አቶ በቴ ኡርጌሳ

ከ 2 ሰአት በፊት

በኦሮሞ ነጻነት ግንባር ውስጥ ‘የማይናወጥ ጽናት’፣ ‘በሀሳብ ውይይት ጀርባውን የማይሰጥ’፣ እና ‘የግንባሩ አዲስ ትውልድ ምልክት’ እየተባሉ የተወደሱት አቶ በቴ ኡርጌሳ ሚያዝያ 3/2016 ዓ.ም. በመቂ ከተማ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለው ተገኝተዋል።

አቶ በቴ እስከ ተገደሉበት ቀን ድረስ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የፖለቲካ ዘርፍን ይመሩ ነበር።

ከዚያ ቀደም ብሎ በተደጋጋሚ በሽብርተኝነት ክስ ተደጋጋሚ እስራት እና እንግልት ደርሶባቸዋል።

ከሶስት ዓመት በፊት ታስረው በነበረበት ወቅት በገጠማቸው የጤና መታወክ ሕይወታቸው ከፍተኛ ስጋት ላይ ወድቆ ነበር።

ከመገደላቸው አንድ ወር ቀድም ብሎም ከፈረንሳዊ ጋዜጠኛ ጋር ቃለ መጠይቅ እያደረጉ በነበረበት ወቅት በቁጥጥር ስር ውለው ከአንድ ሳምንት በላይ ከታሰሩ በኋላ የ100ሺህ ብር ዋስትና በማስያዝ ነበር የተፈቱት።

የእኚህ ፖለቲከኛ ግድያ ልክ እንደርሳቸው በሰላማዊ መንገድ በፖለቲካ ድርጅቶች ታቅፈው ለሚታገሉ ጉልበት አርድ ሆኗል።

ከፖለቲከኛው ግድያ ጋር በተያያዘ አስተያየታቸውን የተጠየቁ ሦሰት የፖለቲካ አመራሮች “ግድያው ፖለቲካዊ እንጂ ሌላ ሊባል ያሉት እድሎች በጣም አናሳ ናቸው ወይንም ዜሮ ነው” ሲሉ ተናግረው ነበር።

እነዚሁ ፖለቲከኞች “የእርሱ ግድያ ዓላማ በሰላማዊ መንገድ የሚደረግን ትግል ተስፋ ማስቆረጥ ነው” ሲሉ ያክላሉ።

አቶ በቴ ከተገደሉ ሁለት ሳምንት ያለፈ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ግን ሞታቸውም አሟሟታቸውም አነጋጋሪ ሆኖ ቆይቷል።

የአራት ልጆች አባቱ አቶ በቴ ግድያቸው በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ቀድሞ የጠየቀው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ነው።

ተከትሎም አሜሪካ፣ አውሮፓ ሕብረት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ገለልተኛ እና አመኔታ ያለው ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

ለደህንነታቸው በጣም በአስቸጋሪ ሁኔታ ይገኛሉ የሚባሉት የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ በየዓመቱ ሚያዝያ 7 የኦሮሞ ጀግኖች ቀን በሚዘከሩበት ዕለት በዙም ባስተላለፉት መልዕክት “የጃል በቴ መስዋዕትነት የሚያቃጥል፣ በንዴትም የሚያሳብድ ነው” ብለው ነበር።

አስተዋጽኦዋቸውንም ሲያስታውሱ “ግዴታውን ያለምንም ፍርሀት፣ በየትኛውም መድረክ የድርጅቱን ዓላማ ስልታዊ በሆነ መንገድ ከሚቃወሙ ፊት በመቆም፣ በሀሳብ ሞግቶ ማስጠበቅ መቻሉን አሳይቶ አልፏል” ብለዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የአቶ በቴ ግድያ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ወይንም በቀጠራቸው ቅጥረኞች መፈጸሙን ያምናል፤ አገኘሁት ያለውንም መረጃ ለሕዝብ ይፋ አድርጓል።

መንግሥት ግን በግድያው ተጠያቂ መደረጉን አውግዞ፣ ምርመራ እንደሚደረግ ገልጿል።

በግድያው የቤተሰብ ግጭት መንስዔ ሊሆን እንደሚችል ጠቅሶ እስከ ባለፈው ሳምንት ድረስ 13 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን መንግሥት አስታውቋል።

አቶ በቴ ኡርጌሳ ከኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ጋር
የምስሉ መግለጫ,አቶ በቴ ኡርጌሳ ከአቶ ዳውድ ኢብሳ ጋር

ለመሆኑ አቶ በቴ ማን ናቸው?

አቶ በቴ 1971 ዓ.ም በምስራቅ ሸዋ ዞን በመቂ ከተማ አቅራብያ ቦቆታ በሚባል አካባቢ ከአባታቸው አቶ ኡርጌሳ ቡላ እና ከእናታቸው ወ/ሮ ጎዳኖ ቦባራ ተወለዱ።

እድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ እዚያው ቦቆታ ተማሩ። ከአምስተኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን ትምህርታቸውን ደግሞ ወደ መቂ ከተማ በመሄድ ተከታትለዋል።

ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በመቂ ካቶሊክ ትምህርት ቤት የተከታተሉት አቶ በቴ፣ ጥሩ ውጤት በማምጣት በባህርዳር ዩኒቨርስቲ የመጀመርያ ዲግሪ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።

ከዩኒቨርስቲውም በ1997 ዓ.ም ከባዮሎጂ ትምህርት ክፍል የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል።

የአቶ በቴ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የሚጀምረውን በ1993 የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ተማሪ ከነበሩበት ጊዜ ነው።

በወቅቱ ሲደረግ በነበረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ መሳተፍ ብቻ ሳይሆን አመራር በመሆንም በቀዳሚነት ተሳትፈዋል።

በዚህም ምክንያት እስር እና እንግልት ደርሶባቸው እንደነበር ከፓርቲያቸው የወጣው መረጃ ያሳያል።

በ1997 ከተመረቁ በኋላ በአዳማ ከተማ በሀራምቤ፣ ኪያሜድ እና ቅድስት ማርያም ኮሌጆች በመምህርነት እና ሌሎች ዘርፎች ሲሰሩ ቆይተዋል።

አቶ በቴ በጤና ሞያ እና ኢኮኖሚክስ ትምህርት ዘርፎች ሌላ ሁለት ዲግሪዎችን ማግኘት ችለዋል።

በኋላም ከአርሲ ዩኒቨርስቲ በድህረ ምረቃ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ተመርቀዋል።

አቶ በቴ ኡርጌሳ ከአቶ ጃዋር መሃመድ ጋር

የቄሮ የወጣቶች ንቅናቄ ከማደራጀት ምርጫ ላይ እስከ መሳተፍ

አቶ በቴ ከዩኒቨርስቲ ከወጡ በኋላ በህቡዕ የኦሮሞ ነጻነት እንቅስቃሴ ውስጥ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደጀመሩ አንድ የትግል አጋራቸው የሆኑ ግለሰብ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በተለይ በ2010 የመንግሥት ለውጥ በማምጣት ሚና የነበረው የኦሮሞ ወጣቶች እንቅስቃሴ፣ ’ቄሮ ቢሉሱማ ኦሮሞ’ ትግል ውስጥ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው።

የትግል አጋራቸው ለቢቢሲ ሲያስረዱ አቶ በቴ በምስራቅ ሸዋ ዞን ቄሮን ሲያደራጁ ኋላም የመምራት ኃላፊነት ወስደው እንደነበር ገልጸዋል።

“ አሁንም በእስር ላይ የሚገኘው ዳዊት አብደታ እና ሌሎችም በምስራቅ ሸዋ ወረዳዎች ውስጥ ተንቀሳቅሰው ቄሮን ሲያደራጁ ነበር። ኋላም በዞኑ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ይመራ ነበር” ሲሉ ያክላሉ።

በ2008 በመላው ኦሮሚያተካሂዶ በነበረው፣ ትልቁ ሕዝባዊ ተቃውሞ ላይ እንቅስቃሴውን ለመምራት ከአዳማ መቂ ተጉዘው የተፈጠረውንም ሲያስታውሱ “እዚያ በደረሰበት ከፍተኛ ድብደባ ሞቷል ተብሎ ተጥሎ ነበር” ብለዋል።

በዚያ ጉዳት ምክንያትም ለአንድ ዓመት በክራንች ይንቀሳቀሱ እንደነበርም ጨምረው ገልጸዋል።

የአቶ በቴ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በኦሮሞ ነጻነት ግንባር ስር ተደራጅተው ይጀምሩ እንጂ በሰላማዊ ትግል ሀሳብን በሀሳብ መሞገት እና በሕዝባዊ ምርጫ በሚገኝ ስልጣን ያምኑ ስለነበር ብዙም ሳይቆይ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ አባል ሆኑ።

በ2010 በተደረገው አገራዊ ምርጫም አቶ በቴ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አባል በመሆን ከእሳቸው ጋር የምርጫ ቅስቀሳ እና ክርክር ሲሳተፉ እንደነበሩ የድርጅቱ ተቀዳሚ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ነገር ግን በ2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ በሰላማዊ መንገድ ሊሳተፍ ወስኖ አመራሩ ከኤርትራ ሲመለስ ቀድሞ እንቅስቃሴ ያደርጉበት ወደነበረው ድርጅት ተመለሱ።

ድርጅቱ ባጋራው የሕይወት ታሪካቸው ውስጥ አቶ በቴ ከ2010 ጀምሮ በኦሮሞ ነጻነት ግንባር ውስጥ ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው ድርጅቱ የሚሰጣቸውን ኃላፊነት ሲወጡ እና በአመራርነት ደረጃ ሲያገለግሉ እንደቆዩ ጠቅሷል።

በርካታ ሰዎች አቶ በቴ በጥቂት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ስማቸው በአጭር ጊዜ እውቅና ማግኘቱን እንዲሁም በድርጅቱ ውስጥ ከፍተኛ ኃላፊነት እንደተሰጣቸው ያምናሉ።

ድርጅቱ በበኩሉ አቶ በቴ በተለያዩ ውስጣዊ እና ውጪያዊ ምክንያቶች ፈተና በገጠሙት ወቅት ኃላፊነት ለመቀበል መቅረባቸውን ይገልጻል።

“በተለያዩ ምክንያቶች በገጠመ የሰው ኃይል ማነስ ምክንያት ከ2012 ጀምሮ እስከታሰረበት 2013 ድረስ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሕዝብ ግንኙነት ሆኖ ያገለግል ነበር” ብሏል።

አቶ በቴ መጋቢት 2013 እስከ 2014 በተለያዩ እስር ቤቶች እንግልት ሲደርስባቸው የነበረ ሲሆን፣ በዚህ ቆይታቸውም በጉበት በሽታ ሕመም ሲሰቃዩ ነበር።

የጤና ሁኔታቸው አስጊ በሆነበት ወቅትም ለሕክምና ሲባል ከእስር እንዲወጡ ተደርጓል።

አቶ በቴ ለአጭር ጊዜ ከሕመማቸው ካገገሙ በኋላ፣ የድርጅቱን የፖለቲካ ዘርፍ የመምራት ኃላፊነት ወስደው በመምራት እስከተገደሉበት ድረስ ሲንቀሳቀሱ ነበር።

አቶ በቴ ኡርጌሳ

“በጽናት ወደ ትግል ከገቡ አዲሱ ትውልድ መካከል ነው”

ከአቶ በቴ ጋር ከሰሩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች መካከል ፕሮፌሰር መረራ አንዱ ናቸው። በ2010 አገራዊ ምርጫ ቅስቀሳ ወቅት “ ከእኛ ጋር ሆኖ ሲከራከር ነበር። ምርጫም ላይ ተሳትፏል” ይላሉ።

“ግድያው እርሱ የሚታገልለትን ሕዝብ መጉዳቱ ጥያቄ የለውም” የሚሉት ፕሮፌሰር መረራ “እርሱ በጽናት ወደ ትግል ከገቡ የአዲሱ ትውልድ አባላት መካከል ነው” ይላሉ።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት የቀድሞ ሰብሳቢ የነበሩት ራሄል ባፌ (ዶ/ር) ከሦስት ዓመት በፊት ለሁለት ቀናት በቢሾፍቱ ከፖለቲካ አመራሮች ጋር በተደረገ ስብሰባ ላይ ከአቶ በቴ ጋር የመተዋወቅ ዕድል ማግኘታቸውን ያስታውሳሉ።

“የበርካታ ወራት እስር ጨርሶ ነበር ወደ ስብሰባችን የመጣው። ከስብሰባም ውጪ ቁጭ ብለን አውርተናል፤ በጥልቀት አውርተናል። በመጀመርያው ቀን በደንብ አድንቄው አለፍኩ። ምክንያቱም ሀሳቡን በግልጽ ይናገር ነበር። በቴ የጽናት ሰው እንደሆነ ፈጥኜ መረዳት ችዬ ነበር። ስለቤተሰቡ ስጠይቀው የፓርቲው አመራር በመሆኑ ምክንያት ያጎደለባቸውን የገለጸበት መንገድ እስካሁን አእምሮዬ ውስጥ ይመላለሳል። በጣም ግልጽ ነበር” ሲሉ ያወሳሉ።

ራሄል (ዶ/ር) የአቶ በቴን የፖለቲካ አቋም፣ ‘ጽንፈኛ’ ብለው ይገልጹታል። እንደዚያ የሚሉት አመለካከቱ ለኦሮሞ ሕዝብ የሚያደላ ስለሆነ እና ጽንፍ የያዘ ስለሆነ እንደሆነ ይናገራሉ።

የእርሳቸው የፖለቲካ አቋም ከአቶ በቴ የፖለቲካ አቋም በእጅጉ የተራራቀ ቢሆንም ግልጽ መሆናቸው እና አቋሟቸውን የሚገልጹበት መንገድ እንደሚገርማቸው ይናገራሉ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ጽንፍ ሳይዙ የጋራ አቋም እንዲኖራቸው ታስቦ በተዘጋጀ መድረክ ላይ ሊስማሙበት የሚቸገሩበትን ጉዳይ “ሳይቀባባ በግልጽ ነው የተናገረው። የገለጸው አቋም ከፊሉ የራሱ አቋም እንጂ የድርጅቱ አለመሆኑንም በግልጽ ተናግሯል” ይላሉ።

አክለውም “አያስመስልም፤ ደግሞ በየትኛውም ሁኔታ አቋምህን መብትህን እና ክብርህን በሚያንቋሽሽ መልኩ አይናገርም” ይላሉ።

ሌላ አቶ በቴን ካደነቁበት ምክንያቶች መካከል የብዙዎቹ የፖለቲካ ተወካዮች ጉድለት ነው የሚሉትን እርሱ ጋር ስላላገኙ መሆኑን ጠቅሰዋል።

“የብዙ ፖለቲካ አመራሮች ችግር ግልጽ (ትራንስፓረንት) መሆን አለመቻል ነው። ፖለቲከኞቹ ሁለት መልክ አላቸው። ስንገናኝ የሚናገሩት እና ውጪ የሚያራምዱት ሀሳብ የተለያየ ነው። በቴ ግን አስመሳይ አይደለም” በማለት ስለ ፖለቲከኛው ምስክርነት ሰጥተዋል።

በኦሮሞ ትግል ውስጥ ‘ለዘብተኛ’ ለሌሎች ደግሞ ‘ጽንፈኛ’

የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ከሚያቀነቅኑ የፖለቲካ ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑት የህብር ኢትዮጵያው ሊቀመንበር አቶ ግርማ በቀለ ልክ እንደ ራሄል (ዶ/ር) አቶ በቴን ያወቁት በጋራ ምክር ቤት ውስጥ እንደነበር ያስታውሳሉ።

ግልጽ አቋም ስላላቸውም ቅርርባቸው መጠናከሩን ጠቅሰው “ከበቴ ጋር በፖለቲካ አመለካከትም በአቋምም በጣም እንራራቃለን። ብዙ እንከራከራለን። በቴ ግን የሀሳብ ብዝኃነት የማክበር ትልቅ ችሎታ አለው” ይላሉ።

“በዚህ የሀሳብ አለመግባባት ምክንያት ማንንም አይቀየምም፣ ፊቱን አያጠቁርም፣ የሀሳብ ልዩነትን አክብሮ፣ በሀሳብ ሙግት የሚያምን ትልቅ ፖለቲከኛ ነበር።”

አክለውም “ለፖለቲካ ቅቡልነት ሲል አቋሙን እና አመለካከቱን የማይሸሽግ በአደባባይ የሚናገር ነው” ይላሉ።

አቶ ግርማ “በዚህም ምክንያት ለኢትዮጵያ ፖለቲካ መዘመን ትልቅ ሚና ይጫወታል የምንለውን ሰው ማጣታችንን ነው የተረዳሁት” ብለዋል።

አቶ በቴ በኦሮሞ ሕዝብ ትግል ውስጥ ለሕዝቡ መብትና ሀቅ የቆሙ፣ በኢትዮጵያ ብሔርተኛ ፖለቲከኞች ዘንድ አሉ የሚባሉ የአመለካከት ችግር ለመቅረፍ የሞገቱ ተብለው ይወደሳሉ።

አቶ በቴ በዚህ ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋጽኦ እውቅና ከሚሰጡ ሰዎች መካከል አቶ ዳውድ እና ፕሮፌሰር መረራ ይጠቀሳሉ።

በአንጻሩ ልክ እንደ ዶ/ር ራሄል አቋማቸው ለአንድ ብሔር በከፍተኛ ሁኔታ የወገነ ከመሆኑ የተነሳ “ጽንፈኛ” በሚል ቃል ይገለጻሉ።

ይህ ሀሳባቸው የበርካታ ኢትዮጵያ ብሔርተኝነት የሚያራምዱ ፖለቲከኞች ሀሳብ ነው።

አቶ በቴ በተለያዩ መድረኮች ያደረጓቸው ንግግሮች ተወስደው “ጽንፈኛ አመለካከት” እንደሆነ በማህበራዊ ሚዲያዎች ተጋርቶም ያውቃል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ሀሳባቸውን የሰጡት አቶ ግርማ ከአቶ በቴ ጋር በአመለካከት ቢራራቁም አቋሙን “ጽንፈኛ” ብሎ መግለጽ ተገቢ አይደለም ይላሉ።

“ሰው ለማሳነስ፣ ሀሳብህ የተለየ ሲሆን ለምን? ተብሎ የሚሰጥ ቅጽል ነው፤ ይህ በፍጹም ትክክል አይደለም። ከእኔ ጋር በሀሳቡ የተለያዩ ጠርዞች ላይ ነው ያለነው። ግን እርሱ ሀሳቤን ያከብራል እኔም ሀሳቡን አከብራለሁ።” ሲሉ ያስረዳሉ።

ፕሮፌሰር መረራ ደግሞ “አቶ በቴ በኦሮሞ ትግል ካምፕ ውስጥ እንድያውም ከሌሎቹ በላቀ ለመናገር የሚሞክር ሚዛኑን ለመጠበቅ የሚታገል ነው” ይላሉ።

“አንዳንዶቹ የሚፈልጉትን ሀሳብ ካልተናገርክላቸው ይከስሱሀል። ስለኦሮሞ መብትም ስትናገር እነርሱ እንደሚፈልጉት ካልተናገርክ ካንተ ሊርቁ ብቻ ሳይሆን ስምህን ለማጥፋት ይሞክራሉ” እላሉ።

አቶ በቴ ይህ ክስ ከቀረበባቸው አንዱ ቢሆኑም በኢትዮጵያ ብሔርተኞች ከሚባሉ ፖለቲከኞች ጭምር ሙገሳን ማግኘታቸው ከሞቱ በኋላ በተለያየ ስፍራ መታዘባቸውን ፕሮፌሰር መረራ ተናግረዋል።

አቶ በቴን በቅርበት እንደሚያውቁ የሚናገሩት የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ፕሮፌሰር ሕዝቅኤል ገቢሳ ሞታቸውን ተከትሎ ባጋሩት ጽሑፍ፣ አቶ በቴ የኢትዮጵያን እና የዓለምን ፖለቲካን ለመረዳት እና ራሳቸውን ለማብቃት መጽሐፍ ማንበብ የሚወዱ እነደነበሩ ተናግረዋል።

“ብዙ ጊዜ መጽሐፍ ላክልኝ ይለኛል። የሚጠይቀኝ መጽሐፍ ደግሞ ስለትግል ነው” የሚሉት ፕሮፌሰር ሕዝቅኤል “በሳል ነው” ይላሉ።

በ2014 በከባድ ሕመም ምክንያት ከእስር ሲለቀቁ ወደ አሜሪካ እንዲኮበልሉ በርካታ ሙከራዎች ተደርገው ቪዛ ማጣታቸውን ጠቅሰዋል።

ኋላም አዲስ አበባ ውስጥ ስራ ለማግኘት ተቸግረው መቂ አካባቢ የሚገኘውን የቤተሰባቸውን የእርሻ መሬት ለማልማት መወሰናቸውን እንደተናገሩ ገልጸዋል።

አቶ በቴ ኡርጌሳ ከቤተሰቦቻቸው ጋር

ሰላማዊ ትግል እና የአቶ በቴ አቋም

ከጥቂት ወራት በፊት ሰላማዊ ትግል በኢትዮጵያ ፖለቲካ የገጠመው ተግዳሮት እና ያለውን ተስፋ በሚል ርዕስ ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ቃለመጠይቅ ሰጥተው የነበሩት አቶ በቴ፣ “ሰላማዊ ትግል ከምንጊዜውም በላቀ አሁን ፈተና ውስጥ ገብቷል፤ ተሰፋ ግን አንቆርጥም” ብለው ነበር።

“ሰላማዊ ትግል ከምን ጊዜውም ይልቅ አስጊ ሁኔታ ላይ ነው።ሙሉ በሙሉ ተዘግቷል ብዬ ማለት አልችልም። ነገር ግን ኦሮሚያ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተዘግቷል ማለት እችላለሁ።”

“ከ2010 ለውጥ ማግስት ብዙ ምኞት እና ተስፋዎች ነበሩ ያሉት አቶ በቴ እነዚያ ተስፋዎች እና ምኞቶች የተገቡትም ቃሎች በ2012 ጠፍተዋል።” ብለው ነበር።

ገዢው ፓርቲ ተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን ሀሳቡን እንዲገዙ በተለያየ መንገድ ለማሳመን እንደሚሞክር፣ እምቢኝ ያሉትን በማሰር እና ከአገር አንዲርቁ በማድረግ እያዳከመ ነው የሚሉ ሀሳቦች አሉ።

በወቅቱ አቶ በቴ መንግሥት ከላይ የተጠቀሱትን ዘዴዎች በመጠቀም ተቃዋሚ ፓርቲዎችን እያቀጨጨ ነው ብለው እንደሚያምኑ ገልጸው ነበር።

“ይህ ሁሉ ቢኖርም ተስፋ አንቆርጥም። ተስፋ ለመቁረጥም እዚህ አልተገኘንም። ተስፋ የቆረጥነው በምርጫ ላይ ተሳትፈን ሕዘብ የመረጠው መንግሥት ለመሆን ካለን እድል ነው። የጨቋኙን ስርዓት መታገላችንን እንቀጥላለን። ይህ ሕዝብ እስካለ ድረስ ትግሉ ይቀጥላል።” ሲሉ ተናግረው ነበር።

አቶ በቴ ከ14 ዓመት በፊት ትዳር የመሰረቱ ሲሆን፣ አራት ልጆችንም አፍርተዋል።