ጉስታቮ ፔትሮ- የኮሎምቢያ ፕሬዝዳንት
የምስሉ መግለጫ,ጉስታቮ ፔትሮ- የኮሎምቢያ ፕሬዝዳንት

ከ 2 ሰአት በፊት

የኮሎምቢያ መከላከያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጥይቶችን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ቦምቦች ሳይዘረፉ እንዳልቀረ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ተናገሩ።

ጉስታቮ ፔትሮ እንዳሉት ከጥይትና ቦምቦቹ በተጨማሪ ሚሳኤሎችም ጠፍተዋል።

እነዚህ ጦር መሣሪያዎች መዘረፋቸው የታወቀው የመከላከያ ግምጃ ቤት ድንገተኛ ቆጠራ በተደረገበት ወቅት ነው።

ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት ምናልባት የሠራዊቱ ከፍተኛ ኃላፊዎች እነዚህን መሣሪያዎች አውጥተው በመሣሪያ ንግድ ላይ ለተሰማሩ ደላሎች ሳይቸበችቧቸው አልቀረም።

የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር በበኩላቸው በጉዳዩ ላይ ምርመራ ተጀምሯል ብለዋል።

መከላከያ ሚኒስትሩ እንዳሉት እነዚህ መሣሪያዎች መዘረፋቸው የታወቀው በሁለት ተከታታይ ቀናት በሁለት ወታደራዊ ቀጠናዎች በተደረገ ድንገተኛ ጉብኝት ነበር።

በዚህም መሠረት አንደኛው የጦር ግምጃ ቤት 808 ሺህ ጥይቶች እና 10ሺህ የእጅ ቦምቦች ጠፍተዋል።

በሌላ ግምጃ ቤት ደግሞ 4 ሚሊዮን ጥይት፣9ሺህ ቦምቦች እና 37 ሚሳኤሎች ተሰርቀዋል።

እነዚህ መሣሪዎች ለማን ተሽጠው ይሆናል? የሚለው መረጃ ባይኖርም መከላከያ ሚኒስትሩ ግን ምናልባት ለሄይቲ አደገኛ ቦዘኔዎች ወይም ደግሞ ለጦር መሣሪያ አስተላላፊዎች አልያም በዓለም አቀፉ የጦር መሣሪያ ጥቁር ገበያ ላይ ተሽጠው እንደሆነ ገምተዋል።

“የሚያሳዝነው የተሸጡት ጥይቶች የኛኑ መከላከያ አባላትን ነው መልሰው የሚያቆስሉት” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

ኮሎምቢያ ከሸማቂ ተዋጊዎች ጋር ዓመታትን ባስቆጠረ ግጭት በድምሩ 450ሺህ ሰዎች ተገድለውባታል።

የተዘረፉትን ጦር መሣሪያዎች ተከትሎ በርካታ ባለሥልጣናት በሙስና እና በሰብአዊ መብት ጥሰት ተከሰዋል።

መከላከያ ሚኒስትሩ ኢቫን ቨላስኩዌዝ ለዜና ዘጋቢዎች እንደተናገሩት ምርመራው እንደቀጠለ ሆኖ አንዳንድ ባለሥልጣናት ከቦታቸው እየተነሱ ነው።

በቀጣይም በሌሎች የአገሪቱ የመከላከያ ግምጃ ቤቶች ተመሳሳይ ቁጥጥርና ቆጠራ እንደሚካሄድ ፍንጭ ሰጥተዋል።

የኮሎምቢያ መከላከያ በቀጠናው ካሉት አገሮች በተሻለ ዘመናዊ ትጥቅና ስንቅ ያለው እንደሆነ ይነገራል።

ይህም በዋናነት ከአሜሪካ በሚገኝ ድጋፍ ነው።

አሜሪካ አደገኛ እጽ አዘዋዋሪዎችን ለማደን በሚል ለኮሎምቢያ መከላከያ በርካታ እርዳታዎችን ታደርጋለች።