የታንዛንያ ጎርፍ

ከ 3 ሰአት በፊት

በታንዛንያ ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት የ155 ሰዎች ህይወት መቀጠፉን የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አስታወቁ።

በዚህ ከባድ ዝናብ ምክንያት 200 ሺህ ሰዎች እና ከ51 ሺህ በላይ አባወራዎች የከፋ ችግር ላይ መውደቃቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

ታንዛንያን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ አገራት መነሻው ከፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ በሆነው እና በአካባቢ በሚፈጠር የውኃ ሙቀት መጨመር በሚከሰተው ኤልኒኖ የአየር ክስተት ምክንያት በከፋ ዝናብ ተመትተዋል።

በዚህም ምክንያት ታንዛንያን ጨምሮ ጎረቤቶቿ ቡሩንዲ እና ኬንያ ሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ ገብተዋል።

በአገሪቱ ፓርላማ ቀርበው ስለ ወቅታዊ ጉዳዮች ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ማጂሊዋ ህይወታቸው ካለፈው 155 ዜጎች በተጨማሪ 236 ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል ብለዋል።

“ከከባዱ የኤልኒኖ ዝናብ በተጨማሪ ንፋስ፣ ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ከፍተኛ ውድመት አድርሰዋል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ

አክለውም “ህይወት መቅጠፍን ጨምሮ፣ እህል፣ ቤቶች፣ የሰዎች ንብረት እንዲሁም መንገዶች፣ ድልድዮች፣ እና የባቡር መንገድ የመሰሳሰሉ መሰረተ ልማቶች ላይ ውድመት አድርሷል” ብለዋል።

በሰሜናዊ ታንዛንያ ሺያ ወረዳ ነዋሪ የሆነ አንድ ግለሰብ ቤቱ ሙሉ በሙሉ በዝናቡ እንደወደመበት ለቢቢሲ ተናግሯል።

“ምንም የቀረኝ ነገር የለም። ያለኝ በሙሉ ተጠራርጎ ተወስዷል” ሲል ገልጿል።

በኬንያዋ መዲና ናይሮቢ አውሎ ንፋስ በቀላቀለው ከባድ ዝናብ እና ጎርፍ መውጫ አጥተው ያሉ ነዋሪዎችን ለመታደግ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዊልያም ሩቶ ሰራዊቱ እንዲሰማራ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

በአንዳንድ የተጨናነቁ መንደሮች ቤቶች፣ ዕቃዎች ተጠርገው ተወስደዋል።

በዚህ ሳምንት አስር ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ በዚህ ወር የሞቱ ሰዎችን ቁጥር ቢያንስ 45 እንዳደረሰው ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል አስታውቋል።

በቡሩንዲ የጣለው ከባድ ዝና ከ100 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን አፈናቅሏል።