ቲም ሎውተን

29 ሚያዚያ 2024, 13:04 EAT

የዩናይትድ ኪንግደም ወግ አጥባቂ የፓርላማ አባል ቻይና ላይ ባቀረቡት ትችት ጂቡቲ ከመግባት እንደተባረሩ ተናገሩ።

ከቻይና ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላት ጂቡቲ ከጥቂት ሳምንት በፊት እንዳባረቻቸው ቲም ሎውተን ገልጸዋል።

የምስራቅ ዎርቲንግ እና ሾረሃምን ግዛቶችን በመወከል የፓርላማ አባል የሆኑት ቲም ሎውተን ጂቡቲ ሲደርስ ከሰባት ሰዓታት በላይ በእስር መቆየታቸውን እና ወደ ጂቡቲ እንዳልገባ ተከልክያለሁ ብለዋል።

ከሶስት ዓመት በፊት በቻይና ማዕቀብ የተጣለባቸው ሎውተን በሁኔታው ብቸኝነት እንደተሰማቸው “በጣም አስፈሪ” እንደነበር ተናግረዋል።

የቻይና የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ክሱ መሰረተ ቢስ ነው ብሏል።

የፓርላማ አባሉ ወደ ጂቡቲ ያቀኑት ለአንድ ቀን አገሪቱን ለመጎብኘትና በአገሪቱ ከተቀመጡትም የዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር ጋር ለመገናኘት ነበር።

ጂቡቲ ከደረሱ በኋላ እንዳይገቡ እና በሚቀጥለው በረራ ተሳፍረው እንደሄዱም አስረድተዋል።

“ይህ የቻይና ኮሚኒስት መንግሥት እጅ ምን ያህል ረዥም እንደሆነ የሚያሳይ ሌላ ምሳሌ ነው። በተለይም በአንዳንድ አፍሪካ አገራት ያላቸው የከፋ ተጽዕኖ አሳሳቢ ነው” ሲሉ ሎውተን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ሆኖም ቻይና እያደረሰችው ያለው መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ተቃውመው ለመናገር በደፈሩ እና ይህንን ለመናገር መድረክ ባጡ ስፍር በሌላቸው ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለው ማስፈራራት ከባድ ስጋት ይፈጥራል” ብለዋል።

ከሶስት ዓመታት በፊት ቻይና በአገሪቱ ላይ “ሃሰተኛ እና የተሳሳተ መረጃ” እያሰራጩ ነው ባለቻቸው ቲም ሎውተንን ጨምሮ በአምስት የፓርላማ አባላት ላይ ማዕቀብ ጥላለች።

ይህም የዩናይትድ ኪንግደም በአገሪቱ ባሉት ኡጉር አናሳ ሙስሊም ማህበረሰብ አባላት ላይ እየደረሰ ያለውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ አስመልክቶ ለወሰደችው እርምጃ አጸፋዊ የበቀል ምላሽ ነው ተብሏል።

የቀድሞው ሚኒስትር እና ሆም አፌይርስ የተሰኘው መስሪያ ቤት ኮሚቴ አባል ከ27 ዓመታት የፓርላማ ቆይታ በኋላ በቀጣይነት በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ በእጩነት እንደማይቀርቡ አስረድተዋል።