ጭምብል ያጠለቀ ፍልስጤማዊ
የምስሉ መግለጫ,የእስራኤልን ሰፈራ በመቃወም ማንነቱን ለመደበቅ ጭምብ አድርጎ የሚታገል ፍልስጤማዊው እአአ 1989 ዌስት ባንክ።

ከ 5 ሰአት በፊት

በቅርቡ በአሜሪካ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እየተካሄዱ ካሉ የጋዛን ጦርነት ከሚቃወሙ ሰልፎች ጋር ተያይዞ ‘ኢንቲፋድ’ የሚለው ቃል በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል።

ኢንቲፋዳ አረብኛ ቃል ሲሆን “ተቃውሞ/አመጽ” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል።

ቃሉ ብዙ ጊዜ የሚያያዘው ፍልስጤማውያን በእስራኤል ላይ ከሚያስነሱት መረር ካለ ተቃውሞ ጋር ነው።

የጋዛ ጦርነትን ተከትሎ አዲስ ኢንቲፋዳ ሊነሳ እንደሚችል ብዙዎች አስተያየታቸውን እየሰጡ ነው።

ሌሎች ደግሞ ኢንቲፋዳ የሚለውን ቃል “ዓለም አቀፋዊ ኢንቲፋዳ” በሚል በመተካት የጋዛ ጦርነት በመላው ዓለም ሰዎችን እንዳስተሳሰረ ያመለክታሉ።

ኢንቲፋዳ ማለት ምን ማለት ነው?

የአረብኛ ቃል የሆነው ኢንቲፋዳ ቀጥተኛ ትርጉሙ ‘ተቃውሞ’ ነው። ይህ ቃል በፍልስጤም እና በእስራኤል መካከል የኖረውን ከባድ ፍጥጫ ለመግለጽ ጥቅም ላይ ይውላል።

የጀመሪያው ኢንቲፋዳ ከእአአ 1987 እስከ 1993 የተካሄደ ነበር። ሁለተኛው ኢንቲፋዳ ደግሞ ከ2000 እስከ 2005 ድረስ ነበር የዘለቀው።

የሐማስን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ የጋዛ ጦርነት መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ከጀመረ በኋላ “ግሎባላይዝ ኢንቲፋዳ” (ዓለም አቀፍ ኢንቲፋዳ) የሚላው ቃል በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ነው።

ከዚህ ቃል በተጨማሪ “ኤሌክትሮኒክ ኢንቲፋዳ”፣ “ኢንቴሌክቹዋል ኢንቲፋዳ” የሚሉ ቃላት የእስራኤልን ምርቶች መጠቀምን ከሚከለክሉ ሐሳቦች ጋር ተያይዘው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየወጡ ይገኛሉ።

ለፍልስጤማውያን ድጋፍ የሚሰጥ ተቃውሞ በአሜሪካው ማሳቹሴት ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ
የምስሉ መግለጫ,ለፍልስጤማውያን ድጋፍ የሚሰጥ ተቃውሞ በአሜሪካው ማሳቹሴት ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ

የመጀመሪያው ኢንቲፋዳ፡ ከእአአ 1987 እስከ 1993

የመጀመሪያው የፍልስጤማውያን ኢንቲፋዳ የተቀሰቀሰው እአአ በ1987 ላይ ጋዛ ውስጥ ነበር።

የዚህ ሰፊ ተቃውሞ መነሻ የሆነው ክስተት ደግሞ የእስራኤል ጦር ታንክን እያጓጓዘ የነበረ ከባድ መኪና በሌላ ተሸከርካሪ ውስጥ የነበሩ 4 ፍልስጤማውያንን ገጭቶ ከገደለ በኋላ ነው።

ከዚያ ክስተተ በፊት በእስራኤል ወረራ ስር ይኖሩ የነበሩ ፍልስጤማውያን ቁጭታቸውን ለ20 ዓመታት አምቀው ይዘው ነበር።

እስራኤል በዌስት ባንክ እና ጋዛ ሰርጥ ስታካሂድ የነበረው ሰፈራ እየተስፋፋ የነበረበት ወቅትም ነበር። በምጣኔ ሃብት ቀውስ ሲሰቃዩ የነበሩት ፍልስጤማውያን በተለያዩ አጋጣሚዎች ከእስራኤል ጦር ጋር ሲጋጩ ቆይተዋል።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ የነበሩት የጋዛ ነዋሪዎች የፍልስጤማውያኑ ሞት ቁጣቸውን አገንፍሎት ከፍተኛ ተቃውሞ በእስራኤል ላይ ተነሳ።

ተቃውሞው ቀድሞ የተቀሰቀሰው በጋዛ በሚገኘው ጃባሊያ ተብሎ በሚጠራው የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ነበር። ከዚያ በፍጥነት ተስፋፋቶ ወደ ዌስት ባንክ እና ቀሪው የጋዛ ክፍል ተስፋፋ።

ፍልስጤማውያን በእስራኤል ወታደሮች ላይ ድንጋይ ሲወረውሩ
የምስሉ መግለጫ,ፍልስጤማውያን በእስራኤል ወታደሮች ላይ ድንጋይ ሲወረውሩ

ወጣት ፍልስጤማውያን ድንጋይ እና በነዳጅ የተሞሉ ጠርሙሶችን ወደ እስራኤል ወታደሮች መወርወርን ተያያዙት።

የእስራኤል ጦር በአጸፋው በገዳይ ጥይቶች ፍልስጤማውያኑን ዒላማ ያደርግ ነበር።

የተባበሩት መንግሥት ድርጅትን ጨምሮ ምዕራባውያን እና ተቋሞቻቸው እስራኤል በተቃዋሚዎቹ ላይ እየወሰደች ያለው እርምጃ ተመጣጣኝ አይደለም ብለው ነበር።

በሁለቱ ወገኖች መካከል ግጭቱ ከፍ እና ዝቅ እያለ እስከ አውሮፓውያኑ 1993 ድረስ ቀጠለ።

ይህ በእስራኤል ላይ የተቀጣጠለው ተቃውሞ ለብዙዎች እንግዳ ነበር። በወቅቱ ለፍስጤማውያን ነጻነት ይታገል ለነበረው የያሲር አረፋት የፍልስጤም ነጻነት ድርጅት (ፒኤልኦ) እንኳ የጠበቀው አልነበረም።

የመጀመሪያው ኢንቲፋዳ ዋነኛ ዓላማ ፍልስጤማውያን በእስራኤል እየደረሰባቸው ያለውን ግፍ ለዓለም ማሳየት ነበር።

በወቅቱ እስራኤል ጦር መሳሪያ ባልታጠቁ ወጣቶች ላይ ጥይት መተኮሷ ብዙ አስተችቷት ነበር።

በመጀመሪያው ኢንቲፋዳ ወቅት የእስራኤል ወታደሮች በፍልስጤማውያን ላይ ጥይት ሲተኩሱ
የምስሉ መግለጫ,በመጀመሪያው ኢንቲፋዳ ወቅት የእስራኤል ወታደሮች በፍልስጤማውያን ላይ ጥይት ሲተኩሱ

በዚህ ኢንቲፋዳ ወቅት ብዙዎች የተቀባበሉት አንድ ሐረግ ነበር። ይህም የወቅቱ የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ይትዛክ ራቢን ያሉት ነው።

መከላከያ ሚኒስትሩ እስራኤል ድንጋይ በሚወረውሩ ወጣት ፍልስጤማውያን ላይ ጥይት መተኮሷ ዓለም ለፍልስጤማውያን እንዲያዝን ስለሚያደርግ ተቃዋሚዎችን ከመግደል ይልቅ “አጥንታቸውን እንስበር” ብለው ነበር።

ኢንቲፋዳው በጊዜ ሂደት መልኩን እየቀየረ ፍልስጤማውያንም ድንጋይ እና ቤንዚል የተሞሉ ጠርሙሶችን ከመወርወር የእስራኤል ወታደሮችን በስለት፣ በቦምብ እና በተቀጣጣይ ነገሮች ማጥቃትን ተያያዙት።

ያሲር አረፋት እና የወቅቱ የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሺሞን ፔሬዝ በኦስሎ።
የምስሉ መግለጫ,ያሲር አረፋት እና የወቅቱ የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሺሞን ፔሬዝ በኦስሎ።

አንዳንድ አሃዞች በመጀመሪያው ዙር ኢንቲፋድ ፍልስጤማውያን 100 ወታደሮችን መግደላቸውን እና እስራኤል ደግሞ ከአንድ ሺህ ያላነሱ ፍልስጤማውያንን መግደሏን ያሳያሉ።

እአአ 1993 ላይ የያሲር አረፋት ድርጅት ፒኤልኦ የሰላም ስምምነት ማዕቀፍ የተዘረጋበትን የኦስሎ ስምምነት ከእስራኤል መንግሥት ጋር ሲፈራረሙ የመጀመሪያው ኢንቲፋዳ ማብቂያ ሆነ።

በዚህ ስምምነት እስራኤል ፒኤልኦን የፍልስጤማውያን ተወካይ አድርጋ ስትቀበል፤ ፒኤልኦ ደግሞ ለትጥቅ ትግል እውቅና ነሳ።

ሁለተኛው ኢንቲፋዳ፡ ከእአአ 2000 – 2005

እአአ 2000 ላይ ኤሪያል ሻሮን በበርካታ የእስራኤል ወታደሮች እና ፖሊሶች ታጅበው አል-አቅሳ መስጂድን ሲጎበኙ።
የምስሉ መግለጫ,እአአ 2000 ላይ ኤሪያል ሻሮን በበርካታ የእስራኤል ወታደሮች እና ፖሊሶች ታጅበው አል-አቅሳ መስጂድን ሲጎበኙ

ሁለተኛው ኢንቲፋዳ “አል-አቅሳ” የሚል ስያሜ ነበረው።

አል-አቅሳ መስጂድ ነው። አል-አቅሳ መስጂድ በእስልምና ሦስተኛው ቅዱስ ቦታ ሲሆን፣ ለአምስት ዓመታት የዘለቀው ታውሞ መነሻ ቦታ ነው።

እአአ 2000 ላይ በወቅቱ የእስራኤል ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የነበሩት ኤሪያል ሻሮን በበርካታ የእስራኤል ወታደሮች እና ፖሊሶች ታጅበው አል-አቅሳ መስጂድን ጎበኙ።

ይህን ተከትሎ በተፈጠረ ተቃውሞ በመጀመሪያው ቀን ሰባት ሰዎች ሲገደሉ ከ100 በላይ የሚሆኑ ፍልስጤማውያን ደግሞ ቆሰሉ።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን በኤሪያል ሻሮን ጠባቂዎች ላይ ጫማ እና ድንጋይ በመወርወር የጀመሩት ተቃውሞ በመላው ፍልስጤማውያን መገኛ በሆኑ አካባቢዎች ተቀጣጠለ።

ታዳጊው ሞሐመድ አል-ዱራ አባቱ ስር ተሸሽጎ ሳለ ነበር ጋዛ ውስጥ በእስራኤል ወታደር የተገደለው።
የምስሉ መግለጫ,ታዳጊው ሞሐመድ አል-ዱራ አባቱ ስር ተሸሽጎ ሳለ ነበር ጋዛ ውስጥ በእስራኤል ወታደር የተገደለው።

በወቅቱ የ12 ዓመት ታዳጊ ከተኩስ እሩምታ እራሱን ለመታደግ አባቱ ጉያ ስር ከተሸሸገ በኋላ ሕይወቱ ሲያልፍ የሚያሳየው ምሥል ብዙዎችን አስቆጣ።

ታዳጊው ሞሐመድ አል-ዱራ አባቱ ስር ተሸሽጎ ሳለ ነበር ጋዛ ውስጥ በእስራኤል ወታደር የተገደለው። ይህ ምሥል በበርካታ ፍልስጤማውያን ልብ ውስጥ ቀርቷል።

እስራኤል ክስተቱን በተመለከተ ምርመራ አካሂዳ ምሥሉን የቀረጸው የፍረንሳይ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋዜጠኛ ለታዳጊው ሞት የእስራኤል ወታደር ተጠያቂ ማድረጉ መሠረተ ቢስ ነው ብላ ነበር።

ሁለተኛው ኢንቲፋዳ ከመጀመሪያው ኢንቲፋድ ከፍተኛ የሆነ ግጭት የተደረገበት ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት በሁለተኛው ኢንቲፋዳ ከ5 ሺህ 800 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል ይላል።

በሁለተኛው ኢንቲፋዳ ፍልስጤማውያን ሮኬቶችን ወደ እስራኤል ከማስወንጨፍ ጀምሮ በሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ላይ እራሳቸውን በቦምብ እስከማጋየት ደርሰው ነበር።