የፍልስጤም ባንዲራ
የምስሉ መግለጫ,የፍልስጤም አስተዳደር ከ2012 ጀምሮ በተባበሩት መንግሥታት የታዛቢነት ደረጃ ተሰጥቶታል

ከ 5 ሰአት በፊት

ባለፈው ሳምንት የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ፍልስጤም የድርጅቱ ሙሉ አባል ለመሆን ባቀረበችው ጥያቄ ላይ ድምፅ ሰጥቷል።

ዩናይትድ ስቴትስ ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣኗን ተጠቅማ ይህን ጥያቄ ውድቅ ብታደርገውም 12 የምክር ቤቱ አባላት ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።

ከእነዚህ አገራት መካከል የአሜሪካ አጋር የሆኑት ፈረንሳይ፣ ጃፓን እና ኮሪያ ይገኙበታል። ዩናይትድ ኪንግደም እና ሰዊትዘርላንድ ድምፀ ተዐቅቦ መርጠዋል።

የፍልስጤም አገዛዝ ፕሬዝዳንት ሞሐሙድ አባስ የአሜሪካ እርምጃ “ሥነ-ምግባር የጎደለው” ነው ሲሉ እስራኤል ደግሞ ውሳኔውን አሳፋሪ ነው በማለት የአሜሪካን እርምጃ አወድሳለች።

ድምፅ የተሰጠው በምን ጉዳይ ላይ ነው?

የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ፍልስጤም የመንግሥታቱ ድርጅት ሙሉ አባል ለመሆን ባቀረበችው ጥያቄ ላይ ነው ድምፅ የሰጠው።

15 አባል አገራት ያሉት የፀጥታው ምክር ቤቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ድምፅ አንዲሰጥ የተጠየቀው ከአልጄሪያ በቀረበው ጥያቄ መሠረት ነው።

አልጄሪያ 193 አባል አገራት ላሉ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላይ ጉባዔ “የፍልስጤም አስተዳደር የተባበሩት መንግሥታት አባል መሆን አለባት” ስትል ጥያቄ አቅርባለች።

አምስት አገራት የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባላት ናቸው። አምስቱም አገራት ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት አላቸው። 10 አገራት ደግሞ በምክር ቤቱ ያላቸው መቀመጫ ጊዜያዊ ነው።

አሜሪካ የእስራኤል የረዥም ጊዜ አጋር ናት። አሜሪካ የፀጥታው ምክር ቤት ያቀረውን ጥያቄ ውድቅ አድርጋለች። የምክር ቤቱ ውሳኔ የሚያልፈው አምስቱም ቋሚ አባላት ሲስማሙበት፣ አሊያም ድምፅን የመሻር መብታቸውን ሳይጠቀሙ ሲቀሩ ነው።

ዩናይትድ ስቴትስ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ሩሲያ እና ቻይና የምክር ቤቱ ቋሚ አባላት ናቸው። ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣንም አላቸው።

የድምፅ አሰጣጡን ተከትሎ በተባበሩት መንግሥት የአሜሪካ ምክትል አምባሳደር የሆኑት ሮበርት ዉድ “አሜሪካ አሁንም ቢሆንም ሁለት አገራት መመሥረት አለባቸው የሚለውን ሐሳብ ትደግፋለች። ይህ ውሳኔያችን ፍልስጤም አገር መሆን አለባት የሚለውን ሐሳብ መቃወም አይደለም። ሁለቱ አገራት ከሚያደርጉት ድርድር ነው መፍትሔ የሚመጣው የሚለውን መርኅን እንደምንከተል የሚያሳይ እንጂ” ብለዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤም አምባሳደር ሪያድ ኤች ማንሱር
የምስሉ መግለጫ,በተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤም አምባሳደር ሪያድ ኤች ማንሱር

ፍልስጤም በመንግሥታቱ ድርጅት ያላት ቦታ?

ፍልስጤም በተባበሩት መንግሥታት ያላት ቦታ አባል ያልሆነች ነገር የታዛቢነት ሚና ያላት የሚል ነው።

በአውሮፓውያኑ 2011 ፍልስጤም የተባበሩት መንግሥታት ሙሉ አባል ለመሆን ጥያቄ አቅርባ ነበር። ነገር ግን በጊዜው የፀጥታው ምክር ቤት ድጋፍ ባለመስጠቱ ሐሳቡ ለድምፅ መስጠት አልቀረበም።

በ2012 ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላይ ጉባዔ ፍልስጤም “አባል ያልሆነች ታዛቢ አገር” እንደትሆን ፈቀደ። ይህ ማለት ጉባዔው በሚያደርገው ውይይት ላይ መሳተፍ ይችላሉ፤ ነገር ግን ድምፅ መስጠት አይችሉም ማለት ነው።

ይህ ውሳኔ በወቅቱ በጋዛ ሰርጥ እና በዌስት ባንክ ተቀባይነት ቢያገኝም እስራኤል እና ዩናይትደ ስቴትስን አስቆጥቷል። በዚህ ውሳኔ መሠረት ፍልስጤም የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ ችሎት፣ የዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት አባል እንድትሆን ሆነ።

“የተባበሩት መንግሥታት ሙሉ አባል መሆን ማለት ለፍስጤም የተሻለ ዲፕሎማሲያዊ ኃይል ማለት ነው። ፍልስጤም አባል ብትሆን በጠቅላላው ጉባዔ ድምፅ ለመስጠት ትችላለች። ምናልባት የፀጥታው ምክር ቤት አባል ልትሆንም ትችላለች” የሚሉት የመካከለኛው ምሥቅ ተንታኙ ኻሊድ አልጊንዲ ናቸው።

“ነገር ግን እኒህ ውሳኔዎች የሁለት አገራት ምሥረታ የሚለውን ሐሳብ እውን ያደርጉታል ማለት አይደለም። እሱ እውን የሚሆነው እስራኤል በኃይል ከያዘቻቸው ግዛቶች ለቃ ስትወጣ ነው” ሲሉ ያክላሉ።

“ፍልስጤም ሙሉ አባል የመሆን ሕልሟ ቢሳካ እንኳ ይህን ያህል ለውጥ አይኖረውም” የሚሉት ደግሞ በለንደን የስኩል ኦፍ ኦሪየንታል ኤንድ አፍሪካን ስተዲስ ምሑር የሆኑት ፕሮፌሰር ጊልበርት አርቻር ናቸው።

“እንዲሁ ትርጉም አልባ ድል ነው ነው የሚሆነው። ልቦለዳዊ አገረ-ፍስጤም ነው የምትሆነው። ምንም አቅም የሌለው “የፍልስጤም አስተዳደር” ከ1967 ወረራ በተረፉ ሥፍራዎች ላይ ያለ፤ እስራኤል ላይ ጥገኛ የሆነ አስተዳደር ነው።”

ምሑሩ አክለው ፍልስጤም ራስ ገዝ እና ነፃ ሆና ለማየት ገና ብዙ ዓመታት ይቀራሉ ይላሉ።

ፍልስጤምን እንደ አገር የሚያያት ማነው?

140 አገራት ፍልስጤምን እንደ አገር ያይዋታል። በተለይ ደግሞ የአረብ አገራት እና ድርጅቶች እንዲሁም ሌሎች ፍልስጤም ራሷን የቻለች አገር ናት ይላሉ።

ነገር ግን እንደ አሜሪካ፣ ዩኬ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና አውስትራሊያ ያሉ አገራት ፍልስጤምን እንደ አገር አይቀበሏትም።

ባለፈው ሳምንት ግን አውስትራሊያ “ሁለት አገራት ምሥረታ የሚለውን ሐሳብ ለማጠናከር” የፍልስጤምን አገርነት ልትደግፍ እንደምትችል አሳውቃለች።

ባለፈው ወር ደግሞ የስፔን፣ የአየርላንድ፣ የማልታ እና የስሎቬኒያ መሪዎች በአውሮፓ ኅብረት ስብሰባ ላይ በጎንዮሽ ባወጡት መግለጫ “ሁኔታዎች ሲመቻቹ” የፍልስጤምን አገርነት ሊቀበሉት እንደሚችሉ አሳውቀዋል።

የአሜሪካ ተወካይ ድምፅ ሲሰጡ
የምስሉ መግለጫ,አሜሪካ የተባበሩት መንግሥታት ሙሉ አባል አገር እንድትሆን የቀረበውን ሐሳብ አሜሪካ ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣኗን ተጠቅማ ውድቅ አድርጋዋለች

አንዳንድ አገራት ለምን እውቅና አይሰጧትም?

ፍልስጤምን እንደ አገር የማይቆጥሯት አገር ይህን ያላደረጉት ከእስራኤል ጋር በድርድር ላይ የተመሠረት ስምምነት ስላልተደረሰ ነው ይላሉ።

ለምሳሌ አሜሪካ ፍልስጤም እና እስራኤል ቀጥተኛ ድርድር ሊያደርጉ ይገባል ባይ ናት። ይህ ደግሞ በሌላ መልኩ ለእስራኤል ፍልስጤም ላይ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት መስጠት ነው ሲሉ አንዳንድ ምሑራን ይከራከራሉ።

በሁለቱ አገራት መካከል በ1990ዎቹ የሰላም ድርድር ተጀምሮ የሁለት አገራት ምሥረታ ሐሳብ የቀረበ ሲሆን፣ ይህ ሐሳብ እስራኤል እና ፍልስጤም ሁለት አገራት ሆነው በሰላም እንዲኖሩ የሚያልም ነው።

ነገር ግን ይህ የሰላም ድርድር ከአውሮፓውያኑ 2000 ወዲህ እየተቀዛቀዘ መምጣት ጀመረ። በ2014 በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል በዋሺንግተን የተካሄደው ድርድር ያለውጤት ተበተነ።

ሁለቱን አገራት የማያስሟሟቸው ነጥቦች የድንበር ጉዳይ እና የወደፊት የአገረ-ፍልስጤም ዕጣ ፈንታ ጉዳይ ናቸው። የእየሩሳሌም ጉዳይ እንዲሁም በእስራኤል ምሥረታ ጊዜ የተሰደዱ የፍልስጤም ስደተኞች ነገርም አከራካሪ ናቸው።

እስራኤል፤ ፍልስጤም የተባበሩት መንግሥታት ሙሉ አባል የመሆኗን ጉዳይ ፈፅሞ አትቀበለውም። በተባበሩት መንግሥታት የእስራኤል አምባሳደር የሆኑት ጊላድ ኤርዳን ሐሳቡ ለጠረጴዛ መቅረቡ በራሱ “ለዘር ማጥፋት ሽብርተኞች” ትልቅ ድል ነው ብለዋል ሲል ኤኤፍፒ ዘግቦ ነበር።

አምባሳደሩ አክለውም በተለይ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ሐማስ በእስራኤል ላይ ከፈጸመው ጥቃት በኋላ ይህ መሆኑ ለቡድኑ ሽልማት እንደመስጠት ነው ብለዋል።

ከእስራኤል ጋር በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ግንኙነት መመሥረት የሚፈልጉ አገራት ለፍልስጤም አገርነት እውቅና መስጠት አደጋ እንዳለው ያውቃሉ።

የእስራኤል አጋር አገራትን ጨምሮ አንዳንድ አገራት ደግሞ በ1933 በሞንቴቪድዮ ስምምነት መሠረት ፍልፍስጤም አገር ለመሆን የሚያበቃውን መሥፈርት አታሟላም ይላሉ።

መሥፈርቶቹ ቋሚ ሕዝብ፣ የተሰመረ ድንበር፣ መንግሥት እና ከሌሎች አገራት ጋር ግንኘኑት ለመመሥረት የሚያበቃ አቅም ናቸው።

ነገር ግን ሌሎች አገራት ደግሞ ፍልስጤም ከአገራት እውቅና ከተሰጣት ራሷን የመቻል መብት ሊኖራት ይገባል ይላሉ።