሉ፤›› ብለዋል፡፡

ይሁንና የተሰጣቸውን ሥልጣንና ኃላፊነት ያላግባብ በሚጠቀሙ የፀጥታ ኃይሎች ላይ ግምገማዎች በማካሄድ፣ ከእስራት ጀምሮ ከሥራ እስከ ማሰናበት ድረስ ዕርምጃዎች መወሰዳቸውን ኃላፊዋ አስታውቀዋል፡፡ 

ቢሮው የከተማዋን ሰላምና ፀጥታ ለማረጋገጥ በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ከ21 ተቋማት ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራርሞ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተገኙት ውጤቶች በጋራ መሥራት በመቻሉ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በመዲናዋ ለሽብር ተግባር ሊውል የነበረ ከ140 ሚሊዮን ብር በላይ መያዙን የገለጹት፣ የቢሮው የዕቅድ በጀት ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ዳሬክተር አቶ ማስረሻ ሀብቴ ሲሆኑ፣ ይህም ሐሰተኛ ገንዘብና በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ገንዘብን ጨምሮ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከቁማር የተሰበሰበ 1.5 ሚሊዮን ብር በቁጥጥር ሥር አንደዋለ አቶ ማስረሻ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በሕገወጥ መንገድ ለሽብር ተግባር ሊውሉ የነበሩ ከ16 ሺሕ በላይ ተተኳሾችን ጨምሮ፣ ከሥውር ትጥቅ እስከ ትልልቅ መሣሪያዎች መያዛቸውን አስታውቀዋል።

ለሥራ ፍለጋ ወይም በሌሎች ምክንያቶች ወደ ከተማዋ የሚደረገው ፍልሰት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን፣ ከፍልሰተኞች ውስጥም ፀጥታ ለማደፍረስ ተልዕኮ ይዞ የሚገባ መኖሩንና ሁለቱን ለመለየትም ቢሮው ከአዲስ አበባ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን ለመቆጣጠር ጥረት እያደረገ መሆኑን ወ/ሮ ሊዲያ ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን በየትኛውም መንገድ ወደ ከተማዋ የሚገባውን የሰው ኃይል ቁጥር አሁን ባለው አሠራር መሠረት ለመቆጣጠር አዳጋች እየሆነ በመምጣቱ፣ የፌዴራል መንግሥት ከክልሎች ጋር በጋራ መሥራት እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ ለዚህም በሁሉም ክልሎች ያሉ ዕድሎችን ለማስፋት የክልል መንግሥታት ኃላፊነት ሊወስዱ ይገባል ብለዋል፡፡