ፖለቲካ

ሲሳይ ሳህሉ

April 24, 2024

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት በጋራ ያቀረቡትን ምክረ ሐሳብ ተከትሎ፣ የሽግግር ፍትሕ ሥርዓት ለመዘርጋት ታምኖበት ወደ ሥራ ከተገባ ከአንድ ዓመት በላይ ተቆጥሯል፡፡

የሽግግር ፍትሕ በአገሪቱ ለዘመናት የተፈጸሙና አሁንም የቀጠሉ ያልጠሩ ትርክቶች፣ ቁርሾዎች፣ አለመተማመኖች፣ የእርስ በርስ ግጭቶችና የሰላም ዕጦቶች፣ አለመረጋጋቶችና እነዚህን አስታከው የሚፈጸሙ ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ችግሮችን ዘላቂ መፍትሔ በመስጠት ሁሉ አቀፍ ፍትሕ ለማስፍን እንደሚረዳ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

በታኅሳስ 2015 ዓ.ም. በፍትሕ ሚኒስቴር የተዋቀረው 15 የባለሙያዎች ቡድን የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አቅጣጫ አማራጮች ሰነድ በማዘጋጀት፣ በየካቲት 2015 ዓ.ም. የጀመረውን ሕዝባዊ ምክክርና የግብዓት ማሰባሰብ ሥራዎችን አጠናቆ መስከረም 2016 ዓ.ም. ይፋ አድርጎ ነበር፡፡

የባለሙያዎች ቡድኑ በምክክሩ ወቅት በሕዝብ አስተያየት ግብዓቶች የተገኙ ዋና ዋና ግኝቶችንና  የራሱን ምክረ ሐሳብ  ይፋ ባደረገበት ወቅት፣ ክስ የመስማትና ውሳኔ የመስጠት ተግባር ያለውና በሽግግር ፍትሕ የሚታዩ ጉዳዮችን የሚዳኝ ልዩ ፍርድ ቤት እንዲቋቋም ሐሳብ ቀርቦ ነበር፡፡ በምክረ ሐሳቡ እንደተብራራው ጉልህ በሆኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ወይም ወንጀሎች ላይ ያተኮረ የክስ ሒደት ሊኖር እንደሚገባ፣ የምርመራና የክስ ሒደቶችን የሚያስተባብርና ልዩ ነፃና ገለልተኛ የምርመራና የክስ ሥራ የሚያከናውን ተቋም እንዲቋቋም ሐሳብ መቅረቡ አይዘነጋም፡፡

በተጨማሪም እውነታን የማፈላለግና የዕርቅ ሥራ ወይም ሒደት የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ውክልናና ተሳትፎ ባረጋገጠ መንገድ በሚመሠረት አዲስ የእውነት አፈላላጊ ተቋም አማካይነት እንዲካሄድ፣ ከፍተኛ ደረጃ ተሳትፎ ባላቸው አጥፊዎች ላይ ያተኮረ የክስ ሒደት ሊኖር እንደሚገባና ምሕረት የመስጠት ኃላፊነትን በሚመለከት አዲስ በሚቋቋም የ‹‹ሀቅ›› አፈላላጊ ኮሚሽን አማካይነት ሊሆን እንደሚገባም ቡድኑ ምክረ ሐሳቡን አቅርቦ ነበር፡፡

በባለሙያዎች ቡድኑ ምክረ ሐሳብና በተሳታፊዎች የውይይት ውጤት መነሻ በማድረግ፣ ባለፉት ጥቂት ወራት በፍትሕ ሚኒስቴር ረቂቅ ፖሊሲው ተዘጋጅቶ ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. የሚኒስትሮች ምክር ቤት አፅድቆት ከዚያን ቀን ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡  የመጨረሻውና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከተወያየበት በኋላ ተስተካክሎ የፀደቀው የፖሊሲው ሰነድ ይህ ዘገባ እስኪዘጋጅ ድረስ ለሕዝብ ይፋ አልተደረገም፡፡

ይሁን እንጂ ከፍትሕ ሚኒስቴር ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የተላከው ረቂቅ የፖሊሲ ሰነድ እንደሚያሳው፣ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ተግባራዊ የሚደረግበት የጊዜ ወሰን ለወንጀል ተጠያቂነት የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ከፀደቀበት 1987 ዓ.ም. ጀምሮ ሲሆን ለእውነት ማፈላለግ፣ ዕርቅ ማስፈንና ለማካካሻ ሥራዎች ዓላማ መረጃና ማስረጃ እስከተገኘ ድረስ መሄድ እንደሚችል በፖሊሲው ተገልጿል፡፡

በመላ አገሪቱ ተፈጻሚ ይሆናል በተባለው በዚህ የፖሊሲ ሰነድ በጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ብቻ ያተኮረ ምርመራና ክስ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን፣ ለዚህም ከባድ ወንጀሎችን መለየት የሚያስችል ግልጽ መለያ መሥፈርት ይዘረጋል ይላል፡፡ በቀጣይ ለፖሊሲው ማስፈጸሚያ የሚሆኑ አዋጆችን ጨምሮ አስቻይ የሆኑ ሕጎችና የአሠራር ማዕቀፎች እንደሚዘጋጁ፣ ፖሊሲውን የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚከናወን፣ ተቋማት በሕግ እንደሚቋቋሙና ለሥራው ተገቢው ድጋፍና ሀብት እንደሚሰባሰብ ተመላክቷል፡፡

በአገሪቱ የወንጀል ሕግ ውስጥ ያልተካተቱ ዓለም አቀፍ ወንጀሎችን በተመለከተ፣ አገሪቱ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር በተጣጣመ መንገድ አዲስ የሕግ ማዕቀፍ እንዲዘጋጅም ይደረጋል ይላል ሰነዱ፡፡

በአጥፊዎች ላይ የወንጀል ሙሉ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ እንዲቻል ያለመከሰስ መብት ተፈጻሚነት እንዳይኖረው የሚደረግ ሲሆን፣ በአገር ውስጥ የማይገኙ ከፍተኛ ደረጃ የወንጀል ተሳትፎ ያላቸው አጥፊዎች ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ከሚገኙበት አገር ተላልፈው እንዲሰጡ ለማድረግ ተገቢ ሥራ ይከናወናል ይላል፡፡

በሽግግር ፍትሕ ሒደት የሚከናወነው የወንጀል ምርመራና ክስ የመመሥረት ተግባር አሁን ካለው የወንጀል ምርመራና ዓቃቤ ሕግ ተቋም ውጪ፣ ነፃና ገለልተኛ ሆኖ ራሱን ችሎ በሚቋቋምና የሕዝብ አመኔታ በሚኖረው አዲስ ልዩ ዓቃቤ ሕግ ተቋም አማካይነት እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡

የሚቋቋመውን የልዩ ዓቃቤ ሕግ ተቋም አመራሮች ምልመላና ሹመት ግልጽ፣ አካታች፣ አሳታፊና ብዝኃነትን በማማከል የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ ሰብዓዊና ዴሞክራቲክ ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ እንደሚፈጸም ለምክር ቤቱ በቀረበው ሰነድ ተብራርቷል፡፡

በሽግግር ፍትሕ ሒደት የወንጀል ተጠያቂነት ሥራ የታለመውን ግብ እንዲያሳካ ለማድረግ ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች የተለየ የራሱ አደረጃጀት የሚኖረው፣ ነፃና ገለልተኛ ልዩ ፍርድ ቤት በሕግ እንደሚቋቋም በቀረበው የፖሊሲ ሰነድ ተቀምጧል፡፡

ይሁን እንጂ (ልዩ ፍርድ ቤትን) መቋቋም ሕገ መንግሥታዊነትን አስመልክቶ የሚነሱ ጥያቄዎች ላይ፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ እንዲቀርብ ይደረጋል ይላል።  

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የልዩ ፍርድ ቤት መቋቋምን ሕገ መንግሥታዊነት የሚያፀና ከሆነ ልዩ ፍርድ ቤት እንደሚቋቋም፣ ውሳኔው ከዚህ የተለየ ከሆነ ደግሞ በልዩ ችሎት አደረጃጀት የዚህን ፖሊሲ ዓላማ ለማሳካት እንደሚሠራ ተመልክቷል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 79 እንደተደነገገው የዳኝነት ሥልጣንን ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች ወይም በሕግ የመዳኘት ሥልጣን ከተሰጠው ተቋም ውጪ የሚያደርግ በሕግ የተደነገገ የዳኝነት ሥልጣን የማይከተል ልዩ ፍርድ ቤት ወይም ጊዜያዊ ፍርድ ቤት አይቋቋምም ይላል፡፡

የልዩ ፍርድ ቤቱን ነፃነት፣ ገለልተኛነትና ተዓማኒነት ለማሳደግ፣ እንዲሁም አገር አቀፋዊና ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነቱን ለማጠናከር የውጭ ባለሙያዎች በአማካሪነትና በአሠልጣኝነት እንደሚሳተፉበት ተገልጿል፡፡

እውነትን የማፈላለግ ሒደት ሥልጣን የሚኖረው የሀቅ አፈላላጊ ኮሚሽን እንደሚቋቋም የተጠቀሰ ሲሆን፣ የሚቋቋመው ኮሚሽን ምሕረት የመስጠት፣ የማካካሻ ሥራን የማከናወን ተደራቢ ኃላፊነት እንደሚኖረውና ኮሚሽኑ የማካካሻ ሥራዎችን የሚመራ መዋቅር በሥሩ እንደሚያደራጂ ተቀምጧል፡፡

የፍትሕ ሚኒስቴር ፖሊሲው በትክክል ወደ መሬት ወርዶ ተግባራዊ የሚሆንበትን ዝርዝር አካሄድ የሚመራ ‹የፖሊሲ አፈፃፀም ፍኖተ ካርታ› የሚያዘጋጅ ሲሆን፣ በፍኖተ ካርታው ፖሊሲው ከፀደቀ በኋላ የሚከናወኑ ተግባራት በዝርዝር ምን እንደሆኑ፣ ቅደም ተከተላቸውን፣ መቼ እንደሚከናወኑ፣ ማን እንደሚያከናውናቸውና በዚህ ፖሊሲ ላይ የተመለከቱ አካላት ተግባርና ኃላፊነት ምን እንደሆነ የሚያመላክት ስለመሆኑ ተብራርቷል፡፡

 የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲውን አፈጻጸም የሚዳኝ ፍርድ ቤት ማቋቋምን በተመለከተ በርካታ አስተያየቶች ሲሰጡ ይደመጣል፡፡ ለአብነት በአመዛኙ ከሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎችና ተቋማት፣ እንዲሁም ከትግራይ ክልል በተለይ ልዩ ፍርድ ቤትም ሆነ ልዩ ችሎት ቢቋቋምም፣ በትግራይ በነበረው ጦርነት በኤርትራ ወታደሮች ተፈጸሙ የሚሏቸውን ወንጀሎች ዓለም አቀፍ በሆነ ተቋምና ሕግ እንዲዳኙ እንፈልጋን ሲሉ ይደመጣሉ፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ‹‹በጦር ወንጀልና ከባድ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የተሳተፉ›› የኤርትራ ወታደሮች ጉዳይ በሌሉበትም ቢሆን፣ በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው በሚቋቋም ልዩ ፍርድ ቤት ሊታይና ተጠያቂነታቸውም ሊረጋገጥ ይገባል ሲሉ ሰባት የመብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች ከአንድ ወር በፊት ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ ድርጅቶቹ በመግለጫቸው በውጭ ኃይሎች የተፈጸሙ ከባድ ወንጀሎች ይፋ ሊደረጉ፣ እውነቱ ሊታወቅና ሊሰነድ ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

በሌላ በኩል ልዩ ፍርድ ቤት ስለማቋቋም የቀረበውን የሕግ ባለሙያዎች ምክረ ሐሳብ፣ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚፃረር መሆኑንና ልዩ ችሎት ማቋቋምን በተመለከተ ደግሞ በልዩ ችሎት የሽግግር ፍትሕ ያለመውን ዓላማ ማስፈጸም አይታሰብም የሚል አስተያየት ሲሰጡ ይደመጣሉ፡፡

የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አቅጣጫ አማራጮችን ይፋ ሲደረግ በሽግግር ፍትሕ የሚታዩ ጉዳዮችን የሚዳኝ ልዩ ፍርድ ቤት በማቋቋም፣ ክስ የመስማትና ውሳኔ የመስጠት ተግባር ማከናወን የሚችል አማራጭ ምክረ ሐሳብ፣ ከሕዝባዊ ምክክር ተሳታፊዎችና ከሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች ቡድን መቅረቡ ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ከቀረበው ሰነድ ውስጥ ልዩ ፍርድ ቤት እንዲቋቋም በባለሙያዎች ቡድን ቀርቦ የነበረው ምክረ ሐሳብ፣ ልዩ ችሎት ይቋቋም በሚል እንዲተካ መደረጉን ሪፖርተር ከምንጮች ለማወቅ ችሏል፡፡

 የሕግ ባለሙያና  የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት፣ እንዲሁም የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ አማኑኤል አሰፋ በግላቸው ለሪፖርተር በሰጡት አስተያያት፣ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ከተቀረፀበት ጀምሮ አሁን የደረሰበት ደረጃ ሲታይ የታለመለትን ዓላማ በተለይም ሰላምና ፍትሕን በሚያመጣ መንገድ አይደለም ይላሉ፡፡ ለዚህ እንደ ምክንያት ያቀረቡት ከፖሊሲው ዕሳቤ ጀምሮ የባለሙያ ቡድኑ ያቀረበውን ምክረ ሐሳብ ተቀብሎና ወደ ሕግ  ቀይሮ በማፅደቅ ወደ ሥራ ለመግባት እየተንደረደረ ያለው የፌዴራል መንግሥት በብቸኝነት መሆኑን ነው፡፡

አቶ አማኑኤል ‹‹በሕግ ቋንቋ ራሱ አጥፊ ራሱ ዳኛ መሆን አይቻልም›› ይላሉ፡፡ ነገር ግን በትግራይ ጦርነት ‹‹የጅምላ ጭፍጨፋ›› እና መሰል ከባድ ወንጀሎች በተለይም ለወንጀሉ መፈጸም የፌዴራል መንግሥት ጠርቶ ያስገባቸው የኤርትራ ወታደሮች ተሳትፈውበት ብዙ ወንጀል ተፈጽሞ እያለ ፖሊሲውን ማርቀቅም፣ ማፅደቅም፣ መክሰስም፣ ፍርድ ማስፈጸምም የፌዴራል መንግሥት በመሆኑ ፍትሕን አያረጋግጥም ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የሽግግር ፍትሕ አስፈላጊነት ላይ እምነት እንዳላቸው የሚናገሩት አቶ አማኑኤል፣ ነገር ግን ይህን ለማድረግና ውጤት ለማምጣት ከተፈለገ አሁን እየተፈጸሙ ያሉ ወንጀሎችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መቆም እንደሚገባቸውም ያስረዳሉ፡፡

በትግራይ ክልል ሁለት ሚሊዮን ዜጎች መፈናቀላቸውና ወደ መኖሪያቸው ሳይመለሱ ወደ ሥራ ቢገባ፣ መፍትሔ ሊያመጣ እንደማይችልና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ባልቆመበት የሽግግር ፍትሕ እተገብራለሁ ማለት ‹‹ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ›› ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የፖሊሲውን የተፈጻሚነት ጉዳይ በተመለከተ በኢትዮጵያ የተዘጋጀው ፖሊሲ የሚፈጸመው በአገር ውስጥ ሕግ ሲሆን፣ በትግራይ ክልል ተፈጸሙ የተባሉ ‹‹ጭፍጨፋዎችና ወንጀሎች›› ደግሞ ከኢትዮጵያ ውጪ ባሉ የኤርትራ ሠራዊት የተፈጸሙ በመሆናቸው፣ በአገር ውሰጥ አሠራር ብቻ ፍትሕን መጠበቅ ሒደቱን ሰባራ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ፍትሕና ሰላም ለማምጣት ከተፈለገ ዓለም አቀፍ ወንጀሎች በዓለም አቀፍ ሕጎችና አሠራር መሠረት መታየት አለባቸው ያሉት አቶ አማኑኤል፣ ዓለም አቀፍ አሠራሮችና ተቋማት በሌሉበት ልዩ ፍርድ ቤትም ሆነ ልዩ ችሎት መቋቋሙ፣ ሁለቱም ከስም ያለፈ በፌዴራል መንግሥት ቁጥጥር ሥር የሚኖሩ አካላት ናቸው ብለዋል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያዊንም ሆኑ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሊተማመኑበት የሚችል፣ የፍርድ ሒደቱን ፍትሐዊ የሚያደርግ፣ የሕግ የበላይነትን የሚያረጋግጥ፣ ለሕዝቦች ዘላቂ ሰላም የሚያመጣ አሠራር ካልተዘረጋ የሆነ አካል ሥልጣን ላይ ሲወጣ  ብቻ ደስ የሚለውን አድርጎ እንደሚሄድ፣ ሌላው ሲመጣ ደግሞ እንዲሁ እያደረገ የሕዝቡ ሥቃይ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ አንድ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ የሆኑ ግለሰብ ስለዚሁ ጉዳይ ለሪፖርተር ሲያብራሩ፣ በክልሉ በብዘዎች ዘንድ የሽግግር ፍትሕ በተጨባጭ ለውጥ ያመጣል የሚል እምነት የለም ይላሉ፡፡ ነፃና ገለልተኛ አካል በሌለበት አገር ‹‹ጉለሌ የሚገኝ ችሎት›› ሄደህ ፍትሕን አገኛለሁ ማለት አይቻልም ብለዋል፡፡ የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በትግራይ ክልል የፈጸሙት ‹‹ወንጀል›› በዚህ መንገድ ፍትሕ ያገኛል ማለት ጨዋታ ነው ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ የሽግግር ፍትሕ ዋና ምክንያትና መነሻ በትግራይ ክልል የነበረውን ጦርነት በሰላም ለመፍታት የተደረገውን የፕሪቶሪያ ስምምነት ተከትሎ በቀረበው ምክረ ሐሳብ እንጂ፣ ከ1987 ዓ.ም. ተብሎ የመጣው ዕሳቤ 1987 ዓ.ም. የነበረው ሁኔታ ራሱን የቻለ የሕገ መንግሥት ጉዳይ ሆኖ ሌላ አጀንዳ ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም የሽግግር ፍትሕ አስፈላጊነት ከትግራይ ክልል ጦርነት ጋር የተያያዘ  በመሆኑ፣ መነሻውም እሱ ላይ ሆኖ መተማመንና መግባባት ተደርሶበት በገለልተኛ ተቋም እንዲታይ መደረግ አለበት በማለት ያስረዳሉ፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ አበባው ደስአለው፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተባብሶ ወደ ሽግግር ፍትሕ ተገባ ማለት የታሰበውን ውጤት ማምጣት እንደማይቻል ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጭምር የት እንደታሰሩ እንኳ በማይታወቅበት ሁኔታ፣ ብሔር ተኮር የመብት ጥሰት እየተፈጸመ ይህ ችግር ሳይፈታና የመቆጣጠሪያ ሥርዓት ሳይዘረጋለት፣ ችግሩን ወደፊት በሽግግር ፍትሕ እናስቆመዋለን ማለት ከፈረሱ ጋሪውን እንደማስቀደም ተደርጎ የሚቆጠር ነው የሚሉት አቶ አበባው፣ ለመሸጋገር እኮ ሰላም አስፈላጊ ነው ይላሉ፡፡

በሌላ በኩል የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽሟል የሚባለው መንግሥት ሆኖ እያለ ራሱ ተቋሙ የሚያቋቁም ከሆነ የገለልተኛነቱ ጉዳይ አጠያያቂ ይሆናል ያሉት አቶ አበባው፣ በዚህ የገለልተኝቱ ጥያቄ ወደ ሥራ ቢገባ ሕዝቡም በቀጣይ የሰብዓዊ መብት ይጠበቅብኛል በሚል እምነት ሊያሳድር እንደማይችል ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ጠንካራ፣ ከልብ የሚሠሩና ገለልተኛ ተቋማት በእጅጉ ያስፈልጋሉ ብለዋል፡፡

ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ኢትዮጵያ ምክትል ዳይሬክተር አቶ መብርሂ ብርሃነ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ድርጅታቸው የተጠያቂነትን ጉዳይ ቢያንስ በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ተቋማት አማካይነት እንዲደራጅ የሚል ምክረ ሐሳብ አቅርቦ ነበር፡፡ ድርጅታቸው ባቀረበው  ቅይጥ ተጠያቂነት ሥርዓት አማካይነት ከፍተኛ ወንጀል የፈጸሙ በዓለም አቀፍ አሠራር በዝቅተኛ ወንጀል የሚጠየቁትን በአገር ውስጥ ሥርዓት እንዲያልፍ በማድረግ፣ ውጤታማ የሆነ ሥራ የሚቻል መሆኑን ያምንበታል ይላሉ፡፡ ይህ ባልሆነበት ግን የአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ የሚንፀባረቅበት ሒደት ይሆናል ብለዋል፡፡

የኤርትራ ወታደሮች የፈጸሙትን ወንጀል በኢትዮጵያ ሕግ ፍርድ እሰጣለሁ ሲል በፖሊሲው መሠረት የይስሙላ ጉዳይ እንደሚሆን የገለጹት አቶ መብርሂ፣ በዓለም አቀፍ ሕጎችና ተቋማት አማካይነት የማይተገበር ከሆነ በሁለት አገሮች መካከል ያለን ጉዳይ በአንድ አገር የውስጥ ሕግ ለመፍታት የማይቻል ቅዥት ነው ይላሉ፡፡

በአፍሪካ ሕገ መንግሥት ጉዳዮች ዳኞች ኔትወርክ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ካሴ (ዶ/ር) በዚህ ጉዳይ ላይ ለሪፖርተር ሲያስረዱ፣ ብዙውን ጊዜ የገለልተኝነት ጉዳይ የሚነሳው ፍርድ ቤቶች ካለባቸው ጫና፣ አቅምና ተፅዕኖ አንፃር ሊሰጡት የሚችሉት ውሳኔ ጥያቄ ውስጥ ሊገባ ስለሚችል ነው ብለዋል፡፡

አንድ ተራ የወንጀል ጉዳይና ከባባድ ወንጀሎችን ማየት ከሕግ ብቻ ሳይሆን ከታሪክም ጋር ሊገናኝ የሚችል በመሆኑ፣ በመሠረታዊነት የሽግግር ሒደቱ ምሉዕ ይሁን ከተባለ ገለልተኛ ፍርድ ቤት ኖረም አልኖረም የፖለቲካ ቁርጠኝነት ትልቁ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡  

ከዚህ በተጨማሪ ራሱን የቻለ ፍርድ ቤት ተቋቁሞ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ የሚያስፈጽመው ፖሊስና የመርማሪው ዓቃቤ ሕግ ነፃነት ካልተወሰነ፣ የፍርድ ቤት ነፃ መሆን ብቻ ብዙ ለውጥ የሚያመጣ አይደለም ብለዋል፡፡ ነገር ግን ቁርጠኝነቱ ካለ ባሉት ፍርድ ቤቶች ውጤት ማምጣት የሚቻልበት ሁኔታ እንደሚኖር አክለዋል፡፡

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ውጤታማነት መሳካት ራሱን የቻለ ወይም ያልቻለ፣ ፍርድ ቤት ከመሆንና ካለመሆን ጋር እንደማይገናኝ የገለጹት አደም (ዶ/ር)፣ የፖሊሲውን ውጤታማነት የሚወስኑት በመሬት ላይ የተመሠረተው ፍትሕ የማስፈን፣ ፖለቲካውን የማቅናት፣ በመንግሥት ውስጥ ቁርጠኝነት መኖሩና ያለመኖር ጉዳይ ናቸው ብለዋል፡፡ እንዲሁም አሁን የሕግ የበላይነት ችግር ውስጥ በመግባቱ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ወደ ሥራ ገብቶ ይፈጸም ከተባለ አገራዊ ሁኔታውም መሻሻል ይኖርበታል ሲሉ አስረድተዋል፡፡