በአትላንታ  ተቃወሞዎችን ለማብረድ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ገብቷል
የምስሉ መግለጫ,በአትላንታ ተቃወሞዎችን ለማብረድ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ገብቷል

ከ 4 ሰአት በፊት

በሎስ አንጀለስ የሚገኘው የደቡብ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ በመጪው ግንቦት 2/2016 ዓ.ም ሊያደርገው የነበረው ዋና የምረቃ ፕሮግራም ከደህንነት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ተሰርዟል።

በአሜሪካ ውስጥ በሚገኙ በርካታ ዩኒቨርስቲዎች እስራኤል በጋዛ ላይ እያደረገችው ያለውን ጥቃት የሚቃወሙ ተቃውሞዎች ተስፋፍተዋል።

በአትላንታ ኤሞሬይ ዩኒቨርሲቲ የ28 ተቃዋሚዎች ትናንት ማክሰኞ ከዩኒቨርሲቲው ለመውጣት አሻፈረኝ ካሉ በኋላ ታስረዋል።

በአሜሪካ የዩኒቨርስተዎች ተቃውሞ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ጀምሮ የነበረ ቢሆን ባለፈው ሳምት በኒው ዮርክ በሚገኘው የኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ድንኳኖችን ተክለው አቀጣጥለውታል።

በአሜሪካ የሚገኙ በርካታ ዩኒቨርስቲዎች ፍልስጤማውያንን በሚደግፉ እና እስራኤልን በሚቃወሙ እንቅስቃሴዎች እየተካሄደባቸው ይገኛሉ።

የደቡብ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ ትናንት ባወጣው መግለጫ ከ65 ሺህ በላይ ታዳሚዎች የሚሳተፉበትን ዋና የምረቃ ፕሮግራም ለማከናወን እንደሚቸገር ገልጿል።

ይህ ውሳኔ ከመተላለፉ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ከፖሊስ ጋር ፍጣጫ ውስጥ የገቡ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ታስረዋል።

ዩኒቨርስቲው ከዚህ ውሳኔ ሶስት ሳምንታት በፊት አስና ታብሱም የታለች ሙስሊም ተማሪ በምረቃ ፕሮግራም ላይ ንግግር ልታደርግ እቅድ ተይዞ ግልጽ ባላደረገው ምክንያት መሰረዙን አሳውቆ ነበር።

በአትላንታ ኢሞሪ ዩኒቨርሲቲ ታቃዋሚዎች ፍልስጤማውያንን እንደሚደግፉ ገልጸዋል። ይህም ብቻ ሳይሆን በአትላንታ እየተገነባ ያለውን የፖሊስ ማሰልጠኛ ላይ ያላቸውን ቅሬታም አሰምተዋል።

ይህ ማስልጠኛ በከተማው ከፍተኛ ውዝግብ ያስነሳ ሲሆን አንዳንድ ተቃዋሚዎች ግንባታው ሎስአንጀለስን የፖሊስ ከተማ ያደርጋል ሲሉ ገልጸውታል።

ዩኒቨርስቲው ባወጣው መግለጫ ይህ “ሁከት” ያጋጠመው ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየጨረሱ እና ለማጠቃለያ ፈተና እየተዘጋጁ ባሉበት ሰዓት ነው ብሏል።

ፖሊስ ተቋሙን ለመጠበቅ በአካባቢው አባላቱን እንዳሰማራ የገለጸ ሲሆን አንዳንድ ተቃዋሚዎች ፖሊስ ቁሶችን ወርውረዋል ብሏል።

የመጀመሪያው የተጠናከረ ተቃውሞ በተቀሰቀሰበት የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ኃላፊዎች ለፖሊስ ከደወሉ በኋላ 100 ሰዎች ለእስር ተዳርገዋል።

ይህ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ወደ በርካታ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ተዛምቷል።

የፍልስጤም ደጋፊዎቹ ተማሪዎች እስራኤል “በጋዛ ላይ እየፈጸመችው ካለው የዘር ጭፍጨፋ” ዩኒቨርሲቲዎች ራሳቸው እንዲያርቁ እየጠየቁ ነው።

በተጨማሪም ለእስራኤል የጦር መስሪያ የሚያመርቱ ተቋማትን እንዳይደግፉም በተቃውሟቸው እያሳሰቡ ነው።

ቺያስቶ ሚሙራ የተባለች የህግ ተማሪ ተቃዋሚዎች በጆ ባይደን እና በዩኒቨርስቲ አመራሮች ከፍተኛ ቅሬታ እንዳለቸው ለቢቢሲ ገልጿል።

“ለዘር ማጥፋት የሚሆን የጦር መሳሪያ ከማምረት እና ለእስራኤል ከማስታጠቅ እንዲቆጠቡ” ተቃዋሚዎቹ መጠየቃቸውን አንስታለች።

በርካታ አይሁድ ተማሪዎች በኮሎምቢያ እና በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ከፍተኛ ስጋት እንዳለባቸው ገልጸዋል። ሌሎች አይሁድ ተማሪዎች ደግሞ ተቃውሞን ተቀላቅለው ታይተዋል።

በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተቃውሟቸውን አቁመው ወደ ስምምነት እንዲመጡ እስከ ትላንት እኩለ ሌሊት ጊዜ ቀነ ገደብ ተቀምጦላቸው ነበር።

ሆኖም ዩኒቨርስቲው ከተቃዋሚዎች ጋር ስምምነት ላይ ባለመደረሱ ሌላ አማራጭ እንደሚመለከት ገልጿል። ምን አይነት አማራጭ የሚለው ላይ ግን በይፋ የተባለ ነገር የለም።