በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሊሽማኒያሲስ ምርምርና ሕክምና ተቋም ተመራማሪዎች

ማኅበራዊ ካላዛርን ለማከም የተሠራው መድኃኒት በሰዎች ላይ መሞከር ተጀመረ

ምሕረት ሞገስ

ቀን: April 24, 2024

የካላዛር ሕሙማንን ለማከም ለ17 ቀናት የሚሰጠውን የመርፌና የእንክብል መድኃኒት ሙሉ ለሙሉ በእንክብል ብቻ ለመተካት የሚያስችለው መድኃኒት፣ በሰዎች ላይ መሞከር መጀመሩን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሊሽማኒያሲስ ምርምርና ሕክምና ተቋም ተባባሪ ተመራማሪ እሌኒ አየለ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

እሌኒ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በምርምሩ 15 የጤና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ሲሆን፣ የዕድሜ ክልላቸው ከ18 እስከ 44 በሚደርሱ 52 ፈቃደኛ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚደረገው የመድኃኒት ሙከራ ምርምር ተጀምሯል፡፡

በኢትዮጵያ በዓመት ከ2,000 እስከ 3,000 ሰዎች በካላዛር በሽታ ይያዛሉ ተብሎ እንደሚታመንና ሥርጭቱ በረሃማ አካባቢ ላይ እንደሚጨምር ያስታወሱት እሌኒ (ዶ/ር)፣ በበሽታው ተይዘው ሕክምና ካላገኙት ውስጥ 95 በመቶ ያህሉ እንደሚሞቱ ጠቁመዋል፡፡

እንደ ወባ ዓይነት ባህሪ ያለውና በገዳይነቱ የተመዘገበው ካላዛር፣ ትኩሳት በማስከተል፣ ጣፊያ በማሳበጥ፣ የደም ሴሎችን በመጉዳት፣ ኢንፌክሽን በመፍጠርና በማድማት ሰዎችን ለሞት የሚዳርግ የውስጥ ደዌ በሽታ መሆኑንም አክለዋል፡፡

በዚህ ገዳይ በሽታ የተጠቁትን ለማከም በሰዎች ላይ የተጀመረው እንክብል ውጤታማ ከሆነ፣ ሕሙማን እንደከዚህ ቀደሙ ረዥም ርቀት ተጉዘውና ለ17 ቀናት ሐኪም ቤት ተኝተው የሚወስዱትን ሕክምና የሚያስቀር ይሆናል፡፡ በየአካባቢያቸው በሚገኙ ጤና ጣቢያዎችም መድኃኒት መውሰድ የሚችሉበትን ሁኔታ የሚፈጥር ነው፡፡

ፈውስ ትኩረት ለተነፈጉ በሽታዎች ኢኒሺዬቲቭ (Drugs for Neglected Diseases Initiative DNDI) እና በአጋሮቹ አማካይነት በኢትዮጵያና በህንድ እየተደረገ የሚገኘው አዲሱ የካላዛር ሕክምና ምርምር፣ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና በሽታውን ለማጥፋት ካስቀመጠው አቅጣጫ ጋር የተጣጣመ እንዲሁም ትኩረት የተነፈገውንና ለማከምም አስቸጋሪ የሆነውን የካላዛር በሽታ ለማዳን ለሚደረገው ርብርብ ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣትም ያግዛል ተብሏል፡፡   

በኢትዮጵያ በምርምር ላይ የሚገኘው አዲሱ የ“LXE408” በአፍ የሚወሰድ መድኃኒት አሁን ከሚሰጠው ሕክምና የበለጠ ፈዋሽና አስተማማኝ ያደርገዋል የሚል እምነት ተጥሎበታል፡፡

እንደ እሌኒ (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ ያሉት የካላዛር ሕክምና አማራጮች ከፍተኛ ውስንነት ያለባቸው፣ ጎጂ ክትባትን ግዴታ የሚያደርጉና እጅግ ቀዝቃዛ የሕክምና ቁሳቁሶች ጥቅም ላይ የሚውሉባቸው ናቸው፡፡

በምርምር ላይ የሚገኘው ሕክምና ፈዋሽ፣ የጎንዮሽ ጉዳቱ አነስተኛና ሕሙማን በመኖሪያ ቤታቸው አቅራቢያ በሚገኙ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ተቋማት የሚያገኙት ነው፡፡

የምርምሩ ውጤታማ መሆን ሕክምናው ባስፈለገበት ጊዜ ሁሉ ታካሚዎች በቀላሉ እንዲያገኙት ከማስቻሉም ባሻገር፣ የበሽታውን ሥርጭትና ጉዳት ይቀንሳል። ከምንም በላይ በሽታውን እስከወዲያኛው ለማስወገድ የሚደረገውን ጥረትም ያግዛል፡፡

በሽታውን በዘላቂነት ከመላው ዓለም በተለይም የችግሩ ተጠቂ ከሆኑት የአፍሪካ አገሮች ለማስወገድ አዳዲስ ሕክምናዎችን ማግኘት እንደሚያስፈልግና አዲሱ ክሊኒካዊ ሙከራ የተሻለ፣ ለታካሚ ተስማሚ፣ ለሁሉም ሰው ተደራሽ መድኃኒቶችን ለማስገኘት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው በዲኤንዲ አይ የካላዛር ፕሮግራም ዳይሬክተር ፋቢያና አልቬዝ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

የቅድመ ክሊኒካዊ ምርምርንና የመጀመሪያ ደረጃ ጥናትን የማጠናቀቅ ብሎም የኬሚካል ምርትና ቁጥጥር ሥራውን ኃላፊነት ወስዶ እየሠራ የሚገኘው ኖቫርቲስ ሲሆን፣ ምርመሩ ውጤታማ ሆኖ መድኃኒቱ የገበያ ፈቃድ ካገኘም የተጠቃሚውን አቅም ባገናዘበ ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያቀርብ ይሆናል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ተመራማሪና የካላዛር በሽታ መከላከል ተጠሪ ሳውራብ ጃይን (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በዋናነትም ሕፃናትን የሚያጠቃው ካላዛር በሽታን ለማስወገድ የሚያስችለውን ምርምር ማሳካት፣ የበሽታው ተጠቂ የሆኑትን ማኅበረሰቦች ከድህነት ለማውጣትም እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

ካላዛር በአሸዋ ዝንብ ንክሻ የሚተላለፍ ሲሆን፣ በምሥራቅ አፍሪካ፣ ደቡብ እስያና ደቡብ አሜሪካ በሚገኙ 80 አገሮች ውስጥ ተንሰራፍቷል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለዚህ በሽታ የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር አንድ ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ አብዛኞቹ ሕሙማንም በምሥራቅ አፍሪካ ይገኛሉ።

የአየር ንብረት ለውጥ የካላዛር በሽታን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት በማወክ በሽታው እስካሁን ወዳልተዳረሰባቸው ቦታዎች እንዲስፋፋ እያደረገ ነው፡፡ በዓለምም በየዓመቱ ከ50,000 እስከ 90,000 የሚደርሱ ሰዎች በካላዛር ይይዛሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ገሚሱ  ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ናቸው፡፡

ከምሥራቅ አፍሪካም ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳንና ኡጋንዳ ከፍተኛውን የሕሙማን ቁጥር እንደሚይዙ በተለያዩ ጊዜያት የተሠሩ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡