ፖሊሶች

ከ 2 ሰአት በፊት

በፍልስጤማውያን ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት በተቃወሙ የኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፖሊሶች ተሰማሩባቸው።

በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ድንኳኖችን ተክለው በጋዛ በፍልስጤማውያን እየደረሰ ያለውን ጥቃት እየተቃወሙ ያሉ ተማሪዎች የአካዳሚክ ህንጻውን ተቆጣጥረው የነበረ ሲሆን በርካታ ፖሊሶች ተማሪዎቹን ለመበተን ሞክረዋል።

በህንጻው ላይ በሚገኘው ሃሚልተን ወደተሰኘው አዳራሽ ለመግባት ፖሊሶች በመሰላል ላይ ሲወጡ እና ተማሪዎቹንም ለመበተን ሲሞክሩ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች ወጥተዋል። በርካታ ተማሪዎች መታሰራቸው ተዘግቧል።

ዩኒቨርስቲው ተማሪዎቹ ተቃውሟቸውን እንዲያቆሙ ካለበለዚያ እንደሚባረሩ አስጠንቅቋቸው ነበር።

የፍልስጤም ደጋፊ ተማሪዎች እስራኤል በጋዛ ላይ የምታደርገውን የዘር ጭፍጨፋ በጦር መሳሪያ እና በሌሎች ነገሮች እያገዙ ነው ካሏቸው ኩባንያዎችም ጋር የንግድ ሽርክናቸውን ዩኒቨርስቲዎች እንዲያቆሙ እየጠየቁ ይገኛሉ።

እስራኤል በጋዛ በሚገኙ ፍልስጤማውያን ላይ የዘር ጭፍጨፋ እየፈጸመች ነው የሚለውን አትቀበለውም።

ተማሪዎች ተቃውሟቸውን እንዲያቆሙ ቀነ ገደብ ተሰጥቷቸው የነበረ ሲሆን ይህንንም በመተላላፋቸው የኒውዮርክ ፖሊስ በዩኒቨርስቲው ባለስልጣናት እንዲገባ ተፈቅዶለታል።

ኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ አዳራሹ በተማሪዎቹ “ቁጥጥር ሆኖ፣ ውድመት ከደረሰበት እና እንዳንገባ እግድ ከጣሉ በኋላ” ምንም ዓይነት አማራጭ አልነበረም ብሏል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ፖሊሶች በዩኒቨርስቲው መሰማራታቸውን ተከትሎ በርካታ ተማሪዎች ለእስር መዳረጋቸው ተዘግቧል።

የፍልስጤም ደጋፊዎች

በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ የቢቢሲ ዘጋቢ ኖሚያ እቅባል በርካታ የኒውዮርክ ፖሊስ አውቶብሶች ከስፍራው ሲወጡ መታየታቸውን እና ጦርነቱን በሚቃወሙ ተማሪዎች ሳይሞሉ እንዳልቀረ ዘግባለች።

በቁጥጥር የዋሉት ተማሪዎች እጃቸው ታስረው ሲወጡ በአካካቢው ተሰብስቦ የነበሩ የፍልስጤም ደጋፊዎች “ልቀቋቸው” እያሉ ድምጻቸውን ሲያሰሙ እንደነበር ተገልጿል።

በአሜሪካ የቢቢሲ የሚዲያ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ወደ 50 የሚጠጉ ተማሪዎች መታሰራቸውን ዘግቧል። ፖሊስ ተማሪዎቹ ተቆጣጥረውት ከነበረው ህንጻ ማስወጣቱን እና ጉዳት እንዳልደረሰ ገልጿል።

በመላው አሜሪካ ባሉ ዩኒቨርስቲዎች የፍልስጤም ድጋፎች እየተቀጣጠሉ እና በግቢዎቻቸው ውስጥ በድንኳኖች እያደሩ ሌት ተቀን የሚቃወሙ ተማሪዎች እየታዩ ይገኛሉ።

በቴክሳስ፣ ካሊፎርኒያ፣ ጆርጂያ፣ ሰሜን ካሮላይና፣ ዩታ፣ ቨርጂኒያ፣ ኒው ሜክሲኮ፣ ካሊፎርኒያ፣ ኒው ጀርሲ፣ ኮነቲከት እና ሉዊዚያና ባሉ ዩኒቨርስቲዎቸ ከ1 ሺህ በላይ የፍልስጤም ደጋፊዎች ታስረዋል።

እስራኤል በከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ ውስጥ የጀመረችውን የተቀናጀ ጥቃት ተከትሎ ከ34 ሺህ 180 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያስረዳል። ከነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውም በሐማስ አስተዳደር ስር ካለው የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በደቡብ እስራኤል በፈጸመው ጥቃት 1 ሺህ 200 ሰዎች መገደላቸውን እና 253 ታጋቾች መወሰዳቸውን የእስራኤል ባለስልጣናት ማስታወቃቸው ይታወሳል።