የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እና የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ
የምስሉ መግለጫ,የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እና የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ

26 ሚያዚያ 2024, 15:45 EAT

የቻይን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋሽንግተን የአገራቸውን “ቀይ መስመር” እንዳታልፍ ለአሜሪካው አቻቸው አስጠነቀቁ።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ለአሜሪካው አቻቸው አንቶኒ ብሊንከን ይህን የተናገሩት ሁለቱ ባለሥልጣናት ዛሬ አርብ ሚያዝያ 18/2016 ዓ.ም. ቤይጂንግ በተገናኙበት ወቅት ነው።

ዋንግ ከብሊንከን ጋር በነበራቸው ስብሰባ የሁለቱ አገራት ግንኙነት መረጋጋት እየታየበት እንደሆነ ጠቅሰው አሁንም ግን “አሉታዊ በሆኑ ጉዳዮች” የቤይጂንግ እና የዋሽንግተን ግንኙነት እየተፈተነ መሆኑን ተናግረዋል።

“ቻይና እና አሜሪካ በትክክለኛው መንገድ ወደፊት ተጉዘው ወደ ተረጋጋ ግንኙነት መመለስ አለባቸው ወይስ በተቃራኒው አቅጣጫ መሄድ?” ሲሉም ጠይቀዋል።

በአንድ ዓመት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ቤይጂንግ የሚገኙት አንቶኒ ብሊንከን፣ ዛሬ አመሸሻ ከቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋር ተገናኝተው የቻይና ጉብኝታቸውን ያጠናቅቃሉ።

ባለፉት ዓመታት በቻይና እና በአሜሪካ መካከል ውጥረት ነግሶ ቆይቷል።

ቻይና በታይዋን እና በደቡብ ቻይና ባሕር ላይ የምታነሳው የይገባኛል ጥያቄ፣ አሜሪካ የረቀቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ወደ ቻይና እንዳይላኩ ማዕቀብ መጣሏ እንዲሁም በአሜሪካ ሰማይ ላይ የታየችው የቻይና “የስለላ” ፊኛ ሁለቱን ኃያላን አገራት ካወዛገቡ ጉዳዮች ቀዳሚዎቹ ናቸው።

ከሁለት ቀናት በፊት ደግሞ የአሜሪካ ሴኔት የቻይናው ቲክቶክ ካልተሸጠ በአሜሪካ እንዲታገድ የሚያዝ አዋጅ ማጽደቁ የሁለቱ አገራት ሌላ ያለመግባባት ምክንያት እንደሚሆን ይጠበቃል።

ዋንግ ከብሊንከን ጋር ፊት ለፊት በተገናኙ ወቅት ሁለቱ አገራት ያላቸው አማራጭ በትብብር መቀጠል ወይም ወደ ግጭት ሊያመራ ወደሚችል አለመግባባ ውስጥ መግባት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የቻይናን የሉዓላዊነት፣ የደኅንነት እና የልማት ቀይ መስመርን አሜሪካ ጭርሶ ማለፍ የለባትም ብለዋል።

ሁለቱ ባለሥልጣናት ከንግግራቸው በኋላ በሰጡት የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፤ “በቻይና እና አሜሪካ ግንኙነት አሉታዊ ተጽእኖዎች አሁንም እየጨመሩ እና እየተደራረቡ ግንኙነቱን በሁሉም በኩል እያወኩ ነው” ብለዋል ዋንግ።

“የቻይና እውነተኛ የልማት ፍላጎት ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ ጫና ውስጥ እየገባ እና የፍላጎታችን መሠረት ፈተና እየገጠመው ነው” ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል።

ሁለቱ ባለሥልጣናት በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ አንቶኒ ብሊንከን ከቻይናው አቻቸው በተለየ መልኩ ለዘብ ያለ አስተያየት ሰጥተዋል።

ብሊንከን ቤይጂንግ እና ዋሽንግተን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ወደፊት ለማራመድ የጋራ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

የባይደን አስተዳደር ለታይዋን ወታደራዊ ድጋፍ ማድረጉ ከቻይና ጠንከር ያለ ትችትን አሰንዝሮ ነበር።

ቻይና ራስ ገዝ የሆነችው ታይዋን ተገንጥላ የወጣች፤ ወደፊት ግን የቻይና አንድ አካል የምትሆን የራሷ ግዛት አድርጋ ትመለከታታለች።

በሌላ በኩል ቻይና የወታደራዊ ቁሶች መለዋወጫ ወደ ሩሲያ መላኳ አሜሪካን እረፍት የሚነሳ ጉዳይ ነው።

የጆ ባይደን አስተዳደር ሩሲያ በዩክሬን ላይ ለከፈተችው ጦርነት ከቻይና የምታስገባቸውን ምርቶች ለግብዓትንት እየተጠቀመችበት ነው ይላል።