ዜና
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሁለት ካምፓሶች በፀጥታ ችግር ተዘግተው ተማሪዎች እንዲሸጋሸጉ ተደረገ

ተመስገን ተጋፋው

ቀን: April 24, 2024

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሥር የሚገኙ የዘንዘልማና የሰባታሚት ካምፓሶች በፀጥታ ችግር ምክንያት በመዘጋታቸው የግብርና፣ የጤና፣ የጂኦሎጂና የዲዛስተር ማኔጅመንት ተማሪዎች የፀጥታው ችግር እስኪቀረፍ፣ ከተማ ውስጥ ባሉ ካምፓሶች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማድረጉን ዩኒቨርሲቲው አስታወቀ፡፡

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ ገድፍ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በዘንዘልማና በሰባታሚት ካምፓሶች ውስጥ ይማሩ የነበሩ በርካታ ተማሪዎች ከተማ ውስጥ ያሉ ካምፓሶች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ናቸው፡፡

በዘንዘልማና ሰባታሚት ካምፓሶች አካባቢ የተኩስ ድምፅ በየጊዜው እንደሚሰማ የገለጹት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ በተማሪዎች ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳይደርስ ከአንድ ወር በፊት ወደ ተለያዩ የዩኒቨርሲቲው ካምፓሶች እንዲዘዋወሩ መደረጉን አቶ ብርሃኑ አስረድተዋል፡፡

የሁለቱን ካምፓሶች ተማሪዎች ቁጥር ለጊዜው እንደማያውቁት ገልጸው፣ በከተማዋ የሚገኙ የዩኒቨርሲቲው ካምፓሶች ውስጥ በቂ ቦታ በመኖሩ ተማሪዎቹ ምንም ዓይነት መጉላላት ሳይደርስባቸው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከሁለቱ ካምፓሶች ውጪ በሌሎች ካምፓሶች ላይ ምንም ዓይነት የፀጥታ ችግር እንደሌለ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገልጸው፣ በባህር ዳር ከተማ ካለው አንፃራዊ ሰላም አኳያ በርካታ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው ለመማር መምጣታቸውን አብራርተዋል፡፡

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለተማሪዎች ጥሪ ሲያስተላልፍ ተማሪዎቹ ያለውን የፀጥታ ችግር በመገንዘብ ተመዝግበው ወደ መጡበት መመለሳቸውን በተመለከተ ጥያቄ ቢቀርብላቸውም፣ ስለጉዳዩ ምንም ዓይነት መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡

ከአንድ ወር በፊት በዘንዘልማና በሰባታሚት ካምፓሶች አካባቢ ሌሊት በነበረ ተኩስ ምክንያት፣ ተማሪዎች ዕቃቸውን ሳያወጡ ወደ ተለያዩ ቦታ ሸሽተው እንደነበር የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በወቅቱ ትምህርት ለአንድ ሳምንት ያህል ተቋርጦ ነበር ያሉት ተማሪዎቹ፣ በሁለቱ ካምፓሶች ያለው የፀጥታ ችግር ባለመፈታቱ ፖሊና ፔዳ ካምፓሶች ውስጥ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ከሁለቱ ካምፓሶች ውጪ አለመረጋጋቱ አሁን የተሻለ ቢሆንም፣ አልፎ አልፎም የተኩስ ድምፅ እንደሚሰሙ ተማሪዎቹ አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በርካታ ተማሪዎች በወጣላቸው መርሐ ግብር መሠረት የመጨረሻ ፈተና እየወሰዱ መሆኑን የተናገሩት ተማሪዎቹ፣ የዘንድሮ ተመራቂዎች የምረቃ ቀናቸው መቼ እንደሆነ እስካሁን እንዳልተነገራቸው አክለው ገልጸዋል፡፡

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ባለው የፀጥታ ሁኔታ ምክንያት በጣም ጥቂት ከሚባሉ በስተቀር ብዙዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆናቸውን፣ ነገር ግን የአካባቢው የፀጥታ ችግር እንዴት መቀረፍ አለበት የሚለውን መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አለበት ብለዋል፡፡