ማኅበራዊ በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የተነሳውን ሰደድ እሳት መቆጣጠር አለመቻሉ ተገለጸ

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

ቀን: April 24, 2024

በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበውና በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን  በሚገኘው የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ ከሰባት ቀናት በፊት ሚያዝያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም. የመነሻው ምክንያት ሳይታወቅ የተነሳውን ሰደድ እሳት በቁጥጥር ሥር ማዋል አለመቻል በአካባቢው ነዋሪዎች ሥጋት መፍጠሩ ተገለጸ፡፡

በርካታ ብርቅዬ እንስሳት፣ አዕዋፍና ዕፅዋት በሚገኙበት የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ እሳቱ ከተነሳበት ቀን ጀምሮ የአካባቢው ማኅበረሰብና አመራሮች ለማጥፋት ጥረት ቢያደርጉም መቆጣጠር እንዳልተቻለ ለማወቅ ተችሏል።

የአማራ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዓባይ መንግሥቴ ለመገናኛ ብዙኃን እንደገለጹት፣ የቦታው አቀማመጥ አስቸጋሪ በመሆኑ እሳቱ ጠፋ ሲባል እንደገና ስለሚቀጣጠል በቁጥጥር ሥር ማዋል አልተቻለም፡፡ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይስፋፋና ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆን ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በፓርኩ ውስጥ በተደጋጋሚ እሳት የሚነሳበት ትክክለኛ ምክንያት ምን እንደሆነ ባይደረስበትም፣ ግን በአካባቢው እንስሳቶቻቸውን ለግጦሽ የሚያሰማሩ ነዋሪዎች ፓርኩን በባለቤትነት እንዲጠብቁ ለማድረግ የሚሠራው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ የተዳከመ ስለሆነና በፓርኩ አካባቢ የነበሩ ማኅበረሰቦች ወደ ሌላ ቦታ እንዲሰፍሩ ከተደረገ በኋላ ቃል የተገባላቸው ማቋቋሚያ አለመፈጸሙ የፈጠረው ቁጣ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል፣ ኃላፊው  ግምታቸውን ተናግረዋል።

ቃጠሎው በአካባቢው በሚገኘው የጓሳ ሳርና የተለያ አገር በቀል ዕፅዋት ላይ መጠኑ ያልታወቀ ጉዳት ያደረሰ ቢሆንም፣ በዱር እንስሳት ላይ ግን የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ተጠቁሟል፡፡

ኃላፊው እንዳብራሩት፣ ከፓርኩ አካባቢ ተነስተው አምባራስ የሚባል አካባቢ ላይ ሰፍረው የነበሩ ከ100 በላይ አባወራዎችን በኢኮኖሚ ለማቋቋም የሚውል ወደ 60 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ ከአራት ዓመታት በፊት ቃል ተገብቶ የነበረ ቢሆንም፣ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ቃል የተገባውን ገንዘብ መሰብሰብ ባለመቻሉ ተፈጻሚ ባለመሆኑ፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ጥያቄና ቅሬታ መፍጠሩንና በተደጋጋሚ በፓርኩ የሚነሳውን እሳትም በዘላቂነት ለመቆጣጠር አንዱ እንቅፋት ሆኗል፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ ፓርኩ በመግባት ከሰል በማክሰልና ንብ በማነብ የተሰማሩ ግለሰቦች የሚያያይዙት እሳት ለፓርኩ መቃጠል እንደ አንድ ምክንያትም ሊጠቀስ እንደሚችል፣ ወይም ማኅበረሰቡን እረፍት ለመንሳት ሊሆን እንደሚችል  ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡