ማኅበራዊ የመጥፋት አደጋ ከተጋረጠባቸው ቋንቋዎች ውስጥ ሁለቱ በድጋሚ እንዲያገግሙ እንደሚደረግ ተገለጸ

ሰላማዊት መንገሻ

ቀን: April 28, 2024

የመጥፋት አደጋ ከተጋረጠባቸው ቋንቋዎች ውስጥ የብራይሌና ባጫ ቋንቋዎችን ለመታደግና መልሶ እንዲያገግሙ ለማስቻል እየተሠራ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚያዝያ 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ባቀረበበት ወቅት እንደተገለጸው፣ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸውን ቋንቋዎች ለመታደግ በሚል 22 ቋንቋዎችን የመሰነድ ሥራዎች በመሥራት በዘጠኝ ወራት ውስጥ የብራይሌና ባጫ ቋንቋዎች መልሶ እንዲያገግሙ ለማስቻል፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከጂንካ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ከሌሎች ባለድርሻ አካለት ጋር ምክረ ሐሳብና ግብዓት ማሰባሰብ የሚያስችል የምክክር መድረክ መካሄዱን ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ ተናግረዋል።

የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸው ቋንቋዎች በድጋሚ ለመመለስ በተደረገው ጥረት በደቡብ ኢትዮጵያ ኦሞ ዞን ብራይሌ፣ መዊ፣ አንጉታና ባጫ ቋንቋዎች የተገኙ ሲሆን 145 ዓመታት ያስቆጠረው የብራይሌ ቋንቋ አምስት ተናጋሪ ብቻ በማግኘት ከእነዚህም ውስጥ ብራይሌ የተባለውን ትክክለኛ ቋንቋ የሚናገረው አንድ ሰው ብቻ መሆኑን በማረጋገጥ የቀሩት ሰዎች ከተለያዩ ቋንቋዎች ጋር በመደባለቅ የሚናገሩ መሆናቸው በጥናት መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡

ሊጠፉ የተቃረቡ ቋንቋዎችን የሚናገሩትን አምስቱ ሰዎች በዕድሜ የገፉ በመሆናቸው፣ ከተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር ቋንቋውን ማስቀጠል የሚቻልበት መንገድ እየተሞከረ ነው ብለዋል፡፡

ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና ከምክር ቤቱ አባላት ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጥያቄዎች የቀረበ ሲሆን፣ ከጥያቄዎቹ መካከል እንደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የአገሪቱን የቋንቋዎች ብዛት በጥናት ለይቶ የማወቅ ኃላፊነት ያለበት ቢሆንም ከ80 በላይ ቋንቋዎች በማለት ለምን እንደሚጠቀም ተጠይቋል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለዚህ በሰጠው ምላሽ በውል የሚታወቁ የቋንቋዎች ብዛትን በመለየት በቁጥር ለመግለጽ ጥናት የሚፈልግ በመሆኑ በሒደት ላይ ያለው ጥናትም ቢሆን በአንዳንድ ቋንቋዎች ላይ ያሉ ተመሳሳይነት ወደ አንድ ለማምጣት በሚመከርበት ወቅት የቋንቋው ተናጋሪ ክፍል የሚወክለው መሆን አለመሆኑን እንዲሁም ኅብረተሰቡ ላይ ጥያቄ በማይፈጥር መልኩ ለመሰነድ እየተሠራ መሆኑን የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኃላፊዎች አብራርተዋል፡፡ የጥናቱን ውጤትም በቅርቡ ይፋ ለማድረግ በሒደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ቋንቋዎችን በማበልፀግ የኢኮኖሚው፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ማስተሳሰሪያ ገመድ በማድረግ የአገሪቱን ዕድገት ለማረጋገጥ በዘርፉ ትክክለኛ፣ የሠለጠነና ፕሮፌሽናል የሆነ የሰው ኃይል ለማፍራት ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር በመሥራት የቋንቋ ልማት አጠቃቀምን ለማሳደግ የቋንቋ ልማት ፍኖተ ካርታ (ROAD MAP) በማዘጋጀት ኅብረተሰቡን በቋንቋው ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ ልዩ ልዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ተብሏል፡፡

በተያያዘም በ2012 በጀት ዓመት ፀድቆ ሥራ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ የቋንቋ ልማት ፖሊሲ፣ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቋንቋዎች ፊደል ተቀርፆላቸው በአፍ መፍቻ ቋንቋ ለትምህርት መስጫነት እንዲውሉ አቅጣጫ ከተቀመጠ በኋላ ተጨማሪ ስድስት የብሔር ብሔረሰብ ቋንቋዎች (ሐረሪ፣ ሶማሌ፣ አፋር፣ ትግርኛ ኦሮምኛና ሲዳሚኛ) የክልል የሥራ ቋንቋ በመሆን እያገለገሉ እንደሚገኙ ይታወሳል፡፡

ከአማርኛ በተጨማሪ ለፌዴራል የሥራ ቋንቋነት እንዲውሉ ዕውቅና የተሰጣቸው  (አራት) ቋንቋዎች ማለትም (ኦሮምኛ፣ ሶማሌኛ፣ አፋርኛና ትግርኛ) ቋንቋዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት ተከታታይ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

በፖሊሲው ከተካተቱ ጉዳዮች አንዱ የሆነው የቋንቋዎች ጥናት ኢንስቲትዩት ማቋቋም ሲሆን ይህን በተመለከተ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በቻይና ቤጂንግ የውጭ ጉዳይ ጥናት ዩኒቨርሲቲ (Beijing Foreign Study University) ጋር በመሆን የኢትዮጵያ ጥናት ማዕከል ማቋቋሚያ (Establishing Ethiopia Study Center) ረቂቅ ሰነድ ቀርቦ በሰነዱ ላይ አቅጣጫ መሰጠቱን ሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡

ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የትርጉምና አስተርጓሚነት ሙያ ሥራ ላይ እንዲውል ሥርዓተ ትምህርት (Curriculum) በማዘጋጀት ተግባራዊ ለማድረግ የስምምነት ሰነድ በመፈራረም፣ በአገሪቱ ባሉ ሁለት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የትርጉምና አስተርጓሚነት ፕሮግራም ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

ብዝኃ ቋንቋን (መልቲ ሊንጉዋሊዝም) ለማበረታታት በአገሪቱ የሚገኙ አሥር ቋንቋዎችን በዲጂታል ሥርዓት እንዲሰነዱ ለማድረግ ማስተባበር፣ ክትትልና ድጋፍ ለማድረግ ታቅዶ ከዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ፣ የትምህርት ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንሲ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ሁሉንም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በዲጂታል ቴክኖሎጅ በአንድ ቋት ሥር ሰንዶ በማደራጅት ተጠቃሚ ለማድረግ ሥራ መጀመሩ ተገልጿል፡፡