April 25, 2024 – Konjit Sitotaw
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ከ ‘ ቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ‘ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገው ነበር።
በቃለምልልሱ ፥ ባለፉት ሳምንታት በአማራ እና ትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች የነበረው ግጭት በ ” የሚሊሻ አባላት ” መካከል እንጂ መደበኛ ኃይሎች የተሳተፉበት አልነበረም ብለዋል።
” አማራ ክልል በኩል የነበሩ ሚሊሻዎች የተለያዩ አስጊ እንቅስቃሴያዎችን ሲያደርጉ ነበር። በእኛ በኩል ያሉ የሚሊሻ አባላት ምላሽ ሰጥተዋል ” ሲሉ ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ያወጣውን መግለጫም ” መሬት ላይ ያለውን እውነታ ያላገናዘበ ” ብለዋል።
የሰላም ስምምነቱ ተፈጻሚ እንዳይሆን እያደረገ ያለው ” ሕጋዊ የልሆነ የአማራ አስተዳደር ነው ” ሲሉ ተደምጠዋል።
አቶ ጌታቸው በዚሁ ቃለ ምልልስ ፥ በሰላም ስምምነቱ መሰረት በጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉትን ሰዎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ከስምምነት መደረሱን አስታውሰዋል።
” ሕጋዊ ያልሆኑ አስተዳደሮችን ለማፍረስ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር አብረን እየሠራን ነው። ከአማራ ክልል ጋርም ቢሆን በተወሰነ ደረጃ አብረን እየሠራን ነው ” ብለዋል።
” የፕሪቶሪያው ስምምነት ተፈጻሚ እንዳይሆን የሚሹ አካላት እንዳሉ ግን በጣም እርግጠኞች ነን ” ሲሉ ተደምጠዋል።
አቶ ጌታቸው እነዚህ አካላት እነማን እነደሆኑ በግልጽ በስም ጠርተው አልጠቀሱም።