April 25, 2024 – EthiopianReporter.com 

የአገር ጉዳይ ሲነሳ የብዙዎች ቀልብ የሚሳበው ሥጋት ወደ የሚያጭረው የሰላምና የፀጥታ ዕጦት ነው፡፡ በእርግጥም በአሁኑ ጊዜ የአገር ተስፋ የሚያጨልሙ ድርጊቶች ከየአቅጣጫው በብዛት ይስተዋላሉ፡፡ ነገር ግን አገር አጥፊ ከሚባሉ ሥጋቶች ይልቅ በጋራ ብሔራዊ ራዕይ ወደ ልማት፣ ዴሞክራሲ፣ እኩልነት፣ ማኅበራዊ ፍትሕና የጋራ ተጠቃሚነት የሚያሸጋግሩ ተስፋ ሰጪ ጉዳዮች ላይ ለመረባረብ የሚያስችል ምኅዳር ለመፍጠር መረባረብ ለአገር ይጠቅም ነበር፡፡ ይሁንና የአገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን በሕዝብ ስም በሚያቀነቅኑት የሥልጣንና የጥቅም አጀንዳ ምክንያት፣ ቢያንስ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት አገር ጤና አጥታ የኢትዮጵያ ሕዝብም መከራ እያጨደ ነው፡፡ ከአገር ሰላም፣ ደኅንነትና ጥቅም በፊት ምንም ዓይነት የሚቀድም ዓላማም ሆነ አጀንዳ ማራመድ አይገባም ቢባልም አዳማጭ ሊገኝ አልቻለም፡፡ በዚህም የተነሳ አየሩን የሞላው ተስፋ ሳይሆን ሥጋት ነው፡፡

ብዙዎቹ የፖለቲካ ልሂቃን ኢትዮጵያ ለገጠማት ችግር መንስዔው ምንድነው ሲባሉ፣ ምላሻቸው የሚመሠረተው ከቆሙለት የፖለቲካ ፍላጎት አኳያ ነው፡፡ በዜግነትም ሆነ በብሔር ፖለቲካ የተደራጁ ፓርቲዎች አመራሮችና አባላት፣ አንዳቸው ለሌላቸው ዕውቅና ሰጥተው በልዩነት ውስጥ ለአገር አብሮ መሥራት እንደሚቻል መገንዘብ አይፈልጉም፡፡ ልዩነቶችን በፀጋ ከመቀበል ይልቅ ለግጭት ምክንያት እንዲሆኑ አጥብቀው ይሠራሉ፡፡ በሕግና በሥርዓት ለመተዳደር የሚያስችል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ ለሚያስፈልጉ ጠቃሚ ጉዳዮች መጨነቅ ሲገባቸው፣ አንዱ ሌላውን እንዴት ጠልፎ ጥሎ የበላይነቱን እንደሚይዝ እንቅልፍ አጥተው ስለሚያድሩ ለሴራ ፖለቲካ አመቺ መደላድል እንዲፈጠር አድርገዋል፡፡ ብዙዎቹ ለስሙ ፖለቲከኞች ይባሉ እንጂ ርዕዮተ ዓለማዊ መሠረት የሌላቸው ብቻ ሳይሆኑ፣ ለሚያቀነቅኑት ዓላማ የረባ ፕሮግራምና ማኒፌስቶ እንደሌላቸውም የታወቀ ነው፡፡ በኋላቀር አስተሳሰብ የታጀሉ ስለሆኑ ሥራቸው ግጭት መጥመቅ ነው፡፡

የፖለቲካ ልሂቃኑ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ከዘለቀው ጉዞአቸው ከጥፋቶችና ከስህተቶች መማር ስለማይፈልጉ፣ ኢትዮጵያን የግጭት አውድማ በማድረግ የሕዝቡን ሕይወት ተስፋ ቢስ እያደረጉት ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ነን እያሉ ቢመፃደቁም ተግባራቸው ግን ለአምባገነንነት በጣም ቅርብ ነው፡፡ ለዚህ ትንሹ ማሳያ ሁሉም በሚባል ደረጃ ውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲያቸው ሲገመገም በአድባርይነትና በአስመሳይነት የተሞላ ነው፡፡ ፓርቲዎቹን የሚመሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ማንነት ሲፈተሽም ቃልና ተግባራቸው የተጣጣመ አይደለም፡፡ ብዙዎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች የማኅበራትን ያህል ጥንካሬ፣ ሥርዓትና አመራር ስለሌላቸው መኖራቸው የሚታወቀው ምርጫ ሲኖር ወይም አንድ አገራዊ ክስተት ሲፈጠር ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በተረፈ ለሥልጣንና ለጥቅም ያቆበቆቡ አመራሮቻው ሁከት ለመፍጠር ወይም ያቀዱትን ለማሳካት ነው ሴራ ጉንጎና ላይ ጊዜያቸውን የሚያባክኑት፡፡

ለሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መቀስቀስ ዋነኛው ምክንያት በገዥው ብልፅግና ፓርቲና በሕወሓት መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ነበር፡፡ ሁለቱ ወገኖች በሰከነ መንገድ ተቀምጠው ተነጋግረው ልዩነቶቻቸውን መፍታት ባለመቻላቸው፣ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ወገኖች ዕልቂትና በበርካታ ቢሊዮን ዶላሮች ለሚቆጠሩ ንብረቶች ውድመት ምክንያት ሆነዋል፡፡ በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ የተካሄደው ያ አውዳሚ ጦርነት በውጭ ኃይሎች አስገዳጅነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ቢገታም፣ አሁንም ከዚያ ሁሉ መከራና ሥቃይ መማር ባለመቻሉ ራያ ውስጥ ሌላ ዙር ችግር እየተፈጠረ ነው፡፡ ድርጊቱ ያለ ከልካይ ሲቀጥል በሌሎች የይገባኛል አካባቢዎችም ችግሩ ተባብሶ ይቀጥላል፡፡ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ እየተካሄደ ያለው ውጊያም በጊዜ ፈር እንዲይዝ ባለመደረጉ፣ የመከራ አዝመራ እያጨዱ ያሉት ያለ ኃጢያታቸው የተፈረደባቸው ንፁኃን ናቸው፡፡ አገር እንዲህ ተቀስፋ ተይዛ ብዙዎቹ የፖለቲካ ልሂቃን ለመፍትሔ የሚረዳ በጎ ሐሳብ ማቅረብ ተስኗቸዋል፡፡

ገዥው ብልፅግና ፓርቲ አገር ሲመራ ከእነ ስህተቶቹም ቢሆን ጠቃሚ ትሩፋቶች ይኖሩታል፡፡ እነዚህ ትሩፋቶች ለአገርና ለሕዝብ ጠቃሚነታቸው የሚመሰከረው ግን በደጋፊዎቹ ብቻ ሳይሆን፣ ገለልተኛ ሆነው አሠራሩን በአንክሮ በሚከታተሉት ጭምር መሆን አለበት፡፡ የሚቃወሙትም ቢሆኑ በጭፍን ሳይሆን በመርህ ላይ ተመሥርተው ቢሆን ተመራጭ ነው፡፡ ነገር ግን የገዥውም ሆነ የተቃዋሚው ጎራ ፅንፍ ላይ ሆኖ አንዱ ሌላውን ማጥላላት ስለሚቀናው፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተረፈው መከራና ሥቃይ ብቻ ነው፡፡ ከፅንፈኝነት በመለስ በዴሞክራሲያዊ ዕሳቤዎች ላይ በመመሥረት ልዩነትን አክብሮ በሕግና በሥርዓት ከመንቀሳቀስ ይልቅ፣ የጉልበቱ መንገድ ብቻ ስለሚመረጥና ካለፉት ስህተቶችም መታረም ስለማይፈለግ አገር የተረፋት ነጋ ጠባ ጭቅጭቅ ነው፡፡ አንዱ ሌላውን አስወግዶ የበላይነቱን ለማግኘት የሚመርጠው፣ ግጭት አስነስቶ አገሪቱን በደም በማጠብ ስለሆነ ሕዝባችን እየተጎዳ ነው፡፡

ከእንዲህ ዓይነቱ እጅግ አስከፊና አስመራሪ ልማድ ውስጥ መውጣት ያስፈልጋል፡፡ በተለይ የፖለቲካ ልሂቃን የእስካሁኑን አክሳሪ ጉዞአችሁን በሚገባ መርምራችሁ በቃ በሉ፡፡ በገዥውም ሆነ በተቃውሞ ጎራ ውስጥ ያላችሁ ወገኖች ከሥልጣን በላይ አገርና ሕዝብ እንዳሉ አስቡ፡፡ ሥልጣንና የሚያስገኘው ጥቅም ጊዜያዊና አላፊ መሆኑ በመገንዘብ ለዘላቂ ሰላም፣ ለጋራ ልማትና ዕድገት፣ ለማኅበራዊ ፍትሕ፣ ለዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች፣ እንዲሁም ለነፃነት በአንድነት ለመሥራት የሚያስችል ዓውድ እንዲፈጠር ምከሩ፡፡ የዛሬው ትውልድ በትናንት የታሪክ ቁርሾዎች ላይ ብቻ እንዲቸነከር አድርጋችሁ አገሩን እንዲያጠፋ አትገፋፉት፡፡ ለእናንተ የማይረካ የሥልጣን ጥም ስትሉ የትውልዱን ተስፋ አታጨልሙ፡፡ ለሕዝብ የህሊና ዳኝነት ራሳችሁን አስገዙ፡፡ የጉልበት መንገድ ያተረፈው ዕልቂትና ውድመት እንጂ ዕድገት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕፎይታ የሚያገኘው ከሰላም እንጂ ከጦርነት እንዳልሆነ ተገንዘቡ፡፡ ስለዚህም በኢትዮጵያ የሥጋት ጨለማ ተገፎ የተስፋ ጭላንጭል ይታይ!