ኪዝ ቦይድ

25 ሚያዚያ 2024, 14:59 EAT

አህጉረ አፍሪካን በፍጥነት በሩጫ በማቋረጥ ክብረ-ወሰን ለመስበር ያለመው ግለሰብ በደኅንነት ስጋት ምክንያት ዕቅዱ ሊከስምበት እንደሆነ ተናግሯል።

ኪት ቦይድ ላለፉት 270 ቀናት ከደቡብ አፍሪካዋ ኬፕ ታውን እስከ ግብፅ ካይሮ ሲሮጥ ከርሟል።

ነገር ግን በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው የፀጥታ ችግር ወደኋላ እያስቀረው እንደሆነ ተናግሯል። ቦይድ ሦስት ጊዜ በሰሜን ኢትዮጵያ በኩል ለማቋረጥ ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

አልፎም አንድ ጊዜ የጦር መሣሪያ በያዙ ሰዎች ተይዞ እንደነበር እና ከመታፈን ለጥቂት እንዳመለጠ ተናግሯል።

ብሪታኒያዊ-ደቡብ አፍሪካዊው ቦይድ እንዳለው ታጣቂዎች እሱን እና ካሜራ ይዞ የሚከተለውን ማይክል ለማፈን ሲሞክሩ “አበቃልን” ብሎ አስቦ ነበር።

“ከመንገድ አውጥተው ወደ ጥግ ሲወስዱን የነበረው ሁኔታ አሁንም ያቃዠኛል” ይላል።

“መንገዱን ይዘን ከሄድን ፖሊስ አሊያም ወታደሮች መጥተው ያድኑናል እያልኩ ለማይክል ስነግረው ነበር።”

ሁኔታው ወደ “የለየለት አፈና” ሊሸጋገር ቀርቦ ነገር ግን “በአስደናቂ ሁኔታ ተፈታ” ሲል ያስታውሳል።

ኪዝ ቦይድ

ባለፈው ወር ራስል ኩክ አሊያም በቅፅል ስሙ “ሀርደስት ጊዘር” አህጉረ-አፍሪካን በ352 ቀናት ሮጦ ማጠናቀቁ ይታወሳል።

እንደ ቦይድ ሁሉ ኩክም የጦር መሣሪያ በያዙ ሰዎች ዝርፊያ ደርሶበታል።

ቦይድ የቀረውን 500 ኪሎ ሜትር በሰላም አጠናቆ በድንቃ ድንቅ መዝገብ ስሙን ያሰፍር ዘንድ የኢትዮጵያ መንግሥት ጥበቃ እንዲያደርግለት ጠይቋል።

“የተቀሩት 500 ኪሎ ሜትሮችን ሳንጨርስ ቀርተን ክብረ-ወሰን የመስበር ዕድላችን ከባከነ በጣም የሚያሳዝን ነው። ከ26 ዓመታት በኋላ ክብረ-ወሰኑን ለመስበር ጫፍ ሲቀረን ሕልማችን ቢከስም ያበሳጫል” አክሎ ብሏል።

ሯጩ ጨምሮ “አሁን ሁሉም ነገር የሚወሰነው በኢትዮጵያውያን ነው። ይህን ክብረ-ወሰን እሰብራለሁ አልሰብርም የሚለውን የሚመልሱት እነሱ ናቸው። በመቶ በመቶ በእነሱ እጅ ነው ያለሁት።”

ቦይድ ሩጫውን በአውሮፓውያኑ ግንቦት 7 በማጠናቀቅ የዓለም ክብረ-ወሰንን በ30 ቀናት ማሻሻል ይፈልጋል።

“እኔ የ57 ዓመቱ ወፍራም ሰው ለ26 ዓመታት የተያዘ ክብረ ወሰን መስበር ከቻልኩ፤ ለዚያውም በዓለማችን እጅግ ከባድ በሚባለው ሥፍራ፤ እናንተ የወጣንችሁትን ለማሳካት ከተነሳችሁ ምን ልታደርጉ እንደምትችሉ አስቡት።”