April 29, 2024 – Konjit Sitotaw
በየዓመቱ የአገሮችን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሪፖርት የሚያወጣው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከቀናት በፊት ወደ 200 የሚጠጉ አገሮችንና ግዛቶችን በተመለከተ ያጠናቀረውን ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡
ኢትዮጵያን በተመለከተ ይፋ ባደረገው ባለ 68 ገጽ ሪፖርት በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይም በትግራይ ክልል የተካሄደው ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ቢገታም፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ ድንበር አካባቢዎች የኤርትራ ታጣቂዎች የሚያደርጉት ጥቃት መቀጠሉን በመጀመሪያው የሪፖርቱ ማብራሪያ ላይ ገልጿል፡፡
በ2015 ዓ.ም. ልዩ ኃይሎች ወደ መደበኛ ፖሊስ ወይም የመከላከያ ሠራዊት አባልነት ወይም ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጉን የጠቀሰው ሪፖርቱ፣ ይህንንም ተከትሎ በአማራ ክልል ከፋኖ ታጣቂዎችና በኦሮሚያ ክልል ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነግ ሸኔ) ጋር ግጭት መቀጠሉንም ያወሳል፡፡
ሪፖርቱ በነሐሴ 2016 ዓ.ም. በአማራ ክልልና እንደ አስፈላጊነቱ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተፈጻሚ ይሆናል ተብሎ በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ በመንግሥት ኃይሎች አማካይነት ሰፋ ያሉ የመብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል ይላል፡፡ ከሕግ ውጪ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ የተፈጸሙ ግድያዎች፣ አስገድዶ መሰወር፣ ማሰቃየትና ኢሰብዓዊ ቅጣቶች በመንግሥት አካላት መፈጸማቸውን በሰፊው አብራርቷል፡፡
ከባድና ሕይወትን አደጋ ውስጥ የሚጥሉ የእስር ቤት አያያዞች፣ በኃይል አስገድዶ ማሰርና ማቆየት፣ በጦርነት ወቅት ከሕግ አግባብ ውጪ የሚከናወኑ የንፁኃን ዜጎች ግድያና የአካል ጉዳት፣ በኃይል ማፈናቀልና ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እንዲዘዋወሩ ማድረግ፣ አካላዊ ጥቃት ማድረስ፣ ፆታዊ ጥቃት፣ የሚዲያ ነፃነትን በከፍተኛ ሁኔታ መገደብ የሚሉት ተጠቅሰዋል፡፡
በጋዜጠኞች ላይ የሚደርስ ዛቻና ጥቃት፣ ያለ ምክንያት በቁጥጥር ሥር ማዋል፣ ሳንሱር፣ በሐሰተኛ ስም የማጥፋት ዘመቻና ውንጀላ፣ የኢንተርኔት ነፃነትን በከፍተኛ ሁኔታ መገደብ፣ ሐሳብን በሰላማዊ መንገድ ለመግለጽ የሚደረጉ የመብት ጥያቄዎችንና የመደራጀት መብት ላይ ጫናና ጣልቃ ገብነት በሰፊው መስተዋሉ በሪፖርቱ ተካቷል፡፡ በተጨማሪም በድርጅቶች ላይ ማውጣት ተጠቅሷል፡፡
በተመሳሳይ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትንና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን የፋይናንስ አጠቃቀማቸውንና እንቅስቃሴያቸውን የሚገድቡ ሕጎች፣ በመንግሥት ውስጥ የሚፈጸም ከፍተኛ ሙስና፣ በዓለም አቀፍና በአገር አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ላይ የሚደረግ ዘለፋ፣ ጥቃትና ገደብ፣ አስገድዶ መድፈርና ትንኮሳዎች፣ ፆታዊ ጥቃቶች፣ በአናሳ ብሔረሰቦች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችና የወንጀል ድርጊቶች በሪፖርቱ ተዘርዝረዋል፡፡
ሰፋ ያሉ የንፁኃን ዜጎች ግድያ፣ በጅምላ ማፈናቀል፣ በታጣቂዎች የሚደረግ ዝርፊያና የንብረት ማውደም፣ እንዲሁም በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ከሕግ አግባብ ውጪ የተገደሉ የመንግሥት አመራሮች መኖራቸውን ጠቅሶ በአፋር፣ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በአካባቢ የሚሊሻ አባላት መገደላቸውንና በርካቶች መፈናቀላቸው በሪፖርቱ ተተንትኗል፡፡
የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ዓመታዊ ሪፖርት በተጠናቀቀው እ.ኤ.አ. ከ2023 በመንግሥት አካላት ከፍተኛ የሆነ የመብት ጥሰት መከናወኑን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡ መረጃውን ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ከሂዩውማን ራይትስዎች፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፣ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)፣ በተለይም በአማራ፣ በኦሮሚያና በትግራይ ክልሎች ተፈጸሙ የተባሉ የመብት ጥሰት ሪፖርቶችን በመመልከት መሆኑን አስታውቋል፡፡
የክልል የፖሊስ አካላት አደገኛና ከመጠን በላይ የሆነ ኃይል በንፁኃን ዜጎች ላይ እንደሚጠቀሙ፣ ለአብነትም እ.ኤ.አ. በየካቲት 2023 በወልቂጤ ከተማ የመጠጥ ውኃ ጥያቄ እንዲመለስላቸው በሰላማዊ ሠልፍ ለመጠየቅ የወጡ 30 ዜጎችን በጦር መሣሪያ መግደላቸውን፣ በአዲስ አበባ የመስጊድ መፍረስን የተቃወሙ ሦስት ንፁኃን ዜጎችን የመንግሥት ኃይሎች መግደላቸውን፣ በዚህም ረገድ የፌዴራል ፖሊስ የተፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶችን ለመመርመር የሄደበት ርቀት ውስን መሆኑን አብራርቷል፡፡ የተወሰዱ ዕርምጃዎችም ሚስጥራዊ ተደርገው መቀመጣቸውን ጠቅሷል፡፡
በኃይል አስገድዶ መሰወር በተለይም በመንግሥት ላይ የተለየ ሐሳብ የሚሰነዝሩ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የፖለቲካ ተንታኞች፣ የቀድሞ የሠራዊት አባላት፣ የምርመራ ጋዜጠኞችና የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎች ላይ በብዛት ሥወራ እንደሚፈጸም አስታውቋል፡፡
ከአዲስ አበባ ወደ ጂቡቲ የሚጓዙ ሾፌሮች የሚያነሱት የፀጥታ ችግር መንግሥት ለመፍታት አለመቻሉን፣ ሾፌሮች ሲታገቱና ሲገደሉ የፀጥታ ሁኔታውን ለማስተካከል እንደተሳነው በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
በሕገ መንግሥቱ የተከለከለ በቁጥጥር ሥር በዋሉ ግለሰቦች ላይ ማሰቃየትና አካላዊ ጥቃቶች መፈጸሙንና በተለይም በአማራ፣ በቤኒሻንጉል በጉሙዝ፣ በጋምቤላና ሶማሌ ክልሎች እስረኞችን በመደብደብ መረጃ እንዲያወጡ ይደረጉ እንደነበር ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ተረድቻለሁ ብሏል፡፡
የማይታወቁና ሚስጥራዊ የማቆያ ቦታዎች መኖራቸውን፣ መጥፎና አሳሳቢ የሆነ የእስረኞች አያያዝና የማሰቃየት ተግባር በተለይም በፖሊሶች፣ በማረሚያ ቤት ጠባቂዎች ወይም በሌሎች ወታደራዊና የፀጥታ ኃይሎች አማካይነት ይፈጸም እንደነበር ጠቅሷል፡፡ እነዚህ ድርጊቶች ይፈጸሙ የነበሩት በፖሊስ ጣቢያዎች፣ በማቆያ ቦታዎች፣ በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች፣ በወታደራዊ ማዕከላት፣ ሚስጥራዊ በሆኑና ባልታወቁ የማቆያ ቦታዎች እንደሆነ ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡
የማረሚያ ቤቶች ሁኔታ ከባድና ሕይወትን አደጋ ውስጥ የሚጥል መሆኑን የሚያብራራው ሪፖርቱ፣ ይህም ሊሆን የቻለው ታራሚዎችና በቁጥጥር ሥር የዋሉ ግለሰቦች በተጨናነቀ ቦታ እንዲሆኑ በመደረጉ ሳቢያ በምግብ እጥረት፣ በሚደርሰባቸው አካላዊ ጥቃት፣ በቂ ባልሆነ የመፀዳጃ አገልግሎትና መሰል አሳሳቢ ምክንያቶች ነው ብሏል፡፡
በጅምላ አስሮ ማቆየት የተለመደ አሠራር ነው የሚለው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ሪፖርት፣ ለታራሚዎች ጥራት ያለው ምግብና ውኃ፣ እንዲሁም የመፀዳጃ አገልግሎት፣ የሕክምና አለመኖር፣ በመኖሪያ ቤት ውስጥ የኤሌክትሪክ አቅርቦት አለመኖሩን ይጠቅሳል፡፡
ታራሚዎችን በተደበቀና ለብቻው በተሠራ ቤት ውስጥ እንደሚቆዩ፣ በዚህ ማቆያ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ማድረግ የማይችሉ መሆኑንና የምግብ፣ የውኃና የመፀዳጃ አገልግሎት እንደማያገኙም ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡
የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ጭምር እስረኞችን ከማቆያ ቤት እያወጡ ይረሽኑ እንደነበር የገለጸው ሪፖርቱ፣ መንግሥት ብዙ ያልታወቁ ሚስጥራዊ የማቆያ ቦታዎችን መጠቀሙ እየጨመረ ነው ይላል፡፡
በሕገ መንግሥቱና በሌሎች ሕጎች አማካይነት ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ ማንንም በቁጥጥር ሥር ማዋል እንደማይቻል ቢደነግግም፣ ባለሥልጣናት ተጠርጣሪን ያለ ምንም ማስረጃ በቁጥር ሥር እንደሚያውሉ፣ ክስ ሳይመሠረት ለ14 ቀናት እንደሚያቆዩ፣ ፍርድ ቤቶች በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ለሚቀርቡ ክሶች ማስረጃ እንዲቀርብ ግፊት ቢያደርጉም ፖሊስ ተጨማሪ መረጃ እየጠየቀ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ዜጎችን የእስር ጊዜ እንደሚያራዝም በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
በዋስትና መፈታት መብት ቢሆንም ፖሊስ በዋስትና እንዲፈቱ በፍርድ ቤት ውሳኔ ያገኙ ዜጎችን እንደማይለቅ፣ ይባስ ብሎ ሌላ ተጨማሪ ክስ እንደሚመሠርት የጠቀሰው ሪፖርቱ፣ በተደጋጋሚ የዋስትና መብቶች እንደሚጣሱ አንዳንዴም እስረኞችን ወደ ክልሎች በማዘዋወር በሌላ ተጨማሪ ወንጀል እንዲጠየቁ እንደሚያደርግ ተጠቅሷል፡፡
መንግሥት ከነሐሴ 2015 ዓ.ም. ወዲህ ተግባራዊ እያደረገ ባለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት መጋዘኖችን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ የወጣት ማዕከላትን፣ የግል መኖሪያዎችንና ሌሎች ቦዎታችን ወደ ማቆያነት በመቀየር በሺዎች የሚቆጠሩ የአማራና የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡ በተወሰኑ አካባቢዎች ሕፃናትን በወንጀል ተጠርጥረዋል በሚል ጥርጣሬ ብቻ በማቆያ ቦታ እንደሚታገቱ አብራርቷል፡፡
ረዥም ጊዜ የሚወስድ የፍርድ ሒደት፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው እስረኛ፣ ቀልጣፋ ያልሆነ የፍርድ ቤት ውሳኔና ውስን የሰው ኃይል ያላቸው ፍርድ ቤቶች ለፍርድ ሒደት መዘግየት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡
በሕጉ መሠረት ፍርድ ቤቶች ነፃና ገለልተኛ እንዲሆኑ ቢጠበቅም፣ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት የፍርድ ቤቶችን ገለልተኛናትና ሚዛናዊነት የማያከብር መሆኑን የጠቀሰው ሪፖርቱ፣ የፍትሐ ብሔር ችሎቶች በተሻለ በገለልተኝነት ቢሠሩም የወንጀል ጉዳይ ችሎቶች ደካማና በከፍተኛ ሁኔታ የታጨቁና የተጨናነቁ ናቸው ይላል፡፡
የመንግሥት አካላት ከድንበር ያለፈ የማስፈራራት ተግባር ይፈጽማሉ የሚለው ሪፖርቱ፣ ለአብነትም ከሳዑዲ ዓረቢያ ለኢትዮጵያ መንግሥት ተላልፎ የተሰጠ ጋዜጠኛ ስለመኖሩ አስረድቷል፡፡ በተመሳሳይ በውጭ አገር የሚኖሩ ዳያስፖራ ጋዜጠኞች በኢትዮጵያ ያሉ ቤተሰቦቻቸው ማስፈራሪያና ዛቻ እየደረሰባቸው ነው ብሏል፡፡
ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ የግል ንብረትን መበርበር እንደማይቻል በሕግ የተቀመጠ ቢሆንም መንግሥት ይህንን ፈጽሞ እንደማያከብር ያብራራል፡፡
መንግሥት የፖለቲከኞችንና የግለሰቦችን ስልክ በአቅጣጫ ጠቋሚ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎችና በኢንተርኔት የታገዘ የኮሙዩኒኬሽን መሣሪያዎችን በመጠቀም፣ የመጥለፍ ሥራ ላይ መሰማራቱ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
የመንግሥት አካላት እ.ኤ.አ. ከ2021 ጀምሮ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ዜጎችን ስልክ ለመበርበር የሚረዳ ሰለብራይት ከተባለ የእስራኤል ኩባንያ የስለላ መሣሪያ ገዝቶ ሥራ ላይ ማዋሉን፣ የኦንላይን የመረጃ ምንጭ የሆኑ ድረ ገጾችንና ኢንተርኔት በተደጋጋሚ መዝጋቱንና ለዚህም ይግባኝና አቤቱታ የሚጠየቅበት መንገድና አሠራር አለመኖሩን አብራርቷል፡፡
የመንግሥትን አሠራር አጥብቀው የሚጠይቁ የሰብዓዊ መብቶችና የሚዲያ ተቋማት ቢሮዎች ተሰብሮ መገባቱን፣ የሚዲያና የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ተቋማት ላይ የሚፈጸምን ዝርፊያ በተመለከተ ምርመራ እንዲያካሂድ መንግሥት ቢጠይቅም እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ምን ዓይነት ዕርምጃ እንደወሰደ ማወቅ አልተቻለም ብሏል፡፡
የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ የሚነሱ የሰብዓዊ ዕርዳታዎች አቀራረብና የፀጥታ ሁኔታውን በተመለከተ አስተያየት የሚሰጡ ጋዜጠኞች፣ የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎችና ሌሎችንም አስገድዶ እንደሚያስር በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
በርካታ ቁጥር ያላቸው ጋዜጠኞችን በበቀል ዕርምጃ በወንጀል ክሶች በተለይም ከፅንፈኝነትና ከአሸባሪነት ጋር በተገናኘ በቁጥጥር ሥር ካዋላቸው በኋላ፣ በቁጥጥር ሥር በዋሉበት ጉዳይ ሳይጠየቁ የጋዜጠኝነት ሥራቸውን ስላከናወኑ ብቻ ለተወሰነ ጊዜ ታስረው እንደሚለቀቁ፣ ይህም የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋዜጠኞችን አፋቸውን ለማዘጋትና ፍራቻን ለመልቀቅ የሚጠቀሙበት ሥልት በመሆኑ ነው ሲል ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡
በኢትዮጵያ በቴሌኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ የመንግሥት ተፅዕኖ መስፋቱን የገለጸው ሪፖርቱ፣ በኢትዮ ቴሌኮም አማካይነት የኦንላይን ሚዲያ በአገር አቀፍ ደረጃ እየዘረጋ ነው ብሏል፡፡
ዕውቅና ያልተሰጣቸው ሰላማዊ ሠልፎች የወንጀል ዕርምጃ እንደሚያስከትሉ የጠቀሰው ሪፖርቱ፣ ሰላማዊ ሠልፎችን ማድረግ ያልተለመደ ተግባር መሆኑን፣ ሰላማዊ ሠልፎች ከተካሄዱ ግን የፖለቲካ ምኅዳሩ ላይ ለውጥ መኖሩ ማሳያ ስለመሆኑ ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡
ሕጉ በአገር ውስጥ መንቀሳቀስ፣ የውጭ አገሮች ጉዞ ማድረግ፣ መሰደድና መመለስን የሚያከብር ቢሆንም መንግሥት የዜጎችን እንቅስቃሴ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ጉዞዎች ላይ ክልከላና ገደብ ስለማስቀመጡ ያወሳል፡፡ በአገር ውስጥ ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል በሚደረጉ ጉዞዎች በተለይም ትግራይ፣ አማራ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና ምዕራብ ወለጋ አካባቢዎች መንቀሳቀስ የማይቻል ነው ይላል፡፡ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት በርካታ የኬላ መቆጣሪያዎች በተለይ ክልሎችን በሚያገናኙ መንገዶች መኖራቸው፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ለማከናወን እንዳይቻል ስለማድረጉ አብራርቷል፡፡
ሪፖርቱ እ.ኤ.አ. በ2023 የኦሮሚያ ክልልና የፌዴራል ፖሊስ በሕዝብ በዓላትና መሰል ጉዳዮች ወደ አዲስ አበባ የሚደረጉ ጉዞዎችን የፀጥታ ሥጋት በሚል ሰበብ ከከተማ ውጭ የሚመጡ ዜጎች እንዳይገቡ ገደብ ስለመጣላቸው አውስቷል፡፡ በዚህ ገደብ የተነሳ በአመዛኙ ከጎጃምና ከጎንደር የአማራ ክልል ከተሞች የሚመጡ ወጣቶች ላይ ያተኮረ እንደነበር አስረድቷል፡፡ በተመሳሳይ ወደ ውጭ አገር የሚጓዙ ግለሰቦች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ያለ ምንም ትዕዛዝ ከአገር እንዳይወጡ እንደሚከልከሉ አመላክቷል፡፡ ለአብነትም የቀድሞ የአማራ ልዩ ኃይል አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ ለሕክምና ወደ እስራኤል ሊያደርጉት የነበረው ጉዞ በፀጥታ ኃይሎች መሰረዙን አስታውሷል፡፡
መንግሥት እ.ኤ.አ. ከ2020 ጀምሮ ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ለጥገኝነት የሚመጡ ዜጎችን መመዝገብ ማቆሙን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ድርጅት ማስታወቁን ጠቅሶ በዚህም የተነሳ ያልተመዘገቡ ኤርትራውያን ጥገኝነት ፈላጊዎች ቁጥር ማሻቀቡንና እንደ ስደተኛ ባለመመዝገባቸው ምንም ዓይነት አቅርቦት እንደማይደርሳቸው ጠቅሷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ኤርትራውያንን መመዝገብ ቢያቆምም ለ40 ሺሕ ሱዳናውያንና ለ100 ሺሕ የሶማሌላንድ ዜጎች የጥገኝነት ምዝገባ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም የጥገኝነት ምዝገባ ተደርጎላቸው የሚኖሩ ሰዎች የመንቀሳቀስ መብታቸው የተገደበ ነው ይላል፡፡
በአገሪቱ ሕግ በሙስና ድርጊት የተሳተፉ አካላት በወንጀል እንደሚጠየቁ የተደነገገ ቢሆንም፣ መንግሥት ሕጉን በሚገባው መጠን እንደማይተገብረው ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
የተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ሰብዓዊ መብቶችን በተመለከተ የሚያከናውናቸው ተግባራት፣ በማያቋርጥ የደኅንነት ሥጋትና ገደብ የተነሳ ምርመራ አካሂደው ለሕዝብ ይፋ ለማድረግ እንደሚቸገሩ ጠቅሷል፡፡ የአገር ውስጥ ድርጅቶች በተደጋጋሚ፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ድገሞ አልፎ አልፎ ከፀጥታ አካላት ማስፈራሪያና ዛቻ እንደሚደርሰባቸውና በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡
ሪፖርቱ ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ የዕርዳታ ድርጀቶች፣ የሰብዓዊ መብት ተቋማትና ዲፕሎማቶችና በተለዩ ቦታዎች እንዳይንቀሳቀሱ ገደብ እንደሚጣልባቸው ሪፖርቱ ያብራራል፡፡
አስገድዶ መድፈር ወንጀል መሆኑ በሕግ ቢደነገግም በትዳር አጋሮች የሚፈጸሙ መሰል የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎችን ሕጉ የማይተገብር መሆኑን፣ ፆታ ተኮር ጥቃቶች የማይታዩ መሆናቸውን፣ የጠለፋ ትዳር ሕገወጥ ቢሆንም አሁን በበርካታ የአገሪቱ አካባቢዎች ችግሩ መቀጠሉ በሪፖርቱ የተዳሰሱ ጉዳዮች ናቸው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ይኖራሉ የሚባሉ ከ10,000 በላይ አይሁዳውያን (ቤተ እስራኤላውያን) በመንግሥት ጥበቃ የሚደረግላቸው ቢሆንም፣ በማኅበረሰቡ መገለል እንደሚደርስባቸው ተገልጿል፡፡ በተመሳሳይ በገጠሩ የአገሪቱ አካባቢ ተመሳሳይ መገለልና እንደ ልዩ ፍጥረት አድርጎ የማየት፣ እንዲሁም በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ችግር እንደሚፈጠርባቸው በሪፖርቱ ተካቷል፡፡